Sunday, April 29, 2012

በቴዲ አፍሮና በአዲካ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ


ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከአዲካ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንትስ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

ቴዎድሮስና አዲካ ውዝግብ ውስጥ የገቡት ‹‹ጥቁር ሰው›› በተሰኘው የቴዎድሮስ አዲሱ አልበም ከስፖንሰርና ከሽያጭ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮና አዲካ መጋቢት 1 ቀን 2004 .. ባደረጉት ውል፣ ቴዎድሮስ የአልበሙን ዋና ሲዲ (ማስተር ሲዲ) በአራት ሚሊዮን ብር ሸጧል፡፡ ክፍያውም በሁለት ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ 

በዚህ ውል መሠረት አዲካ ያወጣውን ሙሉ ወጪ ከመለሰ በኋላ ከሚገኘው የተጣራ ትርፍ ቴዎድሮስ 20 በመቶ ገቢ ያገኛል፡፡ ይህም ለአምስት ዓመታት የሚቀጥል ሆኖ፣ ከአምስት ዓመት በኋላ በሲዲው ላይ ያለው ሙሉ መብት ከአዲካ ወደ ቴዎድሮስ ይዛወራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በውሉ መሠረት አዲካ ስፖንሰር የመፈለግና በህትመቱ ላይም የስፖንሰሩን ማስታወቂያ የመጠቀም መብት ይሰጠዋል፡፡ በቴዲና በአዲካ መካከል በዋናነት አለመግባባቶች የተፈጠሩት በእነዚህ ነጥቦች ዙርያ ሲሆን፣ አለመግባባታቸውም እየከረረ መምጣቱን ምንጮች እየገለጹ ነው፡፡ በአለመግባባቱ ውስጥም የሦስትዮሽ ውል የፈረመው ቤሌማ ኢንተርቴይመንት ኩባንያም ሌላኛው ተዋናይ ነው፡፡

ለቴዲ ቅርብ የሆኑ የመረጃ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ቴዲ በሲዲው ላይ የሜታ ቢራ ማስታወቂያ ይለጠፋል ብሎ አላሰበም፡፡ ነገር ግን ሲዲው በሚታተምበት ወቅት የሜታ ቢራ ማስታወቂያ በዋናው ሲዲ ላይ ተለጥፎ የተመለከተው ቴዲ ‹‹ሙዚቃዬን ትልልቅ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናትም ያዳምጡታል፤ ለሕፃናቱ የመጠጥ አርዓያ መሆን አልፈልግም፤›› የሚል ሐሳብ በመሰንዘሩ፣ የሜታ ቢራ ማስታወቂያ የተለጠፈበት ኮፒ እንዲወገድ ብሎም ለገበያ እንዳይቀርብ ስምምነት ላይ ይደረሳል፡፡ በቴዲ በኩል ያሉ መረጃዎች የሜታ ቢራ ዓርማ የተለጠፈባቸው ሲዲዎች ብዛት 120 ሺሕ ነው ቢባልም፣ በአዲካ በኩል ግን 87 ሺሕ ኮፒዎች ናቸው፡፡‹‹በውላችን መሠረት የስፖንሰሩ ጉዳይ ይመለከተናል፤ ለእኛ ግን ምንም የቀረበልን ሐሳብ የለም፤›› ሲሉ የቤሌማ ኢንተርቴይመንት ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወሰን አበጀ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሚያዝያ 6 ቀን 2004 .. ለሚሠራጨው ሲዲ ማስተር ሲዲውን አሥር ቀን እየቀረው የተረከበው አዲካ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶበታል በሚል ሲዲው ላይ ያለውን የሜታ ማስታወቂያ በማርከር በማጥፋት ለገበያ አቅርቧል፡፡ ይህ የተደረገው ብቸኛው ስፖንሰር የተባለው የሜታ ቢራ ፋብሪካ ይሁንታ በመገኘቱ ነው ሲሉ፣ የአዲካ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዋድ መሐመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በገበያ ውስጥ ይህ የተደለዘ ሲዲ መሠራጨቱን የተመለከተው ቴዲ በሁኔታው ደስተኛ አለመሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሌላኛው አለመግባባት ቴዎድሮስ የታተመውን የሲዲ ቁጥር ማወቅ አለመቻሉ ነው ተብሏል፡፡ የቴዎድሮስን ሐሳብ አቶ ወሰንም ይጋራሉ፡፡ 

ቴዲና አዲካ ባላቸው ስምምነት መሠረት ‹‹ጥቁር ሰው›› አልበም ከሚያስገኘው የተጣራ ትርፍ ገቢ ውስጥ 20 በመቶ ለቴዲ አፍሮ የሚከፈል ነው፡፡ የተጣራ ትርፍ መኖሩን ለማወቅ ከሚያገለግሉ ነገሮች አንዱ የታተመውን የሲዲ ቁጥር ማወቅ ነው፡፡ በመጀመርያዎቹ የህትመት ወቅቶች የተዘረጋው የሞባይል አጭር መልዕክት (SMS) ሲላክ የሚጻፍ ሲሪያል ቁጥር ታትሞበታል፡፡ ቴዎድሮስ የሲርያል ቁጥሩ ቢቀጥል የታተመውን የሲዲ ብዛት ማወቅ ያስችላል ብሎ ያምናል፡፡

በሚቀጥሉት የሲዲ ህትመቶች ግን ምንም ዓይነት ሲሪያል ቁጥር ታትሞ ለገበያ እንዳልቀረበ የሪፖርተር መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ ከቴዎድሮስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ቴዎድሮስ ሙሉ ትኩረቱን ሙዚቃው ላይ ከማድረጉ ባሻገር የቢዝነስ ሥራዎችን ማኔጀሩ አቶ አዲስ ገሠሠ ያካሂዳሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ቴዎድሮስ በሁኔታው ደስተኛ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

ቴዎድሮስ ዝርዝር መረጃዎችን ከማኔጀሩ ማግኘት እንደሚቻል ቢገልጽም፣ የሪፖርተር መረጃዎች እንደሚሉት ቴዎድሮስና ማኔጀሩ መግባባት ተስኗቸዋል፡፡ ከማኔጀሩ ከአቶ አዲስ ገሠሠ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከቴዎድሮስ ጋር መግባባት ያልተቻለው ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በቴዲ የመቃወሚያ ነጥቦች አዲካ ኮሙዩኒኬሽን በፍፁም እንደማይስማማና ይልቁንም የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ርቀት መሄዱን፣ የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዋድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በመጀመርያ አዲካ የሜታ ቢራን ማስታወቂያ በሲዲው ላይ ለማተም የውል ስምምነቱ ይፈቅድለታል፡፡ ‹‹ነገር ግን ቴዎድሮስ ሕፃናት ሙዚቃዬን ይሰማሉ ማለቱን እንደ መልካም ነገር ወስደን ከሲዲው ላይ አጥፍተነዋል፡፡ ካለን ጊዜ አንፃር ሲዲው ጥቅም ላይ እንዳይውል ቢባልም በደረስንበት ወቅታዊ ስምምነት ማስታወቂያውን አጥፍተን ገበያ ላይ አውለነዋል፤›› ሲሉ አቶ አዋድ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሲዲው ለገበያ የሚቀርብበት በጣት የሚቆጠሩ ጊዜያት ብቻ ነበሩን፤ ጊዜ ወሳኝ ነበር፤›› ሲሉ አቶ አዋድ የወቅቱን አንገብጋቢነት አስረድተዋል፡፡ ማሽኑ በቀን የማተም አቅሙ 20 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ ሲዲ ነው፡፡ በዚህ የማምረት አቅም የሜታ ማስታወቂያ የተለጠፈበትን 87 ሺሕ ኮፒ ማስወገድ የሚቻል ነገር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ሲሪያል ቁጥር የተሰጠው ለግጥሞቹ ነው ተብሎ አዲካ፣ የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበርና የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በመተባበር ማንኛውም ሰው ኦሪጂናል መግዛቱ የሚታወቅበትና በዚህም የሚሸለምበት አሠራር ነው የተዘረጋው ያሉት አቶ አዋድ፣ ‹‹በነበሩን ጥሩ የሥራ ግንኙነቶች ምክንያት ብሔራዊ ሎተሪ ፈቃድ እንደሚሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ህትመት ቢጀመርም፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ብሔራዊ ሎተሪ ፈቃድ ከልክሏል፤›› ሲሉ የሲሪያል ቁጥር በመጀመርያዎቹ ህትመቶች መካተቱንና በተከታዮቹ ህትመቶች ላይ መቋረጡን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የሲሪያል ቁጥር የታተመው የሲዲ ኮፒ ብዛቱን ለማወቅ አይደለም፤›› ሲሉ አቶ አዋድ ይገልጻሉ፡፡ አንድ ባዶ ሲዲ የሚገዛው በአራት ብር ነው፡፡ የሲዲ መሸፈኛ (ከቨር) አምስት ብር ነው፡፡ የግጥሙ ህትመት ዋጋውም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ከአንድ ሲዲ የሚገኘው ትርፍ ስድስት ብር ነው፡፡ በእስካሁኑ ሒደት የታተመው ሲዲ የወጣበት ወጪ 12 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን፣ አዲካ ሙሉ ወጪውን ከሸፈነ በኋላ ከሚያገኘው የተጣራ ትርፍ ውስጥ 20 በመቶው ለቴዎድሮስ ገቢ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የካሴት ህትመቱ የትና እንዴት እንደተካሄደ ለቴዲ እንቆቅልሽ ሆኖበታል፡፡ ለገበያ ቀረበ የተባለውን የሲዲ ቁጥር እንደማያምንበት ቴዎድሮስ ተናግሯል፡፡ ቴዎድሮስ ከውጭ አገር የታተመ ሲዲ ገብቷል ብሎ ከማመኑም በተጨማሪ፣ ለውጭው ዓለም በምን መንገድ ሲዲው እንደተሠራጨ አሁንም ቴዲ ይጠይቃል፡፡

አቶ አዋድ ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በተመሰከረለት ባለሙያ ኦዲት ይደረግ መባሉን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሒደትም ላይ ኤችኤስቲ የተሰኘው ኩባንያ ተመርጦ ወደ ኦዲቲንግ ሥራ በመግባት ላይ እያለ ቴዎድሮስ ኦዲቲንጉ እንዲቆም ማድረጉ ተሰምቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ወገኖች አለመግባባት በጡዘት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ አካላት በሽምግልና ለመገላገል እየሞከሩ መሆኑ ታውቋል፡