Monday, November 25, 2013

የስዊዘርላንድ ባንክ ለኢትዮጵያ ባቡር ፕሮጀክት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አፀደቀ



-ኢትዮጵያ ለሚገቡ የአሜሪካና የአውሮፓ ኩባንያዎች ፋይናንስ አቀርባለሁ አለ

የስዊዘርላንድ ባንክ ከአዋሽ ወልዲያ (ሃራ ገበያ) ድረስ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ግንባታ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አፀደቀ፡፡

ክሬዲት ስዊስ የሚሰኘው ይህ የስዊዘርላንድ ባንክ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር የብድር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ከአዋሽ እስከ ወልዲያ ድረስ የሚዘረጋውን 389 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ለመገንባት ባለፈው ዓመት ሐምሌ የቱርክ ኩባንያ የሆነው ያፒ ማደርከንዚ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የቱርኩ ኩባንያ ይህንን የባቡር መስመር በ1.7 ቢሊዮን ዶላር ለመገንባት ነው ውል የገባው፡፡ 



ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበለትን የብድር ጥያቄ ሲመረምር የቆየው ክሬዲት ስዊስ ባንክ በመጨረሻ ብድሩን ያፀደቀ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ባንኩ የአውሮፓና የአሜሪካ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በባቡር መስመርና በኢነርጂ ዘርፍ የሚሰማሩ ከሆነ ብድር እንደሚፈቅድ መግለጹን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

በተለይ በባቡር መስመር ግንባታና በኢነርጂ የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የስዊድንና የቱርክ ኩባንያዎች ፍላጐት እያሳዩ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከቻይና በተጨማሪ የአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ ፋይናንስ ለማድረግ ፍላጎታቸው እየተነሳሳ መሆኑን ያሳያል ሲሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ተንታኝ፣ ከባንኩ የተገኘው ብድር መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለዚህ የባቡር መስመር ስዊስ ክሬዲት ባንክ ያፀደቀው 1.4 ቢሊዮን እንደሆነ፣ ፕሮጀክቱ ደግሞ የሚፈልገው 1.7 ቢሊዮን ዶላር በመሆኑ፣ ቀሪው 300 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የባቡር መስመሩ ከመቀሌ ወልዲያ በሰመራ በኩል አድርጐ ጂቡቲ ታጁራ ወደብ ድረስ የሚዘረጋው ፕሮጀክት አካል ነው፡፡

ቀደም ሲል የዚህ ፕሮጀክት አካል የሆነው የመቀሌ ወልዲያ ፕሮጀክት የቻይና ኩባንያ የሆነው ሲሲሲሲ ለመገንባት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል መግባቱ ይታወሳል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት የፋይናንስ ምንጭ የቻይና ኤግዚም ባንክ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ኩባንያዎች የፕሮጀክቱን ግንባታ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡  
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment