Sunday, April 1, 2012

''የማይቀርበት" አሴ ባር!


በግምት ከአርባ ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ከፍ ብሎ ለከፈቱት ካፍቴሪያ የሰጡት ስያሜ ካስትል የሚል ነበር፡፡ ተጠቃሚው የዩኒቨርሲቲ ተማሪአሴ ባርብሎ ለቤቱ ያወጣው ስም ለሃያ ዓመታት ዘልቆ ዛሬ ላይ የቤቱ ቋሚ መጠርያ ሆኗል፡፡

በተለያዩ ዘመናት የነበሩ የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ እንዲሁም የሌሎች ተማሪዎች ሳይቀሩ ሻይ ቡና ለማለት በአሴ ባር ታድመዋል፡፡ በተለይም የስድስት ኪሎ ካምፓስ ተማሪዎች ከአሴ ባር ጋር ያለቸው ቁርኝት ለየት የሚል ነገር አለው፡፡ ሻይ ቡና ማለት ባይፈልጉ፣ ድካም ቢጫጫን ማታ አሴ ባር ጎራ ሳይሉ ማደር ለብዙዎች ቀላል ውሳኔ ላይሆን ይችላል፡፡ አሴ ባር ቦታ አለመኖሩን ሳያረጋግጡ ወደ ሁለተኛ ምርጫ መሔድም ለብዙዎች አይሞከርም፡፡ በዓመቱ መጨረሻ በምርቃት ጊዜ የክፍለ ሀገር ተማሪዎች ወላጆችም በአሴ ባር ይታደማሉ፡፡ እንደተስተናጋጅ ሳይሆን እንደ እንግዳ ሌሊቱንም በዚያው ያሳልፋሉ፡፡ የሰባ ዓመቱ አዛውንት፣ የካፍቴሪያው ባለቤት አቶ አሰፋ አበራ ከተለያዩ ዘመናት ተማሪዎች ጋር ያሳለፉትን ጊዜ በማስመልከት ከምሕረት አስቻለው ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይቺ ካፍቴሪያ መቼ ተከፈተች?

አቶ አሰፋ፡- ደርግ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ከመውሰዱ ቀደም ብሎ፣ በግምት አርባ ዓመታት ያስቆጠረች ይመስለኛል፡፡ ያኔም እንዲሁ ካፍቴሪያ ብቻ ነበረች፡፡ ሻይ ያኔ በቴርሙስ ነበር የሚቀርበው፣ ማሽን አልነበረም፡፡ ያኔም ተጠቃሚው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር፡፡ የተፈሪ መኰንንና የእቴጌ መነን ተማሪዎችም ይመጡ ነበር፡፡ ስንቶቹ እዚች ቤት ተዋውቀው ለጋብቻ በቅተዋል፡፡ አብዛኛው ተጠቃሚ ግን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው፡፡ የአራት ኪሎውም፣ ቴክኖሎጂ፣ ፋርማሲውም ሁሉ ነበር የሚመጣው፡፡ ቤቱ የተማሪ መገናኛ ነው፡፡ ያኔ ሻይ 10 ለስላሳ 20 ኬክ ደግሞ 15 ሳንቲም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ኋላ ታዋቂ ከሆኑ የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እነማንን ያስታውሳሉ?

አቶ አሰፋ፡- ማን ማን እላለሁ፣ በቴሌቪዥን የማየው ትልልቅ ኃላፊ፣ የቢዝነስ ሰው ሁሉ የማውቀው ነው፡፡ እነ ገነት ዘውዴ፣ እነ ዳዊት ዮሐንስ፣ ብርሃኑ ባየ፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩን አቶ ሶፍያን አሕመድን፣ ነብዩ ሳሙኤል፣ ጌታቸው ረዳና ብዙዎችን አውቃለሁ፡፡ ብዙዎች ይቺን ሻይ ቤት ያውቋታል፡፡ የትም ስሔድ የሚያጋጥሙኝ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እዚህች ቤት ቡና የጠጡ ናቸው፡፡ ከረዥም ዓመታት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ እዚሁ ድረስ መጥተው ሰላም የሚሉኝ፣ ገንዘብ የሚሰጡኝም አሉ፡፡ አንተ ሰውዬ በሕይወት አለህ ወይ፣ ያለህ አልመሰለንም ነበር ይሉኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል ውጭ አገር አምባሳደር ሆነው ሲሠሩ ቆይተው ሲመለሱ የጠየቁኝም አሉ፡፡ ስም አላውቅም እንጂ በመልክ የማላውቀው የለም፡፡ የኩሪፍቱ ሪዞርት ባለቤት የተፈሪ መኰንን ተማሪ ነበር፡፡ እሱንም አውቀዋለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከቀድሞና ከቅርብ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ያለዎት ቅርበት እንዴት ነው?

አቶ አሰፋ፡- ከአሁኖቹ ጋር የዕድሜ ልዩነቱም ሰፊ ስለሆነ ብዙ አልቀራረብም፣ ከዱሮዎቹ ጋር ግን በጣም ቅርበት ነበረኝ፡፡ አብሬ ሁሉ ሌላ ቦታ ሻይ ለመጠጣት እሔድ ነበር፡፡ እነሱ ቁጥራቸውም ትንሽ ስለነበር ማን ማን ብሎ መለየት ይቻል ነበር፡፡ ቢሆንም ከእነዚህኞቹ ጋርም ያለኝ ግንኙነት ጥሩ ነው፡፡ ዱሮም አሁንም ለምርቃት ድንኳን ወይም ዳስ ይጣላል፡፡ ለክፍለ ሀገር ተማሪዎች እኔ ሁሉን አድርጌ ዝግጅት አደርጋለሁ፡፡ ወላጆቻቸው የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ እናቴ ወይም አባቴ አሴ ቤት ጠጣ ብሎኛል ብለው መጥተው የሚነግሩኝ ተማሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት በደርግ ዘመን ቤቱን መንግሥት ይፈልገዋል ልቀቁ ተብለው ነበር?

አቶ አሰፋ፡- አዎ ለኢሠፓ የሆነ ነገር ይፈለጋልና መልቀቅ አለብህ ተብዬ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የነበሩ የስድስት ኪሎ ተማሪዎች ራሳቸው በአምስተኛ በር በኩል አንድ ቤት አፈላልገው በማግኘት እዚያ እንድገባና እንድሠራ ሁኔታዎችን አመቻችተው ነበር፡፡ እንደ እድል ሆኖ ቤቱን ሳልነጠቅ ቀረሁኝ፡፡ በዚያ ዘመን ተማሪዎች ለምን እሱ ቤት ብቻ ይገባሉ? ትግሪኛ ሙዚቃ ለምን ይከፍታል? እንግሊዝኛ ሙዚቃ ያጫውታል፣ የኢምፔሪያሊዝም ቅጥረኛ ነው እየተባልኩ በተደጋጋሚ በአብዮት ጠባቂዎች እጠየቅ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬም ወደ ቀበሌ መሔድ ደስ አይለኝም፡፡ እኔ ደግሞ ሁሉንም ሙዚቃ ነበር የማደርገው፡፡ ሴትና ወንድ ጥንድ ሆነው እየተላኩ እንድሰለል ይደረግ ነበር፡፡ ገንዘብ ሁሉ ይወሰድብኝ ነበር፡፡ በርግጥ እኔ አላውቅም እንጂ ዋናዎቹ የኢሕአፓ አንቀሳቃሾች (ተማሪዎች) እዚህች ቤት ይመላለሱ፣ ሁለት ሦስት እየሆኑም ይወያዩ ነበር፡፡ ይህን ያወቅኩት ግን ከጊዜ በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞና የአሁኑን ተማሪ ያነፃፅሩ እስኪ?

አቶ አሰፋ፡- የዱሮ ተማሪ በአስተሳሰብ የላቀ ነው፡፡ የትምህርቱ ሁኔታ ይሁን ወይም ቁጥራቸው በጣም ውስን መሆን የቀድሞ ተማሪ በብዙ መልኩ የተሻለ ነበር፡፡ በማኅበራዊ ንቃተ ኅሊናም ቢሆን የዱሮዎቹ ኃይለኞች ናቸው፡፡ ቢሆንም ያው ሁሉም እንደጊዜው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዛሬ ዙሪያውን በርካታ ካፍቴሪያዎች ተከፍተዋል፡፡ የአሴባር ገበያ ቀዝቅዟል?

አቶ አሰፋ፡- ለተማሪው ምርጫ ስለሚሰጥ የሌሎች መምጣት ደስ ነው የሚለኝ፡፡ እኔ ግን ዛሬም አብዛኛው ተማሪ መጀመርያ እዚህ መጥቶ መሙላቱን ሲያረጋግጥ ነው የሚመለሰው፡፡ ተማሪዎች ቤቱን እንደ ሻይ ቤት ብቻ ሳይሆን እንደማይቀርበት የቤተሰብ ቤት ነው የሚመለከቱት፡፡ እዚህ ቤት መመላለስ እንደ አንድ ኮርስ ነው የሚታየው እያሉ የሚቀልዱኝ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎች እንደ ነጋዴ ሳይሆን እንደ አባት ነው የሚያዩኝ፡፡ ገንዘብ ስጠን አበድረን የሚሉኝም ነበሩ፡፡ አብሬ የምበላውም ከተማሪ ጋር ነው፡፡ አሁን እንኳ ገንዘብ የሚጠይቀኝ ተማሪ የለም፤ የዱሮዎቹ ነበሩ፡፡ እኔም የአቅሜን ትምህርቱ በዲግሪ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር እያልኩ እመክራለሁ፡፡ እኩለ ሌሊት አልፎ እንኳን መውጣት የማይፈልጉ ተማሪዎች አሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቤቱ ከቀድሞ ይዞታው በእድሳት ተቀይሯል?

አቶ አሰፋ፡- ብዙ አልተቀየረም፡፡ በደርግ ጊዜ ብዙ ችግር ስለነበረብኝ ማደስም አልችልም ነበር፡፡ ነገር ግን ተማሪዎች የዱሮውን ይወዱት ነበር፡፡ ሐረግ፣ ሸንበቆ. . . እንደዚያ እንደዚያ ነበር፡፡ ቤቱ ቢታደስ እቃ ቢቀያየር ተማሪው ብዙ ግድ የለውም፡፡ ምክንያቱም ከቤቱ ጋር ያላቸው ቁርኝት የቤተኝነት ነው፡፡ ተማሪው እንዲሁ ዝም ብሎ ቤቱን ይወደዋል፡፡ እኔን ተጣርቶ ደህና እደር ሳይል ዝም ብሎ ጠጥቶ መሔድ የማይሆንለት ተማሪ በርካታ ነው፡፡ እኔም ሥራ ካልበዛ ግራ ቀኙን አየት አድርጌ አንገቴን ዝቅ አድርጌ ሰላምታ እሰጣለሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቡናዎት በጣም ያነቃል ይባል ነበር? ምን የተለየ ነገር አለው?

አቶ አሰፋ፡- ቶሞካና አቦል ቡናን እየቀላቀልን ነበር የምናፈላው፡፡ ማሽኑም የተለየ ነው፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ጣሊያን ውስጥ የተመረተ ነው፡፡ አሁን ደግሞ አቢሲኒያንም ጨምረን ሦስቱን እየቀላቀልን ነው የምናዘጋጀው፡፡ ቡናውን የተለየ ኃይልና ጣዕም የሰጠው ቅልቅሉና ማሽኑ ነው፡፡ ማሽኑን የባሕር ኃይል አባል በነበረ ባለቤቷ አማካይነት ከጣሊያን ያስመጣችልኝ የቀድሞ የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪና እዚህ እየመጣች ሻይ ትጠጣ የነበረች ተማሪ ነች፡፡ በቅርቡ ቤቱ ሲታደስ የመስኮቶችና የበር ዲዛይን የሠሩልኝም ተማሪዎች ናቸው፡፡ ሠርጋቸውን ሁሉ አክብረው የሚጠሩኝ አሉ፡፡ ሸራተን ሲመረቅ በቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አምስት መግቢያ ካርድ ተሰጥቶኝ ነበር፡፡

በየመንገዱ እዚያም እዚህም ያስቆሙኛል፡፡ መኪና አቁመው ወርደው አንተ ሰውዬ በሕይወት አለህ ወይ ብዙ አላረጀህም ይሉኛል፡፡ ሁሌ ውሎዬ ከወጣት ጋር ነው በየት አረጃለሁ? የእኔን ዕድል ማንም አላገኘውም፡፡ እዚህች ቤት ሠርቼ ገንዘብ አላተረፍኩም እንጂ ሰው አፍርቻለሁ፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቅ ደረጃ የትም ልሒድ የሚያውቀኝ አክብሮ የሚቀበለኝ ነው ያለው፡፡ ይህን ሁሉ የተማረ ኃይል ማወቅ ታላቅ ዕድል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአሴ ባር ደንበኛ ከነበሩ የቀድሞ ተማሪዎች ዕርዳታ ያገኙበት የተለየ አጋጣሚ አለ?

አቶ አሰፋ፡- ከዓመታት በፊት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ ልጄ ሦስተኛ ዓመት ሳለ ዓይኑን በጠና ታሞ ደቡብ አፍሪካ ሔዶ ይታከም ተባለ፡፡ ብዙዎች ተባብረውኝ እኔም ያለችኝን ጨምሬ እንዲሔድ ወዲያ ወዲህ ማለት ጀመርን፡፡ አየር መንገድ ስሔድ የሚያውቁኝ የቀድሞ ተማሪዎች ቲኬቱን፣ አብረው ለሚሔዱት አስታማሚዎችም በርከት ያለ ዶላር በማስፈለጉ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብሔራዊ ባንክ ስሔድ ኃላፊው የቀድሞ ተማሪ ሆኖ ሁሉም ተባበሩኝ፡፡ ወንድሙ የትምህርት ማስረጃውን ለማውጣት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢሔድ ዲኑን ጨምሮ ሌሎች መምህራንም የቀድሞ ተማሪዎች የዚህች ቤት ደንበኞች ሆነው ተገኙ፡፡ እውነት የእኔን ዕድል ማንም አላገኘውም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment