Friday, November 22, 2013

በ1997ቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢ የነበሩት አና ጐሜዝ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው

በ1997 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫና ምርጫውን ተከትሎ ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ ውዝግብ አካል የነበሩት የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ አና ጐሜዝ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም. ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ በአውሮፓ ኅብረት ተወክለው ምርጫውን በዋና ታዛቢነት የመሩትና የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባል የሆኑት አና ጐሜዝ፣ ምርጫውን አስመልክቶ ባወጡት ሪፖርት ኢሕአዴግ ከሚመራው መንግሥት ጋር ጥልቅ የሆነ ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡

አና ጐሜዝ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በምርጫው ሳቢያ ውዝግብ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ የኢሕአዴግን ፖለቲካ በተለይም የሰብዓዊ መብት አያያዙን ከመተቸት ተቆጥበው አያውቁም፡፡ ይሁን እንጂ ከምርጫው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አያውቁም፡፡



በሚቀጥለው ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ፣ የካረቢያንና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች የጋራ የፓርላማ አባላት ጉባዔ ላይ ለመገኘት በአገሮቹ ከተወከሉ ግለሰቦች መካከል አና ጐሜዝ እንዳሉበት በኢትዮጵያ በኩል የጉባዔው አስተባባሪ ከሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምንጮቻችን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለፖርቹጋላዊቷ የፓርላማ ተወካይ አና ጐሜዝ ቪዛ ሰጥቶ ይሁን ከልክሎ ለማወቅ ያደግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቧ በቲዊተር ገጻቸው ላይ በአዲስ አበባው ጉባዔ ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡ አና ጐሜዝ በ1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ምርጫ ትዝብት ሪፖርታቸው፣ ምርጫው ነፃና ፍትኃዊ እንዳልነበር ሪፖርት በማድረጋቸው ሪፖርቱ የውዝግቡ ምንጭ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሪፖርቱን ከማጣጣል አልፈው ግለሰቧን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ መዝለፋቸው ይታወሳል፡፡

አና ጐሜዝ በበኩላቸው እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የዕርዳታ ማዕቀብ እንዲጣልበት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም የእንግሊዝና የአሜሪካ መንግሥታት በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ መንግሥት የሚፈጽመውን በደል እያዩ እንዳላዩ፤ እየሰሙ እንዳልሰሙ ችላ ብለዋል፤›› በማለት ከዓመት በፊት የሰላ ትችት በመሰንዘር የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚደረገውን ዕርዳታ እንዲያቆም ተከራክረዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment