Friday, November 22, 2013

«አሜሪካ ግቢ» ሊፈርስ ነው

•በዚህ ዓመት 200 ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ ቤቶች ለመልሶ ልማት ይፈርሳሉ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመልሶ ማልማት ፕሮግራሙ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከታላቁ አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት በሚገኘውና «አሜሪካ ግቢ» ተብሎ በሚጠራው መንደር የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችንና ንግድ ቤቶችን ሊያፈርስ ነው፡፡

በዚህ አካባቢ ለመልሶ ልማቱ የሚፈርሰው ቦታም እስከ ጐርደሜ ወንዝ ድረስ ይዘልቃል ተብሏል፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር አስተባባሪነትና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፈጻሚነት ከማንኛውም ግንባታ ነፃ ሆኖ ለአዲስ ግንባታ ዝግጁ የሚሆነው 16 ሔክታር መሬት ነው፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ልማት ለሚያካሂደው የአካባቢ ልማት ፕሮግራም በአካባቢው እንዲለማ የታቀደው 23 ሔክታር መሬት ቢሆንም፣ 16 ሔክታሩ በአዲስ ከተማ፣ ሰባት ሔክታሩ ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኝ ነው፡፡ አራዳ ክፍለ ከተማ በይደር በርካታ የመልሶ ልማት ሥራዎች የሚጠብቁት በመሆኑ፣ ከጎርደሜ ወንዝ ባሻገር ያለው የአራዳ ክፍለ ከተማ ይዞታ ሥር የሚገኘው ቦታ በይደር ቆይቶ በሚቀጥለው ዓመት እንዲለማ ተወስኗል፡፡


አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመልሶ ማልማት ሲሰማራ ይህ የመጀመሪያው በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችንና ነጋዴዎችን ለማንሳት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቆሙት፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለመሠረተ ልማት ተቋማት ማለትም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ ለኢትዮ ቴሌኮምና ለአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን መሥመራቸውን እንዲያነሱ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢው ነዋሪዎችና የንግድ ተቋማት አካባቢው ለመልሶ ልማት ስለሚፈለግ ለውይይት ዝግጁ እንዲሆኑ ማስታወቁን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ማርቆስ አለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአካባቢው ልማት ጥናት መሠረት የተለያዩ የመኖሪያ፣ የንግድና የመዝናኛ ማዕከል ግንባታዎች በተቀናጀ መንገድ ይካሄዳሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተያዘው የበጀት ዓመት 200 ሔክታር መሬት የሚሸፍን የመልሶ ማልማት ሥራ ለማከናወን አቅዷል፡፡

የመልሶ ልማት የሚካሄድባቸው አካባቢዎች የተጎሳቆሉ፣ ለመኖሪያም ሆነ ለንግድ ሥራ ምቹ ያልሆኑና በመካከለኛው የከተማው ክፍሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ በከተማው አስተዳደር ትኩረት የተደረገበት አሜሪካ ግቢ በርካታ የንግድ ሥራ በተለይም የአልጋ ኪራይ፣ የመጋዘን ኪራይ፣ ወደ ዓረብ አገሮች የሚጓዙ ሴቶች ማቆያዎችና ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ነጋዴዎች የሚስተናገዱበት ስፍራ ነው፡፡ ይህ አካባቢ የመጀመሪያው የአሜሪካ አምባሳደር ያረፉበት በመሆኑ አሜሪካን ግቢ እየተባለ እንደሚጠራ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
http://www.ethiopianreporter.com