Saturday, July 12, 2014

የማይጮሁት ... በዓሉ ግርማን የበሉት ጅቦች -በአበራ ለማ

”ይህችን ውድ የሆነች ትንሽ ቁራሽ ሕይወት እንደ አብርሃም ቤት የለኝ፣ እንደ ሙሴ መቃብሬ ላይታወቅ፡፡ መኖር - መጻፍ - ሕይወትን በተስፋ ወደፊት እየኖርኩና ወደኋላም እያስተዋልኳት፡፡”በዓሉ ግርማ - ደራሲው
እውቁን ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማን በአጸደ ሕይወት ካጣነው፤ በዘንድሮው የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ሠላሳ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ውድ ባለቤቱ ወይዘሮ አልማዝ አበራ በዘመነ ኢሕአዴግ ስለ ባለቤቷ ከቤት እንደወጣ መቅረት ጉዳይ እከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርባ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምስክርነቷን እንድትሰጥ ተደርጋ ነበር፡፡ ያንን የእሷን የፍርድ ቤት የምስክርነት ቃል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቅርቦ ካስደመጠንም ሁለት አሠርታት ዓመታት እንደዋዛ ሊቆጠሩ ነው፡፡ ውድ ባለቤቱ ወ/ሮ አልማዝ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረበችውና እልክና ቁጭት የተመላበት የምስክርነት ቃሏ አንድምታ እንዲህ የሚል ነበር፡፡
”....የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም. ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ እቤት ስልክ ደወለ፡፡ በዓሉ ቤት አልነበረምና ስልኩን አነስቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ’... በዓሉ እንደመጣ እዚያ እቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ...’ ብሎ ስልኩን ዘጋ፡፡ በዓሉ ወደ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወደ ቤት ሲመጣ መልእክቱን ነገርኩት፡፡ ወዲያው ሻወር ወስዶ ወጣና ለመሄድ ሲጣደፍ፣ ’እደጅ ውለህ መምጣትህ ነውና እባክህ ትንሽ እህል ብጤ ቀምሰህ ውጣ’ ብለው፤ ’አልችልም... ብርቱ ቀጠሮ አለንና ወደዚያው መፍጥን አለብኝ’ ብሎኝ ፈጥኖ ከቤት ወጣ፡፡ የማታ ማታ ወደቤት ይመለሳል ብዬ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብጠብቅም የውሃ ሽታ እንደሆነ ቀረ፡፡ ቢቸግረኝ አስፋው ቤት ደወልኩ፡፡ ሚስቱ ስልኩን አነሳች፡፡ ’...አስፋው እቤት ገብቷል?...’ ስል ጠየቅኋት፡፡ ’...አዎን ገብቷል...’ አለችኝ፡፡ ይሄኔ ግራ በመጋባት፤ ’...ባሌን ከቤት ጠርቶ ወስዶት የት ጥሎት ነው እሱ ተቤቱ የገባው?...’ እያልኩ አፋጠጥኳት፡፡ ቀጥዬም ’እስኪ አቅርቢልኝና ላናግረው...’ ስላት፤ ’የገባ ምስሎኝ ነበር እንጂ አልገባም’ ብላ የመጀመሪያ ቃልዋን አጠፈችብኝ፡፡ የስልክ ንግግራችንም በዚሁ ተቋጨ፡፡ ሌሊቱንም እሱን ያየ እያልኩ በየቦታው እየደወልኩ ብጠይቅም፤ አየነው የሚል ሰው ሳላገኝ ነጋልኝ... አሁንም ለክቡር ፍርድ ቤቱ አቤት የምለው፤ አስፋው ዳምጤ ባለቤቴን በዓሉ ግርማን ከቤት ጠርቶ ወስዶ የት እንዳደረሰው ቀርቦ እንዲጠየቅልኝ ነው...” ስትል ነበር - ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ምጻኔዋን ያቀረበችው፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ይህንኑ ካስፋው ዳምጤ ጋር የተያያዘ ጉዳይ፣ ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢና ባሁኑ ጊዜ ተቀማጭነቱ ባሜሪካን አገር ለሆነ አንድ ሌላ ጋዜጠኛ ልንጠይቃት ወደ መኖሪያ ቤታቸው በሄድን ጊዜ ይህንኑ ሁኔታ ዘርዝራ አጫውታን እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ወይዘሮ አልማዝ በቁጭት ከምታነሳቸው ያስፋው ዳምጤ ጉዳይ አንዱ፣ ያ ቤተኛ የነበረ ሰው፤ ባለቤትዋ ደራሲ በዓሉ ግርማ ከታፈነበት እለት ጀምሮ ወደ ቤታቸው ብቅ ብሎ ወይም ስልክ ደውሎ የማያውቅ የመሆኑ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ”ኃጢዓተኛ ሰው ሳያሳድዱት ይሸሻል” (መጽሐፈ ምሳሌ ም.28 ቁ.1) እንዲል ቅዱሱ መጽሐፍ፤ አስፋው ዳምጤ የበዓሉ ግርማን ቤተሰብ እንደሸሸና እንደራቀ ቀርቷል፡፡

ከዚህ ከወይዘሮ አልማዝ ያቃቤ ሕግ ምስክርነት ቃል ወዲህ፤ አስፋው ዳምጤ የተባለ ሰው ሕግ ፊት ቀርቦ የተጠየቀው ነገር ስለመኖር አለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይልቅስ ትዝ የሚለን በዚያኑ በዓሉ ግርማ እንደወጣ በቀረበት ሰሞን፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት ሥራው ተባሮና ለዓመታት ቦዝኖ የነበረው አቶ አስፋው ዳምጤ፤ የኩራዝ አሳታሚ ደርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሁኖ በድንገት በደርግ የመሾሙ ጉዳይ ነበር፡፡ የዚህ ሹመት አንድምታው ከበዓሉ ግርማ ሰለባነት ጋር ተዛምዶ፤ በዘመኑ በነበሩ የቅርብ ታዛቢዎች ዘንድ ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በሽመልስ ማዘንጊያ የበላይነት ይመራ በነበረው የርእዮተ ዓለም መምሪያ ስር ይተዳደር የነበረ የኢሠፓአኮ በኋላም የኢሠፓ ተቋም ነበር፡፡ እና አቶ አስፋው ዳምጤ ለወይዘሮ አልማዝ አበራ ጥያቄ አንድ ቀን መልስ ይሰጡን ይሆናል እያልን ስንጠበቅ ካንድ ጎረምሳ እድሜ በላይ አሳልፈናል፡፡ አሁንም ትንሽ እንጠብቅ ይሆን?... ኧረ አቶ አስፋው ሆይ!... አንድ ይበሉን!!!!
አዎን... በዓሉ ግርማ በዚያን አመሻሽ ላይ እንደወጣ ቀርቷል፡፡ ወያኔ/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ፤ በራስ አሥራተ ካሣ ግቢ ወስጥ የደርግ እስኳዶች በገመድ እያነቁ የገደሏቸውን ሰዎች አጽም በጅምላ የተቀበሩበትን ጉድጓድ እያስቆፈረ አስወጥቶ በቴሌቪዥን ያሳየን ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቅዳሜ ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ላይ የቀረበ በፊልም የተደገፈ ዘገባ፤ አንድ አዲስ ዜና ይዞ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ ከዚሁ ከራስ አሥራተ ካሣ ግቢ ወስጥ ከተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ የእውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ አጽም መገኘቱን አረዳን፡፡ በዚህ የቴሌቪዥኑ ዘገባ ላይ ሁኔታውን በኢሕአዴግ በኩል ሆኖ ያስረዳ የነበረው፤ ቀድሞ በዘመነ ደርግ የአንደኛ አብዮታዊ ሠራዊት ወታደራዊ ደህንነት ኃላፊ የነበረውና በኋላ በትግራይ ውጊያ ላይ የወያኔ ወዶ ገብ ታጋይ የነበረው ሌ/ኮሎኔል አሥራት አየለ ነበረ፡፡ ሌ/ኮሎኔል አሥራት በዘመነ ኢሕአዴግ የሕዝብ ደህንነት ሚኒስቴር ያስተዳደር መምሪያ ሃላፊ ሁኖ ለጥቂት ዓመታት በመሥራትም ይታወቃል፡፡ ስለ በዓሉ ግርማ እጣ ፈንታና ፍጻሜ ሊያረጋግጥልን ችሎ የነበረው የመጨረሻ ዜና ይህ እሱ የነገረን እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡
ይሄው የጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ እንደወጣ መቅረት ጉዳይ ግን ማጠያየቁ የሁሌም እራስ ምታት ሁኖ ቀርቷል፡፡ ደራሲ ገነት አየለ አንበሴ ”የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች” በሚል ርእስ ባዘጋጀቻቸው ሁለት ቅጾች ላይ፤ ሌ/ኮ. መንግሥቱንና ይመለከታቸዋል ያለቻቸውን የደርግ ሹማምንቶች ሁሉ አነጋግራ በመጽሐፏ ገጾች ላይ ተገቢውን ስፍራ አሲዛዋለች፡፡ ካነጋገረቻቸውም ዋና ዋና ሰዎች መካከል፣ ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ጓድ ቁጥር 53 ብላ በመሰየም እውነተኛ ስማቸውን የደበቀችላቸው ዋና ሹምና ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ የአገር ደህንነት ሚኒስትሩ ይገኙባቸዋል፡፡ እኒህ ተጠቃሽ ቅጾች የታተሙት የመጀመሪያው በ1994 ዓ.ም. በሜጋ አሳታሚ ድርጅት፣ ሁለተኛው ደግሞ በሐምሌ 2002 ዓ.ም. በደራሲዋ በራስዋ አሳታሚነት ለንባብ የበቁ ናችው፡፡
ደራሲ ገነት አየለ ጠበቅ ብላ ስለ በዓሉ ግርማ ጉዳይ በስፋት ያነሳችበትና ያጠያየቀችበት መጽሐፏ የመጀመሪያው ቅጽ ነው፡፡ በዚህ በመጀመሪያው መጽሐፏ ላይ ለሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ካነሳችላቸው ደፋር ጠያቄዎች መካከል ይሄ ይገኝበታል፡፡ ”እውቁ ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ከቤቱ እንደወጣ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ ከጠፋ ከጥቂት ቀናት በኋላ መኪናው መንገድ ላይ ቆማ ተገኝታለች፡፡ ’ኦሮማይ’ በተባለው መጽሐፉ የተነሳ እንደተገደለ ይገመታል፡፡ ስለዚህ ምን ይላሉ?...” የሚል ነበር መሪ ጥያቄዋ፡፡
ሌ/ኮ መንግሥቱ ለዚህ ጠያቄ ቀጥታ ፈጣን መልስ መስጠት አቅቷቸው ብዙ ሲዋትቱ በመጽሐፉ ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ ከገጽ 211 እስከ ገጽ 219 (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ) ድረስ ወለሌ ይላሉ፡፡ ሐቅ እየመጣ ሲተናነቃቸው እውነቱን መቋቋም ሲያቅታቸው ካንዱ ነጥብ ዘለው ወደ ሌላው እየዘለሉ አስገራሚ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ሁሉንም እዚህ ላይ ዘርግፎ ማሳየት ያንባቢን ጊዜ መሻማት ነውና፤ ከመልሶቻቸው ውስጥ አንኳር አንኳሩን እየቆነጻጸልኩ ማመልከትን ፈቅጃለሁ፡፡
ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንዲህ እያሉ መልሰዋል፡፡ ”...በዓሉ ግርማን የማውቀው ከአብዮቱ በፊት ነበር፡፡ እኔ ከአሜሪካን አገር እንደመጣሁ ወደ ሐረር ከመሄዴ በፊት ለጥቂት ቀናት አዲስ አበባ አንድ ሆቴል ውስጥ አርፌ ነበር... እዚያ ቦታ ነው በዓሉ ግርማ፣ ብዙነሽ በቀለና እኔ የተዋወቅነው... የተሰጠውን የሥራ መመሪያ በእጄ ጽፌ ያረቀቅሁት እኔ ራሴ ነኝ...” እያሉ ከላይ ከተቀመጠው መሪ ጥያቄ ጋር የማይዛመድ መልስ እየመለሱ ሁለት ገጽ ሙሉ ይፈጁብናል፡፡ (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 212 - 213) ጠያቂዋ ገነት ቢቸግራት ቀጣዩን ጥያቄ ማስከተሏን ልብ እንላለን፡፡ ”ስለዚህ እርስዎ ቀይ ኮከብን በተመለከተ በዓሉ ግርማን መጽሐፍ ጻፍ ብለውታል የሚባለው እውነት ነዋ!?” ስትል ታፋጥጣቸዋለች፡፡ ሌ/ኮ መንግሥቱ ይመልሳሉ፡፡ ”አላልኩትም፡፡ እሱ የፕሮፓጋንዳውና የሥነ ጽሑፍ ዘመቻው አካል ነው እንጂ በግሉ እንዲጽፍ የታዘዘው አንድም ነገር የለም... ’ኦሮማይ’ን ጸፈ፡፡ መጽሐፉን ጽፎ ሲጨርስ ሊያሳትም ሄደ... በዓሉ ለሚመለከተው ሁሉ አሳይቷል፡፡ አልፎልኛል ብሎ አሳተመ፡፡ ተሰራጨ... ’መጽሐፉን አምጡልኝ’ አልኩ፡፡ አንድ ሳምንት ፈጀብኘ፡፡ ማታ ማታ ነው የማነበው፡፡ ጭቅጭቅ እንዳስነሳ ስለተነገረኝ በደንብ አድርጌ አንብቤ ጨረስኩት፡፡ እኔን እንዳውም አመሰገነኝ እንጂ አልነቀፈኝም...” እያሉ አሁንም ወደ ዋናው ጥያቄው ምላሽ ሳይመጡ ሦስት ገጾች ያስገሸልጡናል፡፡ (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 214- 216) ትእግስታችንን ቢፈታተነንም ወደ ፊት ስናዘግም አሁንም ከዳርዳርታ ጋር እንጨዋወታለን፡፡
ሌ/ኮ መንግሥቱ ከገጽ 216 – 219 (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም.) በሰፈረው ምላሻቸው ላይ፤ ረቂቁን እንዲያዩ አስቀድሞ በበዓሉ በራሱ ቀርቦላቸው ባለመመቸት ምክንያት ለማንበብ ያልታደሉትን ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን፣ እራሱን በዓሉ ግርማንና በኋላም የደህንነቱን ሚኒስትር ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴን ጠርተው በየተራ ማነጋገራቸውን ይተርካሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ... ”... ፍቅረ ሥላሴን አስጠራሁ... ’ይሄ መጽሐፍ እንዴት ታተመ? ከመታተሙ በፊት አይተኸዋል ወይ? ’ አልኩት፡፡ ’አላነበብኩትም ፡፡ ለቦርዱ ነው ያስተላለፍኩት ’ አለኝ... ከዚያ በኋላ በዓሉን እራሱን አስጠራሁት፡፡ ’...የብዙ ሰው ደም፣ የብዙ ሰው ላብ፣ የብዙ ሰው ትግል ውጤት ነው፡፡ ያንተ የብቻህ የሥራ ውጤት አይደለም፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ አካል ስለሆነ አቀናጅተህ ለታሪክ እንዲቀመጥ እንጂ አንተ በስምህ ባለቤት ሆነህ እንደራስህ ሥራ አገጣጥመህ እንዴት በመጽሐፍ ልታወጣ ቻልክ?’ አልኩት፡፡ ’ይሄ አልገባኝም ነበር፡፡ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም፡፡ አሁን ነገሩን ሳሰላስለው ምን ያህል ስህተት እንደሰራሁ ተረድቻለሁ’ አለ፡፡ አመነ...” ይሉናል የቀድሞው ፕሬዚዳንታችን ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፡፡
ጥቂት አንቀጾችን ካጓጓዙን በኋላ ደግሞ ”... አብዮቱን ለመጉዳት የሠራኸው አለመሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለህበት ኃላፊነት ቦታ የምትቆይበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም... ለማንኛውም አሁን ወደ ቤትህ ሂድ ብዬ አሰናበትኩት...” ካሉ በኋላ፤ ከኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ያወጉናል፡፡ ”...ትንሽ ጊዜ ቆይቶ’በዓሉ ግርማ ጠፋ’ የሚል ነገር ተነገረኝ፡፡ ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ መጥቶ ’በዓሉ ጠፋ’ አለኝ... ’ወዴት ነው የሄደው?’ ስል፣ ’እኛ አናውቅም’፡፡ ብቻ ጠፍቷል፡፡’ አለኝ... በራሴ መንገድ ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ የምጠይቃቸው ሁሉ ’ሰውዬው ብዙ ጠላቶች አፍርቷል፡፡
በትክክል ስለሆነው ነገር የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የየራሳችን ጥርጣሬ አለን፡፡ የተጨበጠ መረጃ ግን የለንም’ የሚል መልስ ነው የሚሰጡኝ፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? ከዚያ በኋላ በከተማ ውስጥም ’በዓሉ ተገድሏል’ በማለት መወራቱ ቀጠለ፡፡ ሕይወትም ቀጠለ፡፡ ሥራም ቀጠለ....’ (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 217- 219) ብለው በዓሉን የበላውን ጅብ አለማወቃቸውን በእንዲህ አይነት ፌዘኛ ምላሽ ደምድመውልናል ... ጓድ ሊቀመንበር!!!!
እኚህን የቀድሞ ፕሬዚዳንታችንን ጓድ መንግሥቱን በሙስናና የግል ሃብትን በማካበት በናማቸውም፤ በሥልጣቸው ዙሪያ በሚነሱ ጉዳያቸው ላይ ግን ለማንም ምንም ርህራሄ እንደሌላቸው ብዙ እማኞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብዙ የቅርብ ወዳጆቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ለሰይፋቸው እራት ያስገበሩ ’ናማ ኛታ!...’ ለመሆናቸው፤ ብዙ መመራመር አያስፈልግም፡፡ ጀኔራል አማንን፣ ጀኔራል ተፈሪ በንቴን፣ ሌ/ኮ. አጥናፉ አባተን፣ ኃይሌ ፊዳንና ጓዶቹን፣ ሻምበል ታምራት ፈረደን (በእጅ አዙር)፣ አሥራ አንዶቹን ጄኔራሎች እና ወዘተ... ወዘተ... መዘርዘር ይቻላል፡፡ እናም በበዓሉ ግርማ አሳዛኝ ፍጻሜ ላይ፣ ’ እጄ የለበትም፣ አልሰማሁምም፣ አላወቅሁምም...’ እያሉ ዘጠኝ ገጽ ሙሉ ቢቀሳትፉ ማን ያምናቸዋል? ማንስ ይቀበላቸዋል? የእሳቸውንም ሆነ የጓደኛቸውን የሻምበል ፍቅረ ሥላሴን መጻሕፍት ያነበበ ሁሉ፣ (ትግላችንና እኛና አብዮቱ) ሁላችንም የምናውቀውን የዚያን ዘመኑን መሥረታዊ እውነት እንዴት እየሸፈጡ ጻጽፈው እያስነበቡን እንዳሉ ስናይ፤ ማፈራችን አልቀረም፡፡ እናም እንኳን በዓሉ ግርማን የሚያህል በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በቋሚ ተጠሪነት ማእርግ የፖለቲካ ሹመኛ፣ እውቅ ጋዜጠኛና ደራሲ የሆነን ሰው ያሟሟት ጉዳይ ይቅርና የሌላ ሌላ ተራውን ያብዮት ሰለባ ሰው መጨረሻ ሁሉ ሲያውቁ ኖረዋል፡፡ እናም ያያጅቦ ድርሻቸውን መፈጸማቸውን አለማመናቸው የንጹሕ ሕሊና ድሃ መሆናቸውን ብቻ ነው አድምቆ የሚያስነብበን፡፡ በነገራችን ላይ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ”እኛና አብዮቱ” በተሰኘው አዲስ መጽሐፋቸው ላይ እያዩ ሳያዩዋቸው፣ እያወቁ ሳያውቋቸው ካለፏቸው አቢይ ጉዳዮች መካከል የበዓሉ ግርማ ግድያ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ አንዲት አረፍተ ነገር እንኳን ሳያነጥቡ በአርምሞ አለፈውታል፡፡
ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ሁሉ፣ ደራሲ ገነት አየለ በዚሁ ”የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ” በተሰኘው መጽሐፏ ላይ፤ የደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማን መጨረሻ ለማወቅ ከጠየቀቻቸው ሰዎች ማካከል የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ይገኙበታል፡፡ ጸሐፊዋ ገነት አየለ ለእኒህ ሰው ያቀረበችላቸው መሪ ጥያቄ የሚከተለው ነበር፡፡ ”በዓሉ ግርማ እንዴት እንደተገደለ ያውቃሉ?” የሚል ነበር ጥያቄዋ፡፡ ኮሎኔል ተስፋዬ ሲመለሱ፤ ” በዓሉ ግርማ በጻፈው መጽሐፍ በኦሮማይ የተነሳ ችግር ሲገጥመው እኔጋ መጣና አነጋገረኝ... ’ሊቀመንበሩ ሊረዱልኝ ያልቻሉት ምክንያት አልገባኝም፡፡ ጥርስ ተነክሶብኛልና እባክዎን አስረዱልኝ’ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔ በውነቱ እሱ እዚያው አጠገቤ እንደቆመ የሊቀመንበሩ ረዳት ለሆነው ለሻምበል መንግሥቱ ገመቹ ስልክ ደወልኩ፡፡ ’እባክህን የዚህን ሰው ነገር ለሊቀመንበሩ አጣመው ያቀረቡላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡እንዴት ነው ይሄን ነገር ግልጽ የምታደርግላቸው? ወይም የሚቻል እንደሆነ ሁለታችንም ቀርበን እናስረዳ፡፡ አንተ ጋር ልኬዋለሁ የምትችለውን አድርግልት’ አልኩት፡፡ ’ግድየለም ይላኩት፤ እኔ አነጋግረዋለሁ፡፡ ይሄ ምንም አይደለም’ አለኝ፡፡ ከዚያ ወደዚያው ላኩት... ሌላ ጊዜ ቆይቼ ’የበዓሉ ነገር እንዴት ሆነ?’ ብዬ ሻምበል መንግሥቱን ጠየቅሁት፡፡ ’አስረድቻቸዋለሁ፤ ግን እንዴት እንደሆን እንጃ ለጊዜው መለስም አላሉም’ አለኝ፡፡ ’አይ ይሄ የሳቸው የተለመደ ባሕሪ ነው... አዝማሚያው መልካም ሲሆን፤ ነገሩን በጽሞና አስረዳቸው፡፡’ አልኩት...” (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 72) ይሉና ጉዳዩን ለሻምበል መንግሥቱ እንደተዉት ያወሳሉ፡፡
ይህንን ”በዓሉ እኔጋ መጣና አነጋገረኝ...” ሲሉ ለገነት አየለ ቃለ መጠይቅ የሰጡትን የደህንነት ሚኒስትሩን የኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴን አባባል፤ የደራሲ በዓሉ ግርማ የበኩር ልጅ ወይዘሮ መስከረም በዓሉ በላከችልኝ የኢሜል መልእክት ላይ በእጅጉ ኮንናዋለች፡፡ ”ቅጥፈት ነው”ም ትላለች፡፡ የላከችልኝ የኢሜል መልእክቷ እንዲህ ይነበባል፡፡
” Gashe Abera,
... Tesfaye W/Selassie lied when he said Baalu came to his office to plead with him. The truth was, Tesfaye sent his secretary to our house instead. Baalu asked Tesfaye’s secretary, “what did I do to your boss that he is upset and complaining?” The secretary said, “Oh Ato Baalu, you are really harsh on us…” She visited for about 30 min and left. This secretary used to work at Ministry of Information as one of Baalu’s secretaries. She got transferred to become Tesfay’e secretary… Baalu never visited the guy, nor spoken with him after they banned Oromaye. These are a bunch of liars; reading what they had said about Baalu or anyone else made me sick to my stomach. At times they
5
made me hate that I was born from that pathetic place. How could people stand themselves? How could they sleep at night? It takes a generation to heal what happened but unfortunately the saga continues…” የመስከረም በዓሉ የኢሜይል መልእክት፡፡
የወይዘሮ መስከረም በዓሉ ኢሜይል ያማርኛ ነጻ ትርጉሙ ደግሞ እንዲህ ይነበባል….
“ጋሼ አበራ
…በዓሉ ላቤቱታ እሱ ቢሮ መጥቶ እንደነበር ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ሲናገር ዋሽቷል፡፡ እውነቱ ግን በተገላቢጦሹ ነው፡፡ ተስፋዬ ጸሐፊውን ወደ መኖሪያ ቤታችን ልኳት ነበር፡፡ በዓሉ የተስፋዬን ጸሐፊ እንዲህ ሲል ጠየቃት፡፡ ’አለቃሽን ምን አድርጌው ነው እንደዚህ የተበሳጨብኝና የተማረረብኝ?’ ጸሐፊዋም፤ ‘ኦ አቶ በዓሉ በእርግጥ አንተኮ በኛ ላይ የከፋህ ነህ’ ስትል መለሰች፡፡ ከእኛ ጋር የሠላሳ ደቂቃዎች ቆይታ አድርጋ ተለየችን፡፡ ጸሐፊዋ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ከበዓሉ ጸሐፈዎች እንደ አንዷ ነበረች፡፡ የተስፋዬ ጸሐፊ ለመሆን ዝውውር አግኝታ ሄዳ የነበረች ነች፡፡ … ኦሮማይ ከታገደ በኋላ በዓሉ ይህን ሰው አግኝቶት ወይም አነጋግሮት አያውቅም፡፡ እነዚህ ልቅምቃሚ ውሸታሞች ናቸው፡፡ ስለበዓሉም ሆነ ስለሌሎች የተናገሩትን ሳነብ አንጀቴን ነው ያቆሰለኝ፡፡ ስለእነዚህ ክፉ ሰዎች ባሰብኩኝ ቁጥር ከዚያች አሳዛኝ አገር መወለዴን እንድጠላ የሚያደርጉኝ ጊዜያት አሉ፡፡ ሰዎች እራሳቸውን ችለው እንደምን መቆም ይቻላቸዋል? ሌሊት እንደምን እንቅልፍ ሊወስዳቸው ይችላል? የሆነውን ሁሉ ለማከም የትውልድ እድሜን ይጠይቃል፡፡ ግና ምን ያደርጋል የትናንት እውነት ዛሬም ይቀጥላል…” (የመስከረም በዓሉ ኢሜይል … ነጻ ትርጉም የራሴ)
ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ቀደም ብለን ባነሳነው ”የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 72” በሰጡት ቃለ መጠይቅ ቀጣይ አንቀጾች ላይ ደግሞ፣ በዓሉ ግርማ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ችግር እንዳለበት ጠቆም አድርገው የመጥፋቱንም ዜና ያካፍሉናል፡፡ እንዲህ እያሉ... ”በዓሉ መቼም በዚህ መጽሐፉም ብቻ ሳይሆን፤ በሌላ በሌላም ከኛ ጋር በመሥራቱም ሁሉ ብዙ ሰዎች ጠምደውታል፡፡ የሥራ ባልደረቦቹም ቅርበት በመፍጠሩ ጥላቻ አላቸው፡፡ ቆይቶ ጠፋ የሚል ከደህንነቱ ካንደኛው ቅርንጫፍ ተሰማ... ፈልጉት ሁሉ ብለን በጽሑፍ አስተላለፍን፡፡ ከዚህ ውጭ በኛ መሥሪያ ቤት በኩል የምናውቀው ነገር የለም... በምንም ዓይነት እኛጋ አልታሰረም፡፡ በምንም ዓይነት፡፡ እኔ ምንም የሰማሁት ነገር የለም... ስለዚህ በዓሉን የማስገድልበት ምክንያት የለኝም፡፡” (ገጽ 73) ሲሉ በዓሉን የሚመለከተውን አስገራሚውን ቃለ መጠይቃቸውን ጨርሰዋል፡፡ ኮሎኔል ተስፋዬ ሆይ!..... አሁን በላይኛው ቤት እየኖሩ ነው፡፡ እንዲያው ይህን መሰሉን ጥያቄ አንድዬ ሲያነሳበዎት ምን ብለው መልሰውለት ይሆን? እዚያም ዋሽቶ ማምለጥ ይቻል ይሆን? ተሆነ... እግዚኦ ነው!!!!!
ለማንኛውም የደራሲ በዓሉ ግርማ ልጅ ወይዘሮ መስከረም ይህን የኮሎኔል ተስፋዬን ሌላ ቅጥፈት የምታጋልጥበት በኢሜይል ያደረሰችኝ ሌላም ነጥብ አላት፡፡ እንዲህ ይላል…
“ Gashe Abera
… If you would like, you can also add how security agents were following him wherever he goes. They used to follow him all the way to the apartment compound and turned around and leave once he steps out of his car. It became such a normal routine that one of the kids in the area, was able to capture the plate number of the regular agent and gave it to Baalu and Almaz. Yes it may be 30 years ago but that kid is now a small business owner and should able to tell the story in his own words…” ከመስከረም በዓሉ ከደረሰኝ የኢሜይል መልእክት የተቆነጸለ፡፡
ወደ አማርኛ የተመለሰውም ነጻ ትርጉም እንዲህ ይነበባል…
“ጋሼ አበራ
… መልካም ፈቃድህ ከሆነ፣ የጸጥታ ሰዎች በዓሉን እንዴት በየሄደበት ቦታ ሁሉ ይከታተሉት እንደነበረ በጸሑፍህ ላይ ማከል ትችላለህ፡፡ እስከምንኖርበት ሕንጻ ቅጥር ግቢ ድረስ እየተከታተሉት ልክ ከመኪናው ላይ ሲወርድ አይተው፣ መኪናቸውን አዙረው ይሄዱ ነበር፡፡ ይህ ድርጊት በየእለቱ ይፈጸም ስለነበር፤ ባካባቢው የነበረ አንድ ልጅ የጸጥታ ሠራተኞቹን የመኪና ታርጋ ቁጥር መዝግቦ ለበዓሉና ለአልማዝ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ ሠላሳ ዓመታት ቢያልፉም፣ ያ ልጅ ዛሬ ያነስተኛ ንግድ ባለቤት ሁኖ በዚያው አካባቢ ይኖራልና ቢጠየቅ ታሪኩን በራሱ አንደበት ሊተርከው የሚችለው ነው…” (ነጻ ትርጉም የራሴ) ከዚህ የወይዘሮ መስከረም የምስክርነት ቃል ልንረዳ እንደምንችለው፣ ከላይ ኮሎኔል ተስፋዬ “…በኛ መሥሪያ ቤት በኩል የምናውቀው ነገር የለም... በምንም ዓይነት እኛጋ አልታሰረም፡፡ በምንም ዓይነት፡፡ እኔ ምንም የሰማሁት ነገር የለም... ስለዚህ በዓሉን የማስገድልበት ምክንያት የለኝም፡፡” ሲሉ መዋሸታቸውን የሚያጋልጥ የደህንነት ክፍሉ አንድ እኩይ ተግባር ነው፡፡
ያገሪቱ ርእሰ ብሄር የሆኑት ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ እንደጲላጦስ እጃቸውን ታጥበው ከደሙ ነጹህ ነኝ ያሉትን ይበልጥ፤ የደህንነቱ ቁንጮ ሰው ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴም በተራቸው፤ ”ዐይኔን ግምባር ያድርገው” ብለው ምለው ተገዝተው እራሳቸውን እንዴት ነጻ ለማውጣት እንደታገሉ አስተውለናል፡፡ እንግዲህ እንዲህ እንዲህ እያለ በዓሉ ግርማን የበላው ትልቁ ጅብ አልጮህ ሲል እያየን ታዝበናል፡፡ ትንንሾቹ ጅቦችስ የተሻለ ሕሊና ኖሯቸው የማታ ማታ ይጮኹ ይሆን? እስቲ አብረን ኮሎኔል ተስፋዬ ከላይ በሰጡት ምላሻቸው ላይ፤ ”የሥራ ባልደረቦቹም ቅርበት በመፍጠሩ ጥላቻ አላቸው፡፡” ያልዋትን ያንዲት አረፍተ ነገር ጭብጥ በውስጣችን እያመላለስን፤ ወደፊት እናዝግምና እንያቸው፡፡
ይቺው መርማሪ መርማሪ ጸሐፊ ገነት አየለ የበዓሉ ግርማን መጨረሻ የማወቅ ጉጉትዋን በሁለቱ ቱባ ያገሪቱ ቁንጮዎች ምላሾች ላይ ብቻ ተስፋ ቆርጣ አልተወችውም፡፡ ”ጓድ ቁጥር 53” ብላ የሰየመቻቸውንም ሌላ ቱባ የደርግ ባለሥልጣን በር አንኳኩታለች፡፡ እኒህ ሰው ”የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 59” ላይ የሰጧት ምላሽ እንዲህ ይነበባል... ”ስለ በዓሉ ግርማና ስለ ጄኔራል ታሪኩ ዓይኔ አሟሟት የማውቀውን ልንገርሽ...” ሲሉ፤ ይህን ቀጥሎ የሚታየውን አንድ ገጽ አስተያታቸውንና ምስክርነታቸውን መስጠታቸውን ልብ እንላለን፡፡
በዚህ የ”ጓድ ቁጥር ሀምሳ ሦስት” ምላሽ ላይ፤ በኮሎኔል መንግሥቱና በኮሎኔል ተስፋዬ በኩል ብዙ ግልጽ ሳይሆኑልን እየተድበሰበሱ ሲነገሩን የነበሩት ነጥቦች ሁሉ ፍንትው ብለው ይታዩናል፡፡ በዓሉ ግርማን ለማጥፋት ከነኮሎኔል መንግሥቱ ጋር ከመሰጠሩት ጓደኞቹ መካከል ሙሉጌታ ሉሌ አንዱ እንደሆነ በዚህ መጽሐፍ ገጽ 59 ላይ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ጸሑፍ መግቢያ ላይም አስፋው ዳምጤ የተባለ ”ጓደኛው” ከቤት አስጠርቶ እንደወጣ እንዳስቀረው፤ ባለቤቱ ወይዘሮ አልማዝ አበራ ለፍርድ ቤት የሰጠችውን ቃልዋን ማስታወሳችንን ልብ ይሏል፡፡ እናም እዚህ ላይ እንደመንቃት እንልና ”ሙሉጌታ ሉሌና አስፋው ዳምጤ በጋራ በዚህ ሚሽን ላይ የየራሳቸውን ድርሻ ለመፈጸም ሰልፋቸውን አሳምረው ይሆን?” የሚል ጠያቄ በውስጣችን ማቃጨሉ አይቀርም፡፡ ”ለምን?” ቢሉ ጓድ ቁጥር ሀምሳ ሦስት እየነገሩን ያለው ይህ ዓይነቱን የማጥፋት ጥምሮሽ ሴራ ጉዳይ ነውና ነው፡፡ እንዲህ ይጠቀሳሉ ጓድ ቁጥር ሀምሳ ሦስት፤ ”... ለበዓሉ ቅርብ የሆኑና ጓደኞቹን ጭምር አሳመኑና ሁሉም በየተራ መንግሥቱ ጋ እየሄዱ አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲነግሩት ተደርጎ፤ በዓሉን የማጥፋቱ ሴራ ተቀነባበረ...” (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ገጽ 59) ይሉናል ጓድ ቁጥር ሃምሳ ሦስት፡፡
ይህን ያፈጠጠ እውነት ይዘን፤ ”ሙሉጌታ ሉሌ ምን ፍለጋ ጓደኛውን ለማስጠፋት ተባበረ?” ብለን ስንጠይቅ፤ እኚሁ ጓድ ቁጥር ሀምሳ ሦስት፤ ”ለበዓሉ ቅርብ የሆነና ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሚያውቀው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰው ሙሉጌታ ሉሌ ለደህንነት ይሠራል... የበዓሉን ቦታ ይመኝ እንደነበር አውቃለሁ...” (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ገጽ 59) ሲሉ ግልጽ ምስክርነታቸውን የሰጡበትን አረፍተ ነገር እናገኛለን፡፡ ”ጓደኛው” አስፋው ዳምጤ በዓሉን ከቤቱ አውጥቶ ባስረከበ ማግሥት ከሥራ አጥነት ቡዘና ወጥቶ፤ ባንድ ጊዜ የኩራዝ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ተደርጎ እንደተሾመው ሁሉ፤ ሙሉጌታ ሉሌም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሁኖ ለመሾም ቋምጦ እንደነበር ነው ጓዱ የሚነግሩን፡፡ አዎን... ሙሉጌታ ሉሌ የተመኘውን ሹመት አላገኘም፡፡ በወቅቱ ከመምሪያ ኃላፊነት የሹመት ጉርሻ በላይ አላገኘም፡፡ ቢያነስ ቢያንስ ለቦታው መጣኝ የሚሆን የረባ ዲፕሎማ ወይም የመጀመሪያ ድግሪ የግድ ይል ነበርና ቋሚ ተጠሪ ወይም ምክትል ሚኒስትር መሆን አልተሳካለትም፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ እየታገለ እንዳለም ባልጠበቀው ሰዓት ስመ ጥሩው ጋዜጠኛና ምሁር መርእድ በቀለ ምክትል ሚኒስትር ሆኖ ተሾመና አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በድንጋጤ ልቡን ታሞ ለሕክምና ወደ ውጭ አገር ተላከ፡፡ ከሞት ተርፎም ተመለሰ፡፡
ወደ ገነት አየለ ቅጽ ሁለት መጽሐፍ መለስ ብለን ስንቃኝ ደግሞ፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ስለ ሙሉጌታ ሉሌ የሰጡትን አሉታዊ አስተያየትም እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ፤ ”...ሙሉጌታ ሉሌ ስለሚጽፈው ብዙ አትደነቂ፡፡ ልማዱ ነው፡፡ አገራችን በወያኔ እንደተወረረች እኔን አስመልክቶ፤ ’ አጥፍቶ መጥፋት’ የሚል መጽሐፍ ጽፎ ለወያኔ እጅ መንሻ ሲያቀርብ እኔን ፐርሰናል የሆነ ስድብ ሁሉ ነው ሙልጭ አድርጎ የሰደበኝ፡፡ ወያኔዎቹም ዞር ብለው አላዩትም እንጂ እሱ ያቺን ጻጽፎ አንድ ቦታ ይሰጡኛል ብሎ ነበር ተስፋ ያደረገው...” ሲሉ ልማደኛ ምንደኛ ጸሐፊ መሆኑን በማመልከት አሽሙረውበታል፡፡ ኮሎኔል መንግስቱና ሙሉጌታ ሉሌ ደህና አድርገው እርስ በእርስ የተናበቡ መሆናቸውን ማስተዋል አይገድም፡፡ በራሱ በሙሉጌታ ተዘውታሪ ጥቅስ ”አንተም ብሩተስ?...” ያሉት ዓይነት ይመስላል - ኮሎኔል መንግሥቱ፡፡
ሊቀመንበር መንግሥቱ በዘመነ ሥልጣናቸው እነበዓሉ ግርማን ለማስወገድ እነሙሉጌታ ሉሌን ተጠቅመው የቋመጡለትን ሹመት ሳይሰጧቸው ገሸሽ ያደረጓቸውን ያህል፣ እነ ሙሉጌታም ጊዜያቸውን ጠብቀው ቁጭታቸውን፣ ብስጭታቸውንና ንዴታቸውን ተወጥተውባቸዋል፡፡ ወያኔ/ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ በሁለት ወራት ውስጥ ሙሉጌታ ”አጥፍቶ መጥፋት”ን ለቁርስ ነበር ያደረሰው፡፡ በዚህ መጽሐፉ አማካኝነት ጓድነታቸው የበቀል ጽዋን እንዲጎነጩ መደረጋቸውን ይስቱታል ብለን አንገምትም፡፡ ”ለምን? ” ቢሉ ጨዋታው እንዲህ ወዲህ ነበርና ነው...
የኮሎኔል መንግሥቱና የሙሉጌታ ሉሌ የወቅቱ ውልና ስምምነት፤ በብልጣብልጦቹ ሁለት ያልታወቁ ደብተራዎች ድርጊት ሊመሰል የሚችል ነው፡፡ እኒህ ያልታወቁት ሁለት ደብተራዎች ወዳንድ ንፉግ ሰው ቤት ምሳ ተጋብዘው ይሄዳሉ አሉ፡፡ ያ ጋባዥ ሰው ለተጋባዥ ደብተሮቹ ያዘጋጀው ምግብ ክትፎ ነበር፡፡ ታዲያ ስስታሙ ጋባዥ ክትፎው እንዳይበላበት ሲያወጣ ሲያወርድ አንድ መላ አግኝቶ ኖሯል፡፡ ለሁለቱም ከክንድ የረዛዘመ የቀንድ ማንኪያውን ከክትፎው ጋር አዘጋጅቶ ጠበቃቸው፡፡ ደብተሮቹ በዚያ ረዥም ማንኪያ እየዛቁ ክትፎውን ሊበሉ ቢታገሉም አልቻሉም፡፡ ረዥሙን ማንኪያ ወደ አፋቸው ሲመሩ፣ መድረሻውን እየሳተ ወደየ ጆሮ ግንዳቸው ይዘምት ጀመር፡፡ እናም ያንን ምራቅ የሚያስውጥ ክትፎ መብላት አልቻሉም፡፡ ”ምን እናድርግ? ” ሲሉ ደብተሮቹ ተመካከሩ፡፡ አንድ ዘዴም አገኙ፡፡ ”ዚአየ ለዚአከ... ዚአከ ለዚአየ” የምትል ዘዴ ቀየሱ፡፡ ”እኔ ላንተ፣ አንተም ለኔ” እንደማለት ነው፡፡ እናም አንደኛው ደብተራ ሌላኛውን ጓደኛውን በዚያ ረዥም ማንኪያ አየዛቀ ክትፎውን ሲያጎርሰው፣ ጓደኛውም በዚያው
መልክ አጸፋውን እየመለሰ በስምምነታቸው መሰረት ያንን ጥኡም ክትፎ ሙልጭ አደርገው ጨረሱት ይባላል፡፡ ከሁለት አንዱ ደብተራ ስምምነቱን ቢገድፍ ኖሮ፤ አንዱ ፋይዳውን ሲፈጽም ሌላኛው የበይ ተመልካች ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ የኮሎኔል መንግሥቱና የሙሉጌታ ሉሌም ስምምነት እንደደብተሮቹ ስምምነት ጸንቶ ቢቆይ ኖሮ፤ አያ ሙሉጌታን ያን ያህል ግዘፍ ነስቶ ባላስቆጣና ”አጥፍቶ መጥፋት”ን የመሰለ ግባስ ሥራ ባላሠራው ነበር፡፡
ያ ”አጥፍቶ መጥፋት” የተባለ የሙሉጌታ ሉሌ ቅርሻት ግን፣ በዘመነ ወያኔ ለስድሳ ነባር ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ከማስታወቂያ ሚኒስቴር መባረር ጦስ ሆኗል፡፡ እነበረከት ስምኦን የሙሉጌታን እጅ መንሻ ካለመቀበላቸውም በላይ፣ ሕዝቡ የልማደኛ አድርባይ ጋዜጠኞች መዘባበቻ ምሳሌ አድርጎት ሲነጋገርበት እየኖረ ነው፡፡ ለማንኛውም ይህ የገነት መጽሐፍ ታትሞ ከወጣና ለሕዝብ ከተሰራጨ የመጀመሪያው ቅጽ 12 ዓመታት፣ ሁለተኛው ቅጽ ደግሞ አራት ዓመታት ሞልቶታል፡፡ አቶ ሙሉጌታ የረባ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም አልሆነም፡፡ ጦቢያ መጽሔት 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 12፣ 1994 ዓ.ም. ላይ እራሱ ጠያቂ እራሱ መላሽ ሁኖ በራሱ መጽሔት ላይ የሰጠውን ዓይነት የተጠና የማምለጫ ኢንተርቪው ወደ ጎን ትቶ በእውነት የሆነውን ሁሉ ቢያካፍለን መልካም ነው፡፡
አቶ ሙሉጌታ በዚህ እራሱ ለራሱ በሰጠው ኢንተርቪው ላይ ”... ለነገሩ ከእሳቸው ጋር (ከኮሎኔል መንግሥቱ ጋር ለማለት ነው) ባለው የግል ግንኙነት ምክንያት በዓሉን ምን አደረገ ለማለት እንደፈለጉ (ባለመጽሐፎቹን ለማለት ነው) ግልጽ አይደለም” (ጦቢያ 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 12፣ ገጽ 35፣ 1994 ዓ.ም.) ሲል ጣት ያስቀሰረበትን ዐቢይ ጉዳይ፣ እንዲህ ድብስብስ አድርጎ አልፎታል፡፡ እናም ከሱም እውነቱን እስክንሰማ ድረስ በተጨማሪ ስንት ዓመታት እንጠብቅ? ወይንስ ዝምታውን በጨዋ ደምብ እንደመቀበል ቆጥረን እንለፈው?... (በጥቅሱ ውስጥ በቅንፍ የተቀመጡት ማጣቆሚያዎች የራሴ ናቸው)
የእኚሁኑ የቁጥር ሃምሳ ሦስትን ምስክርነት ጉዳይ ሳንቋጭ አንድ ተጨማሪ ነጥባቸውንም እዚህ ላይ ማስታወስ ለሚዛናዊ አተያያችን እርካብ ይሆነናል፡፡ እኚህ ምስክር ስለበዓሉ ግርማ ጉዳት ላይ መውደቅ በሰጡት አስተያት የመጨረሻ አንቀጽ ላይ ያሰፈሩትንም ልብ ብሎ ማስተዋል ይጠቅማል፡፡ ከኮሎኔል መንግሥቱ፣ ከኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ፣ ከሙሉጌታ ሉሌ በተጨማሪም የሽመልስ ማዘንጊያና የሌሎችም አሉታዊ ሚና በዓሉን ክፉ ነገር ላይ እንደጣለው አክለውበታል፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶች የርእዮተ ዓለም መምሪያ ም/ኃላፊ የነበረውን አያልነህ ሙላትንና ማሞ ውድነህን ይጨምራሉ፡፡ ማሞ ውድነህ ደግሞ በእንዲህ እንዲህ ዓይነቱ ውሽክትናና ሰውን መርጆ ማስመረጅ ክፉ ባሕሪው የታወቀ ሰው ነበር፡፡ የክቡር ደራሲ ከበደ ሚካዔልን የየእለት ውሎና እንቅስቃሴ እየተከታተለ፤ ለነኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴና ለደርግ ሰዎች በማቀበል ሴራ ተጋልጦ ፒያሳ ላይ ባቶ ከበደ ሚካዔል የደረሰበትን ያደባባይ ውርደት አንረሳውም፡፡ እንዲህ ነበር የሆነው...
አቶ ከበደ ከሚኖሩበት ጣይቱ ሆቴል ወጣ ብለው፤ በደጎል አደባባይ አካባቢ ንፋስ ሲቀበሉ አሸምቆ ሲከታተላቸው የነበረውን ማሞ ውድነህን ከሩቅ ያዩታል፡፡ በእሳቸው ላይ የስለላ ሥራ እንደሚሠራ ቀደም ብለው ያገኙትን ጥቆማ በሆዳቸው ይዘው እስኪጠጋቸው ይጠብቁታል፡፡ አጠገባቸው ሲደርስ ” ጤና ይስጥልኝ አቶ ከበደ...” ብሎ ለሰላምታ እጁን ሲዘረጋ፤ አቶ ከበደ ከመቅጽበት ”በሕግ አምላክ ይህን ሰላይ ያዙልኝ!...” እያሉ አደባባዩን ቀውጢ ያደርጉታል፡፡ አቶ ከበደን በደንብ የሚያወቋቸው የፒያሳ ሊስትሮዎችና ጎዳና ተዳዳሪዎች ማሞን ለመደብደብ እስከ ራስ መኮንን ድልድይ ድረስ እንዳሳደዱት፤ በወቅቱ የኢትዮጰያ ደራስያን ማህበር ሊቀመንበር የነበረው እውቁ የሥነ ጥሑፍ ሰው ደበበ ሠይፉ ከደረሰው ሪፖርት ተነስቶ በ1981 ዓ.ም. በማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አጋልጦት፤ ማሞ ከጉባዔው እንዲባረር መደረጉን እናስታውሳለን፡፡ ስለዚህም ነው የማሞ ዓይነቱ ልማደኛ ጆሮ ጠቢና አድርባይ እርኩስ ተግባር እንዳዲስ የማይደንቀን፡፡ እናም እነ አቶ ሽመልስ ማዘንጊያ ይህን የተቀሰረባቸውን ውንጀላ አይተውት ከርመዋል፡፡ ግን አንዴም ከሸገር መናኸሪያቸው ሁነው ምላሽ የሰጡትበት አጋጣሚ የለም፡፡ እነ እሳቸውንም ሌላ ብዙ ዓመት እንጠብቅ ይሆን? እንዲያው ያንን የብእር አምበል ”እኔ በላሁት!...” የሚል ያንበሳ ልብ ያለው ጅብ ይጥፋ?! ወይ ነዶ!!!!!!!!
ግን ግን እኒህ የቅርብ ውስጥ አዋቂ ጓድ ቁጥር ሀምሳ ሦስት ማን ይሆኑ? መቼም በዚያን ጊዜ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ እንደ ሙሉጌታ ሉሌ ላለ የመምሪያ ኃላፊ የቅርብ አለቃ ሆኖ ከኢሠፓአኮ የርእዮተ ዓለም መምሪያ ኃላፊ ከሽመልስ ማዘንጊያ በቀጥታ ትእዛዝ ሊቀበልና ሊያስፈጽም የሚችል በሚኒስትር ማእርግ ደረጃ ያለ ሰው ብቻ ነው፡፡ እና በገነት መጽሐፍ ገጽ 59 ላይ እንደምንመለከተው ጓድ ቁጥር ሃምሳ ሦስት ”... ’ይህንን ሰው ሊቀመንበሩ ይፈልጉታልና እንዲመጣ’ ብሎ ሽመልስ ማዘንጊያ ደወለልኝ፡፡ የበዓሉን ቦታ ይመኝ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ መልእክቱ ሲደርሰው እኔጋ መጣና ’ለምን እንደጠሩኝ ታውቃለህ ወይ?’ አለኝ፡፡ እንደደማላውቅ ነገርኩትና ሄደ፡፡ ከዚያ ሲመለስ አሁንም በኔ በኩል አለፈና ’ስለበዓሉ ሊያነጋግሩኝ ነው የጠሩኝ አለኝ...’ በማግሥቱ ወደማታ በዓሉን የደህንነት ሰዎች ይዘውት እንደሄዱ ከቤተሰቡ ሰማሁ...” ያላሉ፡፡ ታዲያ እኚህ ሰው ማን ይሆኑ እንዲህ ለጠሪም ለተጠሪም እመሃል ያሉ ቅርብ ሰው?... የወቅቱን የማስታወቂያና መርሃ ብሄር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኮሎኔል ፈለቀ ገድለ ጊዮርጊስን እንጠርጥር ይሆን? በወቅቱ የነበሩት ሚኒስትር እሳቸው ነበሩና፤ አንድ ቀን ከዚህ የበለጠም የሚያወቁት ምስጢር ኖሮአቸው ያካፍሉን ይሆናል ብለን እንጠብቅ ይሆን?...
በነገራችን ላይ አቶ ሙሉጌታ በዚህ ለራሱ ጥያቄ እራሱ ምላሽ በሰጠበት የጦቢያ ቃለ መጠይቁ ላይ፤ ብዙ ብዙ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ያልተላበሱ ተራ ስድቦችንና አስተያየቶችን አስነብቦናል፡፡ ይሄውም በተለይ በደራሲዋ በገነት አየለ የግል ሰብእና ላይ የተነጣጠረው ያቶ ሙሉጌታ ትችት ነው፡፡ ገነት እኮ እንዳንድ ጸሐፊ ከምንጩ ያገኘቻቸውን ማስረጃዎች እየጠቀሰች ማቅረብ ነው ግዴታዋ፡፡ ይሄ ወዳጄን ሙሉጌታ ሉሌን ይመለከተዋልና እያየሁ ልለፈው ብላ በወገናዊነት አስልታ ብትሠራው ኖሮ፤ ሥራዋ ጭራሹኑ ተአማኒነት የሌለው ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ ምንጯን እየጠቀሰች ያገኘችውን አቅርባለች፡፡ ”ለምን ወንጀሌን፣ ገመናዬን አልሸፈነችልኝም?” በሚል አህያውን ቢፈሩ ዳውላውን ዓይነት አካሄድ ካንድ እድሜ የጠገበና በፕሬስ ዓለም ብዙ ከቆየ ሰው አይጠበቅም፡፡ ንዴቱ በገነት ምንጮች ላይ ከሆነ፣ እዚያው ከምንጮቹ ጋር በእጅ ባለ ተጨባጭ ማስረጃ መከራከር ያባት ነው እንላለን፡፡ ሳይንሱማ ከጭብጡ (ከነጥቡ) ጋር ተፋለሚ ግለሰቡ ላይ ካተከንክ ”ቴስታ ዲጋሊኖ ትባላለህ” ይላል፡፡ ግና ማን ሰምቶ ማንስ ተስተምሮ!.... ነገሩ ”ጅብ ቲበላህ አብረኸው በልተህ ተቀደስ” እንዳለው ዓይነት ይሆን አቶ ሙሉጌታ በቅርብ ጊዜ አንድ መጣጥፉ?... እንዲያ ከሆነ ደሞ የምጸት ሳቅ አብረን እንሳቃ! ቅቅቅ....
ሙሉጌታ ሉሌ ” ... ተናጋሪው ቁጥር 53 እንግዲህ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒሰትር የነበሩት ዶክተር ኮሎኔል ፈለቀ ገድለ ጊዮርጊስ መሆናቸው ነው፡፡ ዶክተር ፈለቀ ደግሞ ከወያኔዎች እሥራት እግዜር ያተረፋቸውና በምንም ሁኔታ ለወይዘሮ ገነትም ሆነ ለሜጋ መግለጫ ያልሰጡና የማይሰጡ ሰው መሆናቸውን አውቃለሁ...” (ጦቢያ 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 12፣ ገጽ 12፣ 1994 ዓ.ም.) ይላል ምጸና ብጤ የታከከበት የቃለ መጠይቁ ምላሽ፡፡ እናም አቶ ሙሉጌታን ቅቅቅቅ!.... ብለን እየተንከተከትን ”እርግጠኛ ነህ? እርግጠኛስ ባትሆን?...” እያልን መጠየቅ ግድ ይለናል፡፡ ሰወዬው እኮ አሁንም በሕይወት አሉ፡፡ እውነትንና ሀቅን ለዚሀ በስባሽ ሥጋቸውና ብዙ ላየች ሕይወታቸው ስስት የሚደብቁ ይመስልሃል? ይቺን ሁላችሁም እየተረማመዳችኋት ለማምለጥ የሞከራችኋትን የበዓሉ ግርማን መጨረሻ ጉዳይ፤ ጓድ ቁጥር 53 ከቁጥር ስም ጥሪ ተርታ ወጥተው እውነቱን ለሕዝባቸው ባደባባይ ሊገልጹ የሚችሉበት ቀን እሩቅ አይመስለኝም፡፡ እደጅ እደጁን እየሸተተን ያለ ጉዳይ አለና እስቲ አብረን እንጠብቅ!!!!!!
በዓሉ ግርማ፣ ባለቤቱ ወ/ሮ አልማዝና ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በ1963 ዓ.ም.
ለማንኛውም ገነት ላይ ከተሰነዘረው ክብረ ነክ ዘለፋ አንዱን ለናሙናነት እዚህ ላይ ልጥቀስ፡፡ ”በወይዘሮ ገነት በኩል ሐራሬ ድረስ በመሄድ ኮሎኔል መንግሥቱን ማነጋገር በአንድ በኩል ጀብዱ (አድቬንቸር) ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ታዋቂነትን ማግኘትና የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ከሞራል ሕግና ከሕሊና ዳኝነት ውጭ ተሠራ አልተሠራ ትርጉም የሚሰጣቸው አይመስለኝም...” (ጦቢያ 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 12፣ ገጽ 11፣ 1994 ዓ.ም.) ዓይነት ትችትን ምን አመጣው? አንድ አንባቢ አንድን የሥነ ጽሑፍ ሥራ መተቸትም መገምገምም ያለበት ከይዘትና ከቅርጹ አኳያ አይቶና መዝኖ ፋይዳውንና ዋጋውን እንጂ፤ ’ገንዘብ አገኘበት፣ ታወቀበት፣ ወዘተ...’ ዓይነት የምቀኝነት ክፉ መንፈስን ተጀቧቡኖ በግብዝነት መኮነንን አይደለም፡፡
የማስታወቂያና መርሃ ብሄር ሚኒስቴርን ካነሳን ዘንዳ ወደ ኋላ ዘመን ተመልሰን የጓዳ ምስጢር ሰነድ መፈተታሽ የግድ ሊለን ነው... አሁን፡፡ በዚህ አጋጣሚም በዓሉና የቤቱ ጋንግስተሮች የነበራቸውን ግንኙነት እንደቤቱ ሰውና የውስጥ አዋቂ ትንሽ የምንለው ይኖረናል ማለት ነው፡፡ በዓሉ ግርማ ከጀማሪ ጋዜጠኝነት እስከ ቋሚ ተጠሪነት የኃላፊነት እርከን የዘለቀው፣ አልጋ ባልጋ በሆነ መንገድ አልነበረም፡፡ ከግራና ቀኙ ጋር እየተላተመ፣ እየተቧጨቀ፣ እየተቆራቆዘ ወዘተ... ነው የኖረው፡፡ ይህንን የጓድ ቁጥር ሀምሳ ሦስትን ምስክርነትና ጥቆማ ሳንዘነጋ፤ በዓሉ ግርማ እንደሙሉጌታ ሉሌ ከመሳሰሉ የሥራ ባልደረቦቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት ስንፈትሽ፤ ውስጣችንን የሚያጠያይቁ ብዙ ሰበዞችን መምዘዝ እንችላለን፡፡ በዓሉ ግርማና ሙሉጌታ ሉሌ ባለቃና ምንዝርነት በማስታወቂያና መርሃ ብሄር ሚኒስቴር ውስጥ አብረው ሲሠሩ ኑረዋል፡፡ ሙሉጌታ ሉሌ፤ በዓሉን በእጅግ የሚጠላውና ከእሱ በፊት የበዓሉን ወንበር ሲቋምጥ የኖረው የሻቢያው ሰው የገዳሙ አብርሃ ጀሌ ነው፡፡
ገዳሙ አብርሃ በአጎብዳጆቹና በቅምጦቹ ሽፋን በማስታወቂያ ሚኒስቴር ወስጥ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ መምሪያዎችን እያማረጠ በመሾም፤ ኤርትራን ከእናት አገርዋ ከኢትዮጵያ ለማስገንጠል በሚዲያው ውስጥ ተቀምጦ ወደር የሌለው ስውር ሚና ለነኢሳይያስ አፈወርቂ የተጫወተ ሰው ነበር፡፡ የኋላ ኋላም የሬዲዮ መምሪያ ኃላፊነቱን ለጡት ልጁ ለሙሉጌታ ሉሌ አዋርሶ የሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሆኖ ይሥራ የነበረና፤ በመጨረሻም ኢትዮጵያን በይፋ ክዶ ተገንጣዩን ሻቢያን አሜሪካ ሄዶ የተቀላቀለ ሰው ነው፡፡ ገዳሙ አብርሃ የነሙሉጌታ ሉሌ ጡት አባት ሆኖ፣ ”ኢትዮጵያ ወይ ሞት!” ብለው የቆሙ የመሃል አገርና የሰሜን ተወላጆችን ሲያሰቃይ የኖረ ጨካኝ ሰው ነበር፡፡ በጥቅማ ጥቅምና በክፍል ሹመት ጋዜጠኛውን እየከፋፈለና እየደለለ ብዙ ዓመታትን ዘልቋል፡፡ ይህን ጸረ ኢትዮጵያ ድርጊት በፈጸመ ቁጥር፣ ይህን ሰው አንድ በሉልን እያሉ የወተወቱና የታገሉ አገር ወዳዶች ሁሉ ከጥቃት አላመለጡም፡፡ በደህንነት መሥሪ ቤት ባልደረቦቹ በነሙሉጌታ ሉሌ መሣሪያነት ከሥራ መባረር፣ እስር፣ ስደትንና እንግልትን በያይነቱ አስተናግደዋል፡፡ ለዋቤነትም እነላእከ ማርያም ደምሴ፣ ጸጋዬ እንደሻው፣ ሞገስ ደምሴ (ዛሬ በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ነዋሪ)፣ የማነ ቸርነት (Green Face)፣ ተፈራ አሥማረና የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ባንድ ወቅት የደረሰባቸውን ግፍ እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በገዳሙ አብርሃ ጸረ አንድነት አቋም ምክንያት የኃይል እርምጃ እንዲወሰድባቸው ትእዛዝ የተላለፈባቸው ጋዜጠኞች እነዚህ ነበሩ፡፡ ተግራ ወደ ቀኝ... ጸጋዬ እንደሻው፣ ተፈራ አሥማረ፣ ላእከ ማርያም ደምሴ፣ ሞገስ ደምሴ፣ አበራ ለማና የማነ ቸርነት
ገዳሙ አብርሃና ጀሌዎቹ ከላይ የተቀሱትን ስድስት ጋዜጠኞች ጉርድ ፎቶግራፍ ከግል ማህደራቸው ውስጥ በማውጣት የሠሩት ደባ ምን ጊዜም ሲታወስ ይኖራል፡፡ ጸረ አንድነቱ ገዳሙ አብርሃ ፎቶግራፎቹን ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ግቢ መግቢያ በር ላይ በማስለጠፍ፤ ”እነዚህ ጸረ አብዮተኞች ስለሆኑ ወደ ግቢው ሲገቡ ብታገኟቸው የኃይል እርምጃ እንድትወስዱባቸው!” ብሎ ለጥበቃ ወታደሮች ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡ ትእዛዝ ፈጻሚው ወታደራዊ የጥበቃ ክፍልም አንዳቸውም ወደ ሥራ ገበታቸው እንዳይገቡ ሲከላከል ለወራት መዝለቁና ይህ ኢፍትሃዊ ድርጊት ትልቅ ወዝግብ ማስነሳቱ ትዝ ይለናል፡፡ በቋሚ ተጠሪነት ሚኒስቴር መሥሪ ቤቱን በሁለተኛ ሰውነት ይመራ የነበረው በዓሉ ግርማ፣ ከስሩ ያሉ ትንንሽ ሰዎች ይህን መሰሉን ጸረ ሕዝብ ተግባር ሲፈጽሙ፣ ”እረፉ!...” የሚልበት አቅሙን ተሰልቦ ከተጠቂዎቹ ጋር እያዘነ ይኖር የነበረ ሰው ነው፡፡
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ባቶ አሰፋ ይርጉ ይመራ በነበረ የብሔራዊ መሠረተ ትምህርት ዘመቻ ገምጋሚ ቡድን ውስጥ ተካቶ ላንድ ወር ያህል በኤርትራ ልዩ ልዩ አውራጃዎች ለሥራ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ወደ መሥሪያ ቤቱ ሲመለስ ነበር ... ይህን የነገዳሙን ጸረ ሕዝብ ተግባር ያጤነው፡፡ ገዳሙ አብርሃ፣ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢና የጎበዞቹን አገር ወዳድ የሥራ ባልደረቦቹን ፎቶግራፍ በማስለጠፍ፣ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ግቢ እንዳይገቡ ያከናወነውን ሕገ ወጥ ተግባር ባቤቱታ የተመለከቱት የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሻለቃ ግርማ ይልማ በሰጡት አስቸኳይ ትእዛዝ፣ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የተለጠፈው ፎቶግራፉ ተነስቶና ያላግባብ የተጣለበት እግድ ተነስቶለት ወደ ሥራ ገበታው መመለሱን ያስታውሳል፡፡ ውሎ አድሮም የቀሩትም ይህ ግፍ የተፈጸመባቸው ጋዜጠኞች ወደ እናት መሥሪያ ቤታቸው ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ በነጻነት ገብቶ ለመውጣት ችለዋል፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ከነዚህ ስድስት ጋዜጠኞች መካከል ገሚሶቹ በሰሜኑ የጦርነት አውድማ ለወራት ግዳጃቸውን ሲፈጽሙ ቆይተው፤ ባኩሪ ሙያዊ ተልእኳቸው በጦሩና በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮትን ማትረፍ የቻሉ ነበሩ፡፡ ወደ መሥሪያ ቤታቸውም ሲመለሱ ከየጦር ክፍሉ የተጻፈላቸውን ከፍተኛ የምስጋና ደብዳቤ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር አቅርበው፣ በዓሉ ግርማን ከመሰለ ያለቆቻቸው አለቃ ምስጋናና ሞገስን አግኝተውበታል፡፡
ታዲያ ያንን የምስጋና ደብዳቤ ይዘው የመጡት ዘማች ጋዜጠኞች በሙሉ እጣ ፈንታቸው እገዳሙ አብርሃ ጥርስ ውስጥ መግባት ነበር፡፡ ”የኤርትራን ሕዝብ ስትጨርሱና ስታስጨርሱ ከርማችሁ ለመጣችሁበት አገልግሎታችሁ ዋጋችሁን እጥፍ አድርጌ እከፍላችኋለሁ፡፡” እያለ እቢሮው አንድ ባንድ እየጠራ ሲደነፋ የቆየበትን እብሪቱን ሳይውል ሳይድር በተግባር ላይ አውሎታል፡፡ በጦር ግምባር ላይ በየበረሃው ተንከራተው አጠናቅረው ያመጡትን ዘገባ በሙሉ እንዳይተላለፉ አግዶና አፍኖ አስቀርቶታል፡፡ በዚህ የገዳሙ አብርሃ ግፍና ጸረ ሕዝብ ድርጊቱ እጅግ የተከፋው የሬዲዮ መምሪያ የፕሮግራም ኃላፊ የነበረው ምስጉኑ ጋዜጠኛ የወንድወሰን ዓለሙ ከፍተኛ ጸብ ውስጥ ገብቶ፤ ጸረ አንድነቱ ገዳሙ አብርሃ ከዚያ እንዲባረር አድርጎታል፡፡ ቀጥሎም እነዚህ ስድስት ትጉሃን ጋዜጠኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዳይገቡ ከማገዱም በላይ፤ እንዳገር ወዳዱ ጸጋዬ እንደሻው የመሰለ አንጋፋ ጋዜጠኛ መጠለያና መተዳደሪያ አጥቶ እበረንዳ ላይ እንዲወድቅ ጭቡ ተሰርቶበታል፡፡ ”ለምን ኤርትራ ሄደህ የጦሩን መዋእለ ዜና ገዘጥክ?...” በሚል የጸረ አንድነቱ የገዳሙ አብርሃ እብሪት ብቻ፤ ለረዥም ዘመን ካገለገለበት መሥሪያ ቤት ያላንዳች ጥፋቱ ልክ እንደ ጓደኞቹ እንደነ ላእከ ማርያም ደምሴ፣ ሞገስ ደምሴ፣ ተፈራ አስማረ፣ የማነ ቸርነትና ሌሎቹም ሁሉ ከሥራ ሊባረር ችሏል፡፡
ጋዜጠኛ ጸጋዬ እንደሻው አፈሩን ያቅልልለትና፤ በሰሜን ጦር ግምባር ለስድስት ወራት ያህል በረሃ ለበረሃ እየተንከራተተ ሲገዝጥ የቆየ ሲሆን፤ በፈንጂ ፍንጣሪም የመቁሰል አደጋ ደርሶበት ነበረ፡፡ ”ያህያ ውሽማ ከጅብ አያስጥልም” እንዲሉ አያ ደርጉ የሞቱለትን ረስቶ የገደሉትንና የሚገሉትን ይንከባከብ ስለነበረ፤ ገዳሙ አብርሃ ይሄንን ሁሉ ጸረ ሕዝብ ተግባር ዓይኑ ስር ተቀምጦ ሲያከናውን ተው ያለው አልነበረም፡፡ ከዚህ ሁሉ የገዳሙ አብርሃ ያስገንጣይ ገንጣይ ተልእኮ ጀርባ ለተካሄደው ደባ ሁሉ የነሙሉጌታ ሉሌ ዓይነት ሰው ድጋፍና ሴራ ከበስተጀርባው እንደበረ ሁሌም ባሰብነው ቁጥር ሲዘገንነን ይኖራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተቃራኒው፤ በዓሉ ግርማ እኛን የበታች ሠራተኞችና ጋዜጠኞችን ያበረታታን ይደግፈንም ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በ1970 ዓ.ም. ወደ ሰሜን ጦር ግምባር ባጋዜጠኝነት ሲዘምት፤ እቢሮው ጠርቶ የሥራ መመሪያ ሰጥቶና አበረታቶ የሸኘው ቋሚ ተጠሪው ጓድ በዓሉ ነበር፡፡ ከዘመቻ መልስም ለተከናወነው ጋዜጠኛዊ ሥራ ምስጋናውንና ይሁንታውን ያለስስት የገለጸለት እሱ ነበር፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ቅጣት፣ እንግልትና ወደ ሌላ መምሪያ እንዲዛወር ብሎም ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ለቆ እንዲወጣ ጨካኝ እርምጃ የተወሰደበት ደግሞ በጸረ አንድነቱ በገዳሙ አብርሃና በጋሻ ጃግሬዎቹ ነበር፡፡
በዓሉ ግርማ በትምህርታችን እንድንገፋ፣ ባጋዜጠኝነት ሙያችን እንድንሻሻል እኛን ከማትጋት ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ባዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የነበረኝን ጅምር ትምህርት እዳር አደርስ ዘንድ ጽፎልኝ የነበረውን የድጋፍ ደብዳቤ፤ እዚህ ላይ ላብነት ያህል መመልከት ይቻላል፡፡
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስታውሰው ሁሉ፤ ጸጋዬ እንደሻውና ተፈራ አሥማረ ምንጊዜም በአብዮት አደባባይ ይካሄዱ የነበሩትን ሕዝባዊ ታላላቅ ስብሰባዎች ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጊዜያዊ እስቱዲዮ ሆነው ፕሮግራሙን ይመሩ የነበሩ የሚዲያ ጀግኖች ነበሩ፡፡ ይህን ሥራ በብቃትና በጥራት ሊወጡት ይችላሉ በሚል እምነት ከሌሎች መሃል መርጦ እዚያ ይመድባቸው የነበረው የበላይ አለቃችን በዓሉ ግርማ ነበር፡፡ እኒህ ሁለት ትጉሃንና ላገራቸው ብሔራዊ ጉዳይ እጅግ ቀናኢ የነበሩ ጋዜጠኞች በእርግጥም ጓድ በዓሉን ያሳፈሩ አልነበሩም፡፡ ጥሩ መቀራረብና መናበብ በመሃላቸው ሰፍኖ ቆይቷል፡፡ ከጓድ በዓሉ ይሁኝታና ሞገስ ማግኘታቸውም በነገዳሙና ጭፍሮቹ ጥርስ ውስጥ አስገብቷቸው ኖረዋል፡፡

በነገራችን ላይ ጸጋዬ እንደሻው ከወደቀበት ከተረሳበት ስርቻ ተፈልጎ በ1980 ዓ.ም፣ ባንድ የጋዜጠኞች ቡድን ውስጥ ተካቶ ኤርትራ ወስጥ በዳግም ዘማችነት እንዲያገለግል ከተገደዱት በደል የደረሰባቸው ጋዜጠኞች አንዱ ነበር፡፡ እንደጸጋዬና እንደኔ ያለነውን ያበረሩንን ሰዎች ሕይወትን ለሚያስገብር ዳግም ዘመቻ ከያለንበት ፈልገው ሲያዘምቱን፤ ባለፈው ላደረሱብን በደል የጠየቁት አንዳችም ይቅርታና ያሳዩት ጸጸት አልነበረም፡፡ ጸጋዬ ባሌ አጋርፋ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ጣቢያ ውስጥ ለነፍሳቸው ያሉ አገር ወዳዶች አስጠግተውት በተራ ሠራተኛነት ተሸሽጎ ይኖር ነበር፡፡
እኔ የዚህ ጽሑፍ ባለቤት ደግሞ ለዚህ ለ1980 ዳግም ዘመቻ ተፈልጌ ታጠቅ ጦር ሠፈር ስላክ፣ በሕዝብ ማመላለሻ ኮረፖሬሽን በሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ሃላፊነት እየሠራሁ ነበር፡፡ ቀደም ሲል በቅንነትና በሃቅ ላገር መዝመትን የወደድነውን ያህል፤ በሁለተኛው ዙር ዘመቻ ጊዜ ግን፣ ከበስተጀርባው ምቀኝነት፣ ተንኮልና ደባ ስለነበረበት ደስተኞች አልነበርንም፡፡
ደርግም ሆነ የማስታወቂያ ሚኒስቴሮቹ ሹማምንት እንደ ሙሉጌታ ሉሌ ያለው ምቀኛ ”እኛ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንቶች ከእጅ ወዳፍ ደመወዝ ሲከፈለን፣ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ግን ወፍራም ደሞዝ እያገኙ ነው” እያለ ባዲስ ዘመንና በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ይዘምትብን የነበረውን ሁሉ አንረሳውም፡፡ እናም በበዓሉ ግርማ ወንበር ላይ ዓይኑን ቢጥል ምን ይበዛበታል?... ምንስ ይደንቃል?...በዓሉ በተለይ የቋሚ ተጠሪነትን ሹመት ካገኘ ከ1970 ዓ.ም. በኋላ ገዳሙ አብርሃና ቡችሎቹ የምቀኝነትና የተበለጥን ባይነት አዶከብሬያቸው ተነስቶባቸው ብዙ ተፈታትነውታል፡፡ በገዳሙ የሚመራ ያረቄ ማህበርተኞች ስብስብም ተቋቁሞ አላላውስ ሲሉት፤ በብእሩ ሊበቀላቸው ተነሳ፡፡ ከነዚያ ተቀናቃኞቹ መካከል ገዳሙ አብርሃ፣ ፀሐዬ ደባልቀው፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ሞገስ ታፈሰ፣ ጎሹ ሞገስ፣ ወሌ ጉርሙ፣ ተፈራ ግዛው፣ ማሞ ውድነህ፣ አሰገደች ይበርታ፣ እምሩ ወርቁና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡
አብዛኞቹ ያንድ መንደር ልጆችና በጎጠኝነት በሽታ የተለከፉ ዓይነት ትንንሽ አሳቢዎቸ ነበሩ፡፡ እናም በእኩይ ድርጊታቸው፣ እሱን ጠምደው በመያዛቸውና አላፈናፍነው በማለታቸው እነዚህንና መሰል ቡችሎቻቸውን ጥግ ለማስያዝ፤ ”የቀይ ኮከብ ጥሪ” የተሰኘውን ሥራውን ላይነ ንባብ አብቅቶ፤ ”እነሆ በረከት!...” አላቸው፡፡ ”የኤምባሲዎች ኮክቴል ግብዣ ካለ በቀር ’ሆራችን’ የሚሉትን የእሜቴን ቡና ቤት ባንኮኒ ሳይሳለሙ ቤት አይገቡም፡፡ ቤቱን መርቀው የከፈቱት የአራት ኪሎ ጋዜጠኞችና የፓርላማ እንደራሴዎች ነበሩ ይባላል፡፡ ከቆርቋሮዎቹ አንዱ ጌታቸው ነበር... ከጥይት ቤት አካባቢ የሽጉጥና የዲሞትፈር ተኩስ አይሎ መሰማት እንደጀመረ፤ ሀብቴ ይርጉ፣ ጉደታ ፈይሳ፣ ታቦር ይመርና ኢዮብ ገብረ ማርያም ተንጋግተው ገቡ፡፡ የአራት ኪሎና የአቡነ ጴጥሮስ አንጋፋ ጋዜጠኞች ነበሩ...” (የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ 1972፣ ገጽ 179 እና 185)
በዓሉ ግርማ በ1972 ዓ.ም. ባሳተመው በዚህ ”የቀይ ኮከብ ጥሪ” ታሪካዊ ልቦለድ መጽሐፉ ላይ፤ ከዋናው ሚኒስትር ጀምሮ እስከ ተራ ሪፖርተሮች ያሉትን የማስታወቂያና መርሃ ብሄር ሚኒስቴር ሠራተኞችን በገጸ ባሕሪነት እየተጠቀመባቸው ደህና አድርጎ ተሳልቆባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹንማ የታሪኩ ዋና እምብርት ጉዳይ ተዋናይ ከማድረጉም በላይ፣ ገጻቸውንና ግብራቸውን እያሰናሰለ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አጭበርባሪ ጎብላንዶች ድብቅ ገመና ፀሐይ አስመትቶታል፡፡ ከነዚህ በገጸ ባሕሪነት ከተሳለቀባቸው ግለሰቦች መካከል ገዳሙ አብርሃ በ”ጌታቸው የሸዋልዑል” አምሳል ተስሎ ቀርቧል፡፡ የገዳሙን ተክለ ሰውነት፣ ባሕሪና መሰሪ ሰብእና በትረካው ውስጥ ደጋግሞ በማንሳት እርቃኑን አስቀርቶታል፡፡ እንዲህ እያለም በቅርብ የምናውቀውን ትክክለኛውን ገዳሙን በትክክለኛው እሱነቱ ያቀርብልናል፡፡ ”ጌታቸው የሸዋልዑል፣ የአጥንቱ መገጣጠሚያዎች እየተጋጩ እንዳያሳምሙት ወይም ዘይት አጥቶ እንደደረቀ መዝጊያ

ሲጥ ሲጥ እያሉ እንዳያሳጡት የሚጠነቀቅ ይመስል እርምጃዎቹን እየቆጠረና እየተንሳፈፈ የለሊት ልብሱን ለብሶ ብቅ ባለበት ጊዜ...” (የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ 1972፣ ገጽ 97) እያለ በገሃዱ ዓለም የምናውቀውን የገዳሙ አብርሃን ተክለ ሰውነት በሥዕላዊ ገለጻ እንደመስታወት መልሶ ያሳናል፡፡ ገዳሙን አብረነው ኑረን የምናውቀው ሁሉ፣ ሲራመድ አየር ላይ የሚንሳፈፍ እፉዬ ገላ የሚመስለውን አኳኋኑን በዓሉ ግርማ ደህና አድርጎ ስሎታል በሚለው እንስማማለን፡፡ ለአሳሳሉ ትክክለኛነትም ይሁንታችንን እንሰጠዋለን፡፡ ገዳሙ ባጥንቱ ብቻ የቀረና እንደልብስ ማስተዋወቂያ ላንቲካ በለበሰው ተሸትሮ፤ እንደሮቦት በቀስታ የሚንቀሳቀስ ሰው ነበር፡፡ ሲራመድ ኮሽታ፣ ሲናገር ድምጽ የሌለው የክፉ መንፈስ ጣእረ ሞት ነበር... የሚመስለው፡፡
ደራሲ በዓሉ ግርማ የገዳሙን ውስጣዊ ባሕሪ ሲገልጽም፤ ”...በስልጣኑ ቀናተኛ ነበር፡፡ በምንም መንገድ ስልጣኑ ሲነካበት አይወድም፡፤ይበሳጫል፣ ይቀጣል፣ ያኮርፋል፣ እና ይጠጣል... ስልጣኑ ሲነካ እንደነብር ተቆጥቶ ራሱን እስከመጉዳት የሚደርሰው፣ መንማናና ደካማ በመሆኑ በስልጣን ጡንቻ ተጠቅሞ አካላዊ ጉድለቱን ለማካካስ ስልጣንን የእልሁ መወጫና የቂም በቀል መቅረፊያ መሳሪያ ለማድረግ ነው...” (የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ 1972፣ ገጽ 102-103) እያለ ደህና አድርጎ ውስጣዊ መሰሪ ሰብእናውንና ተፈጠሮውን ይገልጸዋል፡፡ የገዳሙን ባሕሪና ውስጠ ተፈጥሮውን ጠጋ ብሎ የሚያውቅ ሁሉ በዚህ የበዓሉ ገለጻ ይስማማል፡፡ በሌላ ገጽ ላይ ደግሞ፤ ገዳሙ ማኪያቬላዊ ፍልስፍናን እንደሚያራምድ ክፉ ሰው ሁሉ፤ ለቅርብ ወዳጆቹ ጭምር የማይመለስ መሰሪ መሆኑን እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ”...ቂመኛ መሆኑን ታውቃለች... (ሚስቱን ማለቱ ነው) ስለሆነም፣ ከመወደድ ይልቅ መከበርንና መፈራትን ስለሚመርጥ፣ከጠላቶቹ ይበልጥ ወዳጆቹንም የመጉዳት ዝንባሌ ነበረው፤ ቁንጣጫው የደረሳቸው ወዳጆቹ ሁሉ፤ ”ከጌታቸው የተጠጋ ወዳጅ፣ ከአጋም እንደተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል...” (የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ 1972፣ ገጽ 104) ሲል ውስጠ እኔነቱን ሰርስሮ ለማያውቁት ሁሉ ያሳያል፡፡ ገዳሙ፤ እራሱን በዓሉን ሊበቀለው ያለው ምኞትና ጉጉት ምን ያህል ኃያል እንደነበረም የገለጸበት ስፍራ አለ፡፡
”የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለሁለት ተሰንጥቆ ሲያበቃ ይደረመሳል - የማተሚያ መኪናዎች ይፈነዳሉ - ንፋስ የወሰዳቸው ወረቀቶች ሰማዩን ይሞሉታል -ጋዜጠኞች ከሰባተኛ ፎቅ ተወርውረው ይፈጠፈጣሉ - አንጎላቸው ከአስፋልቱ ላይ እንደንፍጥ ይለጠፋል፡፡ የባንያን እሬሳ ሲቃጠል፣ ሲጋይ፣ ጭንቅላቱ ዓይኑ ሲፈነዳ - ፍጻሜ! ወሬ የለም፡፡ የዓለም ፍጻሜ! የስልጣኔ ፍጻሜ!...” (የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ 1972፣ ገጽ 242) ሲል ለእሱ ለራሱ የሚመኝለትን ክፉ ዓይነት አሟሟት አሳምሮ ገልጾታል፡፡ በዓሉን እያመላከተ ለመሆኑም ”የባንያን እሬሳ ሲቃጠል....” የሚለውን ገለጻ ልብ ይሏል፡፡ ይህም የበዓሉን ባለሕንዳዊ ደምነት ለይቶ ለማሳት የተጠቀመበት ስልት ነው፡፡ በዚህ ገለጻ ላይ ምን ያህል ገዳሙ አጥብቆ በዓሉን እንደሚጠላው በራሱ በበዓሉ ብእር መገለጹን እናስተውላለን፡፡
እንባ እንባ ይለኛል
ይተናነቀኛል...
እንባ የትአባቱ
ደርቋል ከረጢቱ፤
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እየነደደች
መከረኛ ነፍሴ
ገዳሙ፣ ሚኒስትሩን ሻለቃ ግርማ ይልማን የሚያይበት መነጽሩም ምን እንደሆነ ከዚህ የበዓሉ ግርማ ገለጻ ላይ መረዳት እንችላለን፡፡ ገዳሙና ባለቤቱ ትእግስት ከሚያካሄዱት የጋራ ምልልስ ላይ የተወሰደ ነው፡፡ ”እንደ ፍየል ጭራ ገበና ከማይደብቁ አለቆችም ጋር መሥራት አልችልም! በጥፋታቸው የቀጣኋቸው ሰራተኞች በየውይይት ክበቡ አድሃሪ ቢሮክራት እያሉ ሲጨፍሩብኝ ዞር ብሎ ከእነርሱ ጋር ከሚያቶከቱክ አለቃ ጋር መሥራት አልፈልግም፡፡ በሬ ካራጁ ጋር ይውላል ይባላል፡፡ ከፍየል ጭራ ጋር... ጭራውን ከሚቆላ አለቃ ጋር ለመስራት አልፈልግም፡፡ ገባሽ ቲጊ?...” (የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ 1972፣ ገጽ 104) እያለ በቅርብ አለቃው በሚኒስትሩ ላይ ሲማረር ያሳየዋል፡፡
አዎን... በዓሉ ግርማ ቢያንስ ቢያንስ ”የቀይ ኮከብ ጥሪ” እና ”ደራሲው” በተሰኙት ሁለት የድህረ አብዮት መጻሕፍቱ የቅርብ ጠላቶቹን ሊከላከል ብሎም ሊበቀል ሞክሯል፡፡ ”ካድርባይ ብእር ባዶ ወረቀት ይሻላል” እያለ፡፡ እነሙሉጌታ ሉሌ ”ሀብታሙን መስፍን ላነጋግር ሄጄ ድሃውን መስፍን አገኘሁት” (የ1966 ዓ.ም. የመጨረሻ ወራት አዲስ ዘመን ጋዜጣን እትም ልብ ይሏል) እያሉ ስለ ራስ መስፍን ስለሺ የ80 ጋሻ መሬት ባለቤትነት አሳንሰው እየጻፉ፣ ድሃ መሆናቸውን እየነገሩን፤ እያስገመገመ ከመጣው አብዮት መዳፍ እንዲያመልጡ ይጽፏችው የነበሩ የምልጃ ጽሁፎችን እስከዛሬ ድረስ ባግራሞት እናስታውሳቸዋለን፡፡ በወቅቱ ያ የሙሉጌታ ሉሌ ያድርባይነት ጽሑፍ በተራማጅ ምሁራን፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን፣ በዓሉ ግርማን በመሳሰሉ ተራማጅ ጋዜጠኞች፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዘንድ ያስነሳውን የቁጣ አቧራ እስካሁን ድረስ እናስታውሰዋለን፡፡ በዓሉም ይህንን መሰሉን የቅርብ ትዝብቱንና ቅኝቱን በነዚህ በተጠቀሱት ዓይነት መጻሕፍቱ ላይ ባለፈ ባገደመ ቁጥር ስለሚያነሳሳ፣ እነሙሉጌታ ጥርስ ውስጥ ገብቶ ለመኖር ሰበብ ሆኖታል፡፡
ገዳሙ አብርሃና ጭራዎቹ በዓሉ ግርማን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እያጠቁ፤ ያንን የቋሚ ተጠሪነት ወንበር ለመንጠቅ ሲጥሩ እንቅልፍ አልነበራቸውም፡፡ በተለይ ገዳሙ አብርሃ የሱን ወንበር መያዙ በብርቱ ያስፈልገው ነበር፡፡ ምክንያቱም የነሻቢያንና የነጀብሃን የቤት ሥራ እንደልቡ ለማከናወን የሚችለው በእንዲህ ዓይነቱ ሰቀላ ወንበር ላይ መሰየም ሲችል ብቻ ነበርና ነው፡፡ በዓሉ ግን ወደር በሌለው እርጋታው፣ ቻይነቱና የሕዝብ ፍቅር የነዚህን የእምዬ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ደባና ሸር እየተከላከለ ደህና ተጉዞ ነበር፡፡ ግና የኋላ ኋላ ኦሮማይን ሲጽፍ ተመቻችቶ እቀለበታቸው ውስጥ ወደቀ፡፡ እናም በዚያን ጊዜ በጋዜጠኝነት ሽፋን በደህንነት ሚኒስቴር ባልደረብነት (ከሁለቱም መሥሪ ቤት ደሞዝ እየተከፈለው) በማስታወቂያ ሚኒስቴር ወስጥ ይሠራ የነበረው ሙሉጌታ ሉሌ፤ በዓሉ ግርማን ሰለባ አስደርጓል እያሉ የደርጎቹ ሹማምንት ስለሰጡት ጥቆማ እስከዛሬ ድረስ የሚያሳምን ማስተባበያ አልሰጠም፡፡ እናም የደርጉን ሹማምንት
እንመን ወይስ ያቶ ሙሉጌታን ዝምታ በይሁንታነት እንቀበል? ወይስ የዚያ የገናና ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ መቅረት ምሥጢሩ፤ እጅግ በሳይንስና በቴክኖሎጂ በሰለጠነው በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መፍትሄ ያልተገኘለት እንቆቅልሽ ተብሎ ታስቦ ሊቀር ነው?
የእኒህን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ጉዶች አሮጌ ፋይል ከማጠፌ በፊት አንድ በግሌ የማውቀውን በውስጤ የሚጉላላውን ጉዳይ ላንባቢያን ላካፍል፡፡ ሕሊናዬ አውጣው እያለ ሁሌም ያስጨንቀኝ ነበርና ዛሬ ልገላገለው፡፡ ምናልባት አንባቢያን ”ፊያሜታ እምባባ” የተባለችውን የኦሮማይ ድርሰት መታሰቢያ ግጥሜን ፈተና ጉዳይ እተርክ ዘንድ ጠብቀው ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ስለሷ ብዙ ጊዜ ያወሳሁ በመሆኔ ከዛሬ ዋና ጭብጤ ጋር አዛንቄ አልወሰድኳትም፡፡

ይህ ጥቂት ልልበት የፈለኩት ጉዳይ በቀጥታ ከላይ ከጠቀስኳቸው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ጉዶች ፀረ በዓሉ ግርማ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘና እራሴ ምስክር የሆነኩበትን ጉዳይ ነው፡፡ የበዓሉ ግርማ የቀይ ኮከብ ጥሪ በ1972 ዓ.ም. ታትሞ ላይነ ንባብ በበቃበት ዘመን፤ እኔ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ በገዳሙና በጭፍሮቹ ተባርሬ በፕሬስ መምሪያ የአዲስ ዘመን ”የባሕል መድረክ” ገጽ አዘጋጅ ሁኜ እሠራ ነበር፡፡ ተዛውሬ ወደ ፕሬስ ስሄድ የነበረው የመምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለ ማርያም ጎሹ ነበር፡፡ ድንቅ ሰው፣ የተዋጣለት ጋዜጠኛና ምሁር ነበር፡፡ ጥቂት ወራት ደስ ብሎኝ በእሱ ስር እንደሠራሁ፤ እሱ ወደ ቴሌቪዥን መምሪያ ተዛውሮ ከዚያ ሲለቅ፤ ጎሹ ሞገስ የሚባል የጎጠኞቹና የፀረ በዓሉ ቡድኑ ተላላኪ ተጠባባቂ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ ሁኖ መጣ፡፡ ከተራ የሳንሱር ሠራተኝነት ብዙ ደረጃዎችን ባንዴ ተረማምዶ እላያችን ላይ ጉብ ያለ የዘመድ ሰው ነበር፡፡ የኮሎኔል መንግሥቱ አጎት ያቶ አሥራት ወልዴ አሚን ሚስት ወንድም በመሆኑ በዘመድ የተሰጠው ወንበር ነበር፡፡
ታዲያ ይሄ አዲስ ደራሽ ኃላፊ አንድ ቀን ወደ ቢሮው አስጠራኝና ማስጠንቀቂያ ሰጠኝ፡፡ ”የዚህን በዓሉ ግርማ የሚሉትን አድሃሪ መጽሐፍ ባብዮቱ ልሳን (አዲስ ዘመንን ማለቱ ነው) ላይ ማስተዋወቅህን ከዛሬ ጀምሮ እንድታቆም!... በሳምንት እቅድ ላይ የያዘከውም እሱን የሚመለከት ጽሑፍ እንዳይወጣ አግጃለሁ” አለኝ፡፡ የሰማሁትን ማመን ነበርና ያቃተኝ በደነገጠ መንፈስ ውስጥ ሁኜ፤ ”አልገባኝም... በዓሉ ነው አድሃሪ?... እንዴት?... እንዴት ሊሆን ይችላል?... በዓሉ ግርማ አድሃሪ አይደለም!...” እያልኩ ሳግ እየተናነቀኝ ልጠይቅና ልከራከር ተፍጨረጨርኩ ግን ብዙም አልተራመድኩም፡፡ ”በዓሉንና ሥራዎቹን የሚመለከት አንድም ጸሑፍ ከዛሬ ጀምሮ እንዳታወጣ ወስኛለሁ!... አስጠንቅቄሃለሁ!...” ብሎ ከቢሮው አባረረኝ፡፡
ያንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር በአቶ ፈቃደ አዘዘ (በኋላ ዶክተር) የተጻፈና በቀይ ኮከብ ጥሪ መጽሐፍ ግምገማ ላይ ያጠነጠነ፣ እንዳይታተም በጎሹ ሞገስ የተከለከልኩትን ጽሁፍ ይዤ፤ ወደ ቅርብ አለቃዬ ወዳቶ መርእድ በቀለ ዘንድ አዘገመኩ፡፡ ጎሹ ሞገስ፣ በዓሉ ግርማን በአድሃሪነት ፈርጆ እንዳይታተም የከለከለው ጽሑፍ እንደሆነ አስረድቼ ሰጠሁት፡፡ አቶ መርእድ ጽሑፉን በጽሞና ካነበበ በኋላ፤ ”ለምን ይከለክለዋል?... እንዴትስ ስሙን እንዲህ እያለ ያጠፋል?...” እያለ በእጅጉ ተቆጨ፡፡ ምንም እንኳን ያዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጁና ኃላፊው እሱ ቢሆንም፤ እንዲህ ያለውን ዓይን ያወጣ አምባገነን ሰው ውሳኔ መቀልበስ ወይ ማስቀልበስ ባለመቻሉ አዝኖ መቅረቱ ትዝ ይለኛል፡፡ እናም ይህን መሰሉን ፀረ በዓሉ እንቅስቃሴ በየመምሪያው ያዛምቱ እንደነበር፤ ዛሬ በሕይወት ያለነው ሁሉ ቋሚ ምስክሮች ነን፡፡ ባጠቃላይ በዓሉ ግርማ አንድ እራሱን እንኳን ከጥቃት መከላከል ያልቻለ፣ በነዚህ ኩታሮች የተከበበ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነበር ማለት ይቀላል፡፡
በነገራችን ላይ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የፖለቲካ ኮሜንታተር የነበረው ስመ ጥሩው ጋዜጠኛ ንጉሤ ተፈራ (ዛሬ ዶክተር)፤ ከጥቂት ወራት በፊት በጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ. ም. የሸገር ሬዲዮዋ መዓዛ ብሩ ”የጨዋታ እንግዳ” ዝግጅት እንግዳ ሆኖ ባቀረበችው ወቅት፤ ጓድ በዓሉ ግርማ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ተንኮለኞችን አስመልክቶ ለእሱ በግሉ የነገረውን አስገራሚና አሳዛኝ ጉዳይላድማጮቹ አካፍሏል፡፡ http://www.shegerfm.com/2013-05-09-11-11-20
ጋዜጠኛ ንጉሤ ተፈራ ይሠራ ከነበረበት ከብሥራተ ወንጌል የምሥራች ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ በሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትእዛዝና በሻለቃ አጥናፉ አባተ በተፈረመ ደብዳቤ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ በተዛወረበት ወቅት፤ ቋሚ ተጠሪውን ጓድ በዓሉ ግርማን ለመተዋወቅ እቢሮው ገብቶ በነበረበት ወቅት፤ ጓድ በዓሉ የተናገረውን አስገራሚ ነገር አስታውሶ ለመዓዛ አጫውቷታል፡፡ ጓድ በዓሉ ለጋዜጠኛ ንጉሴ የሰጠው አስገራሚ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰዎች ክፉ ባሕሪ ምስክርነት እንዲህ ይላል፡፡ ”....እዚህ አካባቢ ያለውን እውቀት ለመማር ቀናት አያስፈልግህም፡፡ ምናልባት ተንኮላቸውን ለማወቅ ከፈለግህ ግን የማቱሳላን እድሜ ይፈልግብህ ይሆናል...” ሲል ጓድ በዓሉ የሰጠው የቤቱ ዋና ሰው ዐቢይ ምስክርነቱ፣ ሁሌም አብሮት በሕያውነት የሚኖር መሆኑን ዶ/ር ንጉሤ ባግራሞት ገልጾታል፡፡ ከዚህ የጓድ በዓሉ አባባልም ማስተዋል የሚቻለው፤ ጓድ በዓሉ ባንዳንድ ያካባቢው ሰዎች እኩይ ምግባር ምን ያህል ተማሮ የሚኖር ሰው እንደነበረ ነው፡፡ ይህ የተንኮለኝነት እኩይ መንፈሳቸውም ግዘፍ ነስቶ፣ እሱን ለደርግ ሠይፍ አሳልፎ ለመስጠት እንዳበቃቸው፤ የገነት አየለን መጽሐፍ (በዓሉ ግርማን የሚመለከተውን ክፍል) ተመልሶ መመርመርና ”ጓድ ቁጥር ሃምሳ ሦስት”ን አፈላልጎ ማነጋገር ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ደራሲ በዓሉ ግርማ የኢሉባቦር ልጅ ነው፡፡ በመስከረም 1931 ዓ.ም. በዚሁ ክፍለ ሃገር በሱጴ ቦሩ ወረዳ ተወለደ፡፡ እናቱ የኢሉባቦር ተወላጇ ኢትዮጵያዊቷ ኦሮሞ ያደኔ ዳባ ሲሆኑ፣ አባቱ ደሞ የጉጅራት ሕንዱ ተወላጅ ”ባቡ” ወይም ”ጀርማንዳስ” ይባሉ የነበሩት አናጺ ናቸው፡፡ ”ግርማ” የሚለው ያባት መጠሪያ ስም የሕንዳዊው አባቱ ጓደኛ የነበሩት ያሳዳጊው ያቶ ግርማ ወልዴ ስም ነው፡፡በዓሉ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ካቶ ግርማ ጋር መኖር የጀመረው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በልእልት ዘነበ ወርቅ ት/ቤት፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት አጠናቋል፡፡ ከዚያም በ1951 ዓ.ም. ወደ ቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በመግባት፤ በፖለቲካል ሳይንስና በጋዜጠኝነት የባችለር ድግሪውን ተቀብሏል፡፡ በዚህ ዩኒቨርስቲ ቆይታው ወቅት በተማሪዎች ማኅበር ወስጥ ንቁ ተሳታፊ ከመሆኑም በላይ፤ ”VIEWS AND NEWS” የሚባል መጽሔት አዘጋጅ ነበር፡፡ በዚሁ የትምህርት ሕይወቱ ዘመን ውስጥ እያለ፤ ለኢትዮጵያን ሄራልድና ለኢትዮጵያ ሬዲዮ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ያገለግል እንደነበር ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡
በዓሉ የማስተርሰ ድግሪውን ያገኘው ባሜሪካን አገር ከሚገኘው ከሚቺጋን እስቴት ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ያጠናውም ፖለቲካል ሳይንስና ጋዜጠኝነት ነው፡፡ ከአሜሪካ መልስ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥሮ ከዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት ጀምሮ እስከ ቋሚ ተጠሪነት ደርጃ ድረስ ተጉዟል፡፡ በዚህም የሥራ ዓለም ሕይወቱ ሁሉ ከጋዜጠኝነትና ከደራሲነት ዓለም ሳይወጣ ሞሩን የሕይወት ታሪክ መዛግብቱ ያመለክታሉ፡፡ በጋዜጠኝነት የጀመረውን ሙያዊ ተልእኮውን ወደ ፈጠራ ደራሲነት የላቀ ደረጃ አሳድጎን ገሩን ያማርኛ ስነ ጽሁፍ ደረጃ አስመንድጎ፤ ”ካድርባይ ብእር ነጭ ወረቀት ይሻላል” ያለውን ቃሉን ጠብቆ በአርአያነት አልፏል፡፡
በዓሉ ግርማ ለፈጠራ ሥነ ጽሁፍ ተፈጥሮ፤ የሚያይ የሚያስተውል ብእር ጌታ ሆኖ ኖሯል፡፡ ”ካድማስ ባሻገር፣ ሀዲስ፣ የሕሊና ደወል፣ የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ ደራሲውና ኦሮማይ” የተሰኙት ሥራዎቹ አኩሪ ዘለዓለማዊ ሃውልቶቹ ናቸው፡፡ ይህ እንቁ በእረኛ በሕይወት ለመቆየት ቢታደል ኖሮ፤ ዛሬ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሁፍ እድገት ምንኛ አንድ እርምጃ ወደፊት ባስመነጠቀ ነበር እያልን እንቆጫለን፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ከሕግ ባለቤቱ ከወይዘሮ አልማዝ አበራ ሦስት ልጆችን አፍርቶ አልፏል፡፡ መስከረም፣ ዘላለምና ክብረ የተሰኙት ልጆቹ፤ ሁሉም ያባታቸውን ስምና ታሪክ አስከብረው፤ ለመኖር የተጉ ናቸው፡፡ ”የበዓሉ ግርማ ፋውንዴሽን” http://baalugirmafoundation.org/images/logo-name.gif የሚባል ተቋም አቋቁመውና ቋሚ ድረ ገጽ አዘጋጅተው መንቃሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
በዓሉ ግርማ በእጅጉ ያቀርባቸው ከነበሩ ወዳጆቹ መካከል ሁለቱን ላብነት ያህል መጥቀስ ይቻላል፡፡ አብዱ ሙዘይን የኢትዮጵያ ፊልም ማእከል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረውና ታዋቂው የብእር ሰው ስብሃት ገብረ እግዚአብሄር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ የብእር ሰው ስምና ሥራ ለማዝከር፤ ከቤተሰቦቹ ጎን መቆም የሁላችንም የዜግነት ግዴታ ነው፡፡
በዚህ መጠነኛ መጣጥፍ ውስጥ ከግራና ከቀኝ እየተዳሰሱ የቀረቡ መረጃዎች፣ በደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ሕይወትና ሕልፈት ዙሪያ አዲስ የምርምር ሥራ ለሚሠሩ ትጉሃን ሁሉ አንድ የመንደርደሪያ ጭብጥ ይሆናቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በታሪክ፣ በሥነ ጽሁፍና በተጓዳኝ የትምህርት ዘርፎች የመመረቂያ ጽሁፎቻቸውን ለማዘጋጀት ለሚነሳሱ ሁሉ ጥቁም ምንጭና መንደርደሪያ እንደሚሆናቸው እምነቴ ነው፡፡