Sunday, November 10, 2013

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሕይወት ወደ አገራቸው ለመመለስ መንግሥትን እየተማፀኑ ነው

-ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች መሞታቸው ተጠቁሟል

-‹‹በሕገወጥ መንገድ ለሄዱት ክትትልና ጥበቃ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ለተለያዩ ሥራዎች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በተለያዩ ጊዜያት በሄዱ ኢትዮጵያውያን ላይ የአገሪቱ መንግሥት ከአገር እንዲወጡ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ተከትሎ፣

ዜጎች እየተገደሉ መሆኑን በመጠቆም መንግሥት እንዲታደጋቸው እየተማፀኑ ነው፡፡የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት፣ ከተለያዩ አገሮች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ የገቡና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ከ16 ሺሕ በላይ ዜጎች እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ወደአገራቸው እንዲመለሱ በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት፣ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ አገሮች ዜጎች እየታደኑ በመታሰር ላይ መሆናቸውን የተለያዩ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙኃን እየገለጹ ነው፡፡



ፈትያ አህመድ የተባለች ኢትዮጵያዊት ለሪፖርተር ደውላ እንደገለጸችው፣ ስልክ የምትደውለው በተደበቀችበት ቦታ ሆና ነው፡፡ ‹‹ቁጥራቸው የማይታወቅ ብዙ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፡፡ የታሰሩም ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ወንዶች በየቀኑ ላለፉት ሰባት ቀናት እየታደኑና እየተገደሉ ነው፡፡ በወንዶቹ ላይ ክትትሉና ግድያው የፀናው ለማምለጥ ስለሚሞክሩ ነው፡፡ ሴቶቹን እየወሰዱ በጠባብ ክፍል ውስጥ እያጎሯቸውና አንዳንዶቹንም እየደፈሯቸው ነው፤›› በማለት አስታውቃለች፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻችላቸው ሲጠይቁት ‹‹ጠብቁ እየተነጋገርንበት ነው›› ከማለት ውጪ እየደረሰባቸው ላለው ስቃይና ግድያ አፋጣኝ ምላሽ እንደነፈጋቸው የገለጸችው ፈትያ፣ ግድያና መንገላታቱ እየደረሰባቸው ያሉት ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መንገድ የገቡት ብቻ ሳይሆኑ፣ በሕጋዊ መንገድም ሄደው ከአሠሪዎቻቸውና ከወኪሎቻቸው ጋር ባለመስማማታቸው፣ ፖስፖርታቸውን እየተነጠቁ ያለምንም ማስረጃ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን አስረድታለች፡፡

በሰው አገር እንዲሰደዱ ያደረጋቸው የተሻለ ሥራ ሠርተው ወደ አገራቸው በመመለስ፣ ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸውን ለማስተዳደር መሆኑን የገለጸችው ፈትያ፣ የአንድ አገር መንግሥት ዜጎቹን ማየት ያለበት እንደ እናትና አባት መሆን እንዳለበትና በሕገወጥ መንገድ የሄዱ ቢሆንም አሁን እየደረሰባቸው ላለው ግድያ፣ ድብደባና ስቃይ ፈጥኖ መድረስ እንዳለበት ገልጻለች፡፡ በመሆኑም እየደረሰባቸው ካለው ስቃይና እልቂት ሊታደጋቸው እንደሚገባም ሳግ እየተናነቃት መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በሳዑዲ ዓረቢያ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና እየደረሰባቸው ስለሚገኘው ግድያ፣ እስራትና ስቃይ ተጠይቀው በትዊተር ገጻቸው በሰጡት ምላሽ ሚኒስቴራቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዜጎቹ ጎን መሆኑንም አክለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያውያኑ ስለደረሰባቸው ግድያ፣ ውክቢያና እስራት በተመለከተ እንደተናገሩት፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በአገሩ የሚገኙ የሌሎች አገሮች ዜጎች፣ በሕጋዊ መንገድ የሚያንቀሳቅሳቸውን ሰነድ እንዲያድሱ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር፡፡ በቀነ ገደቡ ማሳደስ ያልቻሉ አገሩን ለቀው መውጣት አለባቸው ብለዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ደግሞ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የይለፍ ደብዳቤ ማግኘት እንዳለባቸው፣ ኤምባሲው በአሁኑ ጊዜ ሰነድ ያላቸውን እያደሰና የይለፍ ደብዳቤ እየሰጠ እንደሚገኝ፣ በሕገወጥ መንገድ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ኤምባሲውን የሚያገኙት ችግር ሲገጥማቸው ብቻ በመሆኑ፣ አስከፊ ችግር ሲደርስ ለዜጎች ትክክለኛ ጥበቃና ክትትል ለማድረግ ለኤምባሲው አስቸጋሪ እንደሆነበት አስታውቀዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን በሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ጋር በመሆን ለዜጎች ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሚኒስቴሩ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ ፖሊስ ግን የአገሪቱ መንግሥት የሰጠው ቀነ ገደብ እንዳበቃ የመኖሪያ ቤቶችን፣ ሱቆችን፣ ሆቴሎችንና የተለያዩ የሥራ ቦታዎችን በመውረር፣ ዜጎችን እንደ በግ እየጎተተና ሊያመልጡ የሚሞክሩትን በመግደል ሕገወጥ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን፣ በተለይ ነዋሪነታቸውን በሳዑዲ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ድረ ገጾች እያሳወቁ ነው፡፡

ልጆቻቸውን በሕጋዊ መንገድ፣ በደላላና በተለያዩ ዘዴዎች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የላኩ ኢትዮጵያውያን ወላጆች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ሰሞኑን በየመንና በሳዑዲ ዓረቢያ መንገዶች ላይ ተገድለውና ተጥለው የሚታዩ የኢትዮጵያውያን አስከሬኖች ያዩ ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ፣ መላ ኢትዮጵያውያንን ሥጋት ውስጥ የከተተ መሆኑን ልጃቸውን ከአራት ወራት በፊት የላኩት አቶ ፍስሐ ይህደጎ ተናግረዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመለከተው መስሏቸው ለመጠየቅ ሲሄዱ፣ የሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑን እንደነገሯቸው የገለጹት አቶ ፍስሐ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሄዱ ልጃቸው እንዴት እንደሄደች ከጠየቋቸው በኋላ በሕጋዊ መንገድ መሆኑን ሲያረጋግጡ ‹‹እሷ ችግር የለባትም ችግር የተፈጠረው በሕገወጥ መንገድ በሄዱት ላይ ነው፤›› ተብለው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ፍስሐ ግን ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ያለውን የግፍ ግድያና እንግልት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲሰሙ እየተረበሹ መሆኑን አልደበቁም፡፡ እንደ አቶ ፍስሐ ሁሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወላጆች በጭንቀት ላይ መሆናቸውን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየገለጹ ነው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment