Monday, November 4, 2013

ድሬዳዋ በወረርሽኝ ሥጋት ላይ ነች በዚህ ወር ብቻ 2ሺ ህሙማን ተመዝግበዋል

የበሽታውን ምንነት ለማወቅ ናሙና ተልኮ ምርመራ እየተደረገ ነው፡፡
የድሬዳዋ ከተማ በጉንፋን መልክ በሚከሰት የበሽታ ወረርሽኝ ሥጋት ላይ ነች፡፡ በዚህ ወር ብቻ በበሽታው የተያዙ 2ሺ ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡
ከወባ ጋር ተመሣሣይነት አለው በተባለው በዚህ በሽታ የተያዙ ህሙማን፣ በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታልና በተለያዩ የከተማዋ ክሊኒኮችና የጤና ተቋማት ምርመራና ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡ በበሽታው ተይዘው ህይወታቸው ያለፈ ህሙማን እንዳሉ ምንጮች ቢጠቁሙም፤ የከተማው ጤና ቢሮ ለሞት የተዳረጉ ህሙማን መኖራቸውን አላውቅም ብሏል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሣሁን ኃ/ጊዮርጊስን ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ ችግሩ ወረርሽኝ በሚባል ደርጃ ተከስቷል ለማለት እንደማይቻልና ገና ስለሁኔታው ማጣራት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወቅቱ የወባ በሽታ የሚስፋፋበት ወቅት ከመሆኑ አንፃር በአካባቢው ጠበቅ ያለ ዝግጅትና ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሣሁን፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከወትሮው የተለየ ቁጥር ያላቸው ህሙማን መመዝገብ መቻላቸው ሁኔታውን ትኩረት እንድንሰጥበት አስገድዶናል ብለዋል፡፡
በዚህ ወር ብቻ 2ሺ ሰዎች መመዝገባቸውንም አቶ ካሣሁን ተናግረዋል፡፡ የበሽታውን ምንነትና የመተላለፊያ መንገዱን ለማወቅ ናሙናውን ወደ አዲስ አበባ የጤናና ሥነ-ምግብ ምርምር ኢንስቲቲዩት (ፓስተር) መላኩንና ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የበሽታው ምንነት ባልታወቀበት ሁኔታ ግን ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩም አቶ ካሳሁን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ሁኔታውን አስመልክቶ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በየዕለቱ ወደ ፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እየላኩ መሆናውን እና የበሽታውን ምንነትና የመተላለፊያ መንገዱን በቀጣዩ ሳምንት መረጃው ተጠናቆ እንደደረሳቸው ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ከሸንሌና ሔረር ተነስቶ ወደ ከተማዋ ተዛምቷል የሚል ጥርጣሬ ባሳደረው በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ የራስ ምታት፣ ማንቀጥቀጥና ነስር እንደሚታይባቸውና በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚታየው ከፍተኛ ሙቀት ለችግሩ መፍጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
http://addisadmassnews.com