Monday, April 9, 2012

የሸክላ ማጫወቻ/ግራማፎን/ እና የሙዚቃ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ


የመጀመሪያው ግራማፎን በ1889 ዓ.ም. ሄንሪ ደ አርሊንስ እና ኒኮላስ ሊዋንቲቭ ለምኒሊክ አመጡላቸው፡፡ይኸውም መጫወቻ ብቻ ድምፅ መቅጃ አልነበረም፡፡በኋላ ግን በዓመቱ በ1890 ዓ.ም. ከንግስት ቪክቶሪያ የተላኩ የእንግሊዝ መልዕክተኞቸረ በመጡ ጊዜ ድምፅ መቅጃውን ይዘውላቸው መጡ፡፡ኢትጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፃቸው በዲስክ የተቀረፀው የምኒሊክ እና የጣይቱ ነው፡፡ይህ ቀረፃ ዛሬ በእንግሊዝ ሃገር በለንደን ከተማ ብሪቲሽ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ሪከርድ ሳውንድ በተባለው ሙዚየም ውስጥ ይገኛል፡፡
የሙዚቃ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ የተከፈተው በ1887 ዓ.ም. ነው፡፡ምኒሊክ ከሩሲያ የሙዚቃ አስተማሪ አስመጥተው ትምህርት ቤቱን በከፈቱበት ጊዜ ከመምህሩ ጋር 40 የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች መጥተው ነበር፡፡አሁን ያለው አንጋፋው የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ተመርቆ የተከፈተው ሰኔ 30 ቀን 1962 ዓ.ም. ነበር፡፡አይ እምዬ ምኒሊክ!
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ( Recording History ) በሸክላ የተቀረፁት የመጀመሪያ ስራዎች የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ዜማዎች ሲሆኑ ዘመኑም በአጤ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ነበር፡፡
ተሰማ እሸቴ የተላኩበትን የመካኒክነት ትምህርት አጠናቀው አጥጋቢ ውጤት ከማምጣታቸውም በላይ የመጀመሪያውን የአማርኛ ዜማ ሸክላ እዚያው በጀርመን ሀገር አስቀረፁ፡፡በጀርመን ቆይታቸው ወቅት የጀርመን የሙዚቃ ድርጅት ጠይቋቸው የኢትዮጵያ መዲናና ዘለሰኛ ዜማዎችን በ17 አይነት ስልት ተጫወቱ፡፡
ኩባንያው የተሰማ እሸቴን ዜማዎች በ17 ሸክላዎች የቀረፀው ሲሆን ለዜማው ባለቤት 17 ሺህ የጀርመን ማርክ ከፈለ፡፡ለአንድ ዜማ አንድ ሺህ ማርክ ማለት ነው፡፡ በዘመኑ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን አሁንም እነዚህ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ብርቅዬ ሸክላዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ይገኛሉ፡፡እነዚህ በተቋሙ እጅ ያሉት 16 ሸክላዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዜማዎችን የያዙ ሲሆን ባጠቃላይ 32 ዜማዎች ተቀርፀውባቸዋል፡፡እያንዳንዱ የሸክላ ገፅ  A ወይም B ተብሎ ተሰይሟል፤የዜማው ስም ተፅፎበታል፤የተሰማ እሸቴ ስም እና የተሰራበት ሀገር ሰፍሯል፡፡
በ1925-26 አካባቢ ዓ.ም. አካባቢ የእነ ፈረደ ጎላ፤ንጋቷ ከልካይ እና ተሻለ መንግስቱ የዜማ ሸክላዎች ብቅ እካሉ ድረስ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሸክላዎች ከ20 አመታት በላይ አቅም ባላቸው ቤተሰቦች ዘንድ በብቸኝነት በግራማፎን ሲደመጡ ቆይተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment