ቀደም ሲል ሠኞ ህዳር 9 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ አቶ መላኩ ፈንታ ባቀረቡት መከራከሪያ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን በማስረዳት ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊታይ እንደሚገባ የገለፁ ሲሆን አቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ በሠጠው አስተያየት፤ ተከሣሹ በእርግጥም በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ም/ቤት አባል መሆናቸውን ተቀብሎ፣ ነገር ግን የሚመሩት መስሪያ ቤት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለመሆኑ፣ ተጠቃሹ ያላቸው የሚኒስትር ማዕረግነት ለጥቅማ ጥቅም አላማ ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ አስረድቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለረቡዕ ህዳር 11 ቀን 2006 ቀጠሮ የሠጠ ሲሆን ረቡዕ እለት የዋለው ችሎትም መዝገቡ የተቀጠረው በፍርድ ቤቱ የቀረበውን ጉዳይ ከማየት ስልጣን ጋር ተያይዞ በተነሣው ጭብጥ ላይ ብይንና ትዕዛዝ ለመስጠት መሆኑን አስታውቆ ብይን ሠጥቷል፡፡
ፍ/ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት ነው የሚለው ሣይረጋገጥ ወደ ክርክር መግባት አይቻልም ካለ በኋላ፣ በተነሣው መከራከሪያ ጭብጥ መሠረት፣ አቶ መላኩ ሚኒስትር ናቸው ወይስ አይደሉም? ሚኒስትር ከሆኑስ ጉዳዩን አከራክሮ የመወሠን ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት ነው የሚለው የግድ እልባት ማግኘት አለበት ብሏል።
ፍ/ቤቱም አቶ መላኩ ፈንታ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ከግራ ቀኙ ክርክር እና ከተለያዩ ሠነዶች ማረጋገጡን በብያኔው አስታውቆ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ አዋጅ መሠረት፤ የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት (ሚኒስትሮች ጨምሮ) በስራ ሃላፊነታቸው ምክንያት ተጠያቂ በሚሆኑባቸው ሙስናን ጨምሮ ማናቸውም የወንጀል ጉዳዮች የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የስረ-ነገር ስልጣን የተሰጠው መሆኑ በግልፅ ስለ ደነገገ፣ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሁለት አዋጆች ሁለት ንኡስ አንቀፆች ህገ-መንግስታዊ ናቸው? አይደሉም? የሚለው ትርጉም የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ብሏል - ፍ/ቤቱ፡፡
በተለይ የአቶ መላኩ ጉዳይ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚታይ ከሆነ፣ በህገ መንግስቱ የተከበረላቸውን መሠረታዊ ጉዳያቸውን በይግባኝ እንዲታይ የማቅረብ መብት በግልፅ የሚጋፋ መሆኑን ያመላከተው የፍ/ቤቱ ብይን፤ አቶ መላኩ በዋና ወንጀል አድራጊነት ከሌሎች ሠዎች ጋር ተጣምሮ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው በመሆኑና የሁሉም ተከሣሾች ጉዳይ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቢታይ ሁሉም ተከሣሾች በህገ መንግስቱ የተከበረውን የይግባኝ ጉዳይ የማቅረብ መብት በግልፅ የሚጋፋ ከመሆኑም ሌላ የአቶ መላኩ ጉዳይ ብቻውን ተነጥሎ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እንዲሁም ከእሣቸው ጋር የተከሠሡት ሌሎች ተከሣሾች ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተነጥሎ ይታይ ቢባል ደግሞ ሁሉም ሠዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማናቸውም አይነት ልዩነት ሣይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል ከሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 25 መሠረታዊ መርህ ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ፍ/ቤቱ በብይኑ አትቷል፡፡ ይሄ ማለት፣ አቶ መላኩ በጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳያቸው ይታይ ቢባልና ሌሎች ተከሣሾች ተነጥለው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ጉዳያቸው ይታይ ቢባል፣ ሌሎች ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸው ሲከበርላቸው፣ አቶ መላኩ የይግባኝ መብት እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ይሆናል፡፡ የአቶ መላኩም ሆነ የሌሎች ተከሣሾች ሠብአዊ መብት በእኩል እንዲጠበቅ አከራካሪው ጉዳይ የህገ-መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ብሏል፡፡ በዚህ መሠረት የህገ መንግስታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሣኔ ሊያገኝ የሚገባ በመሆኑ፣ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፣ ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች የማጣራት ሃላፊነት የተጣለበት በመሆኑና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 20(6)፣ አንቀፅ 25፣ አንቀፅ 10 እና አንቀፅ 13(1) ይቃረናሉ ወይስ አይቃረኑም? እንዲሁም የስረ ነገሩ ስልጣን የየትኛው ፍ/ቤት ነው? የሚለውን እንዲመረምርና ትርጉም እንዲሠጠው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳዩ ሊመረመር እንደሚገባ በማመን፣ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ፍ/ቤቱ በይኗል፡፡
ፍ/ቤቱ በሠጠው ትዕዛዝም የብይኑ ትዕዛዝ ግልባጭ በመሸኛ ለፌደሬሽን ም/ቤት ፅ/ቤት እና የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ፅ/ቤት በእለቱ እንዲላክ በማለት ለታህሣስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በፍ/ቤቱ ብይንና ትዕዛዝ ዙሪያ የህግ ትንታኔ እንዲሠጡን ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ምሁራን፤ እንዲህ አይነቱ ብይን ከዚህ ቀደም በእነ አቶ ታምራት ላይኔ እና አቶ ስዬ አብርሃ ላይ ተግባራዊ ተደርጐ እንደነበር በመጠቆም፣ ፍ/ቤቱ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የሚላቸውን ጉዳዮች በራሱ ከመወሠኑ በፊት ለሚመለከተው አካል መምራቱ ተገቢ ነው ብለዋል።
http://addisadmassnews.com
No comments:
Post a Comment