ከሁለት ዓመት ወዲህ ብቅ ካሉ ወጣት ሴት አትሌቶች መካከል በውጤታማነት የምትጠቀሰው ቡዜ ድሪባ ናት፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በኢንተርናሽናል የመም መድረክ ላይ ብቅ ያለችው በ2004 ዓ.ም. በዱባይና በሞናኮ ከተሞች በተደረጉት የ1500 ሜትርና የ3000 ሜትር ሩጫ ውድድሮች ነው፡፡
ከመካከለኛ ርቀት ወደ ረዥም ርቀት 5000 ሜትር ለመሸጋገርም ጊዜ አልወሰደባትም፡፡ ሐቻምና በባርሴሎናው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና በ5000 ሜትር አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቋ ተተኪነቱን እንደምትይዝ ተስፋ ተጥሎባታል፡፡
ለዚህም አምና በተካሄደው የሞስኮው ዓለም ሻምፒዮና መሠረት ደፋር ባሸነፈችበት የ5000 ሜትር ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ ሆና በመቅረቧ አምስተኛነት ለመያዝ አስችሏታል፡፡ በዓለም ወጣቶች አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተጀመረው የሩጫዋ ጉዞ በዓለም ሻምፒዮናና በአህጉራዊ ውድድሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ለዘንድሮ ውድድሮች ከተመረጡትና ጥሪ ከተደረገላቸው አትሌቶች አንዷ ብትሆንም ልትገኝ አልቻለችም፡፡
ምክንያቱም ለቀረበላት የትዳር ጥያቄ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ከምትወደው ሩጫ ራሷን አርቃ ወላጆቿ ዘንድ መደበቅን መምረጧ ታላቅ ወንድሟ አቶ ገመቹ ድሪባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹በአገሪቱ በባህልም ሆነ በአኗኗር ሥርዓት ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ ሰው የወደዳትን አልያም የወደደችውን አግኝቶ መኖር የሚችለው በፍላጎትና ፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ ነው›› የሚሉት አቶ ገመቹ እህታቸው እየገጠማት ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው ይላሉ፡፡
ቡዜ የትዳር ጥያቄ እየቀረበላት ያለው በኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብና የብሔራዊ ቡድን የ5 ሺሕ እና 10 ሺሕ ሜትር ሩጫ አሠልጣኝ በሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ቶሌራ ዲንቃ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ገመቹ ይህም ጥያቄውን ፈቅዳና ወዳ ሳይሆን ተገዳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አትሌቷ በክለብ ታቅፋ መሮጥ የጀመረችው በአሰልጣኝ ቶሌራ በሚሠለጥኑ በቢሾፍቱ ከተማ ክለብ በመሆኑ ትውውቃቸው ከዚያ እንደሚነሳም ያወሳሉ፡፡ አያይዘውም ‹‹በወቅቱ ግለሰቡ የቢሾፍቱ ክለብ አሰልጣኝ ነበር፡፡ በመሀል እንደማንኛውም ሰው የፍቅር ግንኙነት ጀምረው ይሆናል፡፡ ይኼ ደግሞ አግባብ ባለው ሕግ የተደገፈ ባለመሆኑ ሕጋዊ ለማድረግ የግድ መፈቃቀድን ይጠይቃል፡፡ በዚሁ መሠረት ቡዜ ፈቃደኛ አለመሆኗን ብትገልጽለትም ግለሰቡ ግን እስካሁን ድረስ እየተከታተለና እያስፈራራ ሊያሠራት አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ ሕዝብና መንግሥት በሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነት በመመካት ከእሷም አልፎ እኔን ጨምሮ ቤተሰቦቿን ሊያስኖረን አልቻለም፤›› ብለዋል፡፡
የግለሰቡ ማስፈራሪያና ዛቻ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ ጉዳዩን ለቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር፣ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ለኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ በደብዳቤ እንደጠየቁ፣ ነገር ግን መፍትሔ እንዳላገኙም የአትሌቷ ወንድም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዘንድሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይፋ ካደረጋቸው ብሔራዊ አትሌቶች ቡዜ አንዷ ብትሆንም ካለፍላጎቷ የትዳር ጥያቄ የሚያቀርብላት ግለሰብ የአምስትና አሥር ሺሕ ሜትር አሰልጣኝ በመሆኑ ልምምዷን በአግባቡ እንዳትሠራ ጫና እያደረገባት ነው፡፡ ይህንኑም ለፌዴሬሽኑ ደግመን ደጋግመን አቅርበናል፡፡ በግለሰቡም ላይ ተገቢውን የዲሲፕሊን ዕርምጃ እንዲወሰድና እሷም ወደ ዝግጅቷ እንድትመለስ ብንጠይቅም የሚሰማን ግን አላገኘንም፤›› ብለዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ፖሊስና የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዋና ኢንስፔክተር ቶሌራ ዲንቃ በበኩላቸው፣ ከአትሌቷ ጋር ባልና ሚስት ሆነን በአንድ ቤት ከሦስት ዓመት በላይ መቆየታችን መላው የአትሌቲክስ ቤተሰቡም ሆነ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የሚያውቀው የአደባባይ ምስጢር ነው ይላሉ፡፡
አትሌቷ ዛሬ ለደረሰችበት ከመብቃቷ በፊት በ2002 የውድድር ዓመት ለቢሸፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ክለብ ገብታ ያላትን ክሕሎት እንድታሳይ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዳደረጉላትና ከዚያም ከ800 ሜትር ጀምሮ አሁን ውጤታማ እስከሆነችበት አምስት ሺሕ ሜትር ያደረጉላትን ድጋፍ ተከትሎ ሁለታቸውም በመፈቃቀድ ፍቅር ጀምረው አብረው መኖር መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹አስገድዷት ነው›› ለሚለው ለአቶ ገመቹ ጥቆማ ዋና ኢንስፔክተሩ፣ ‹‹የፖሊስ ሠራዊት አባል ነኝ፡፡ ሕጉን በሚገባ አውቃለሁ፡፡ እንኳን ትልቅ ደረጃ ለደረሰች አትሌት ይቅርና ማንም ሰው ከፍላጎቱ ውጪ ተገዶ የትዳር ጓደኛ ሊይዝ እንደማይችልም ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ወዳኝ ወድጃት በአንድ ቤት ከሦስት ዓመት በላይ ተቀምጥናል፡፡ የእሷና የእኔ ቤተሰቦች የሚያውቁት እውነት ነው፡፡ ለዚህ ውሳኔ ያበቃትን ባላውቅም ቤቷን ለቃ እስከሄደችበት ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት ንግግርም ሆነ ግጭት የለንም፡፡ ሁለታችንን በቅርበት ለሚያውቁ ጉዳዩን አስረድቼ በሽምግልና እንዲፈታ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ነገር ግን መፍትሔ ሊመጣ ግን አልቻለም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ለአትሌቷ ውሳኔ ምክንያት የሆነው ወንድሟ ነው፡፡ ከእሱ ጋር ለጊዜው ምክንያቱን ባልገልጸውም የተጣላንበት አጋጣሚ አለ፡፡ እያስፈራራ ለሚለው ግን፣ ከሕፃንነቷ ጀምሮ ለትልቅ ደረጃ ያበቃኋትን መናገር ቀርቶ ሌላ ሰው እንኳ እንዲናገራት አልፈቅድም፡፡ አሁንም ከጀርባዋ ሌላ ነገር ስላለ እንጅ ቡዜ በእኔ የምትከፋ ልጅ እንዳልሆነች እሷም እኔም እናውቃለን፤›› የሚሉት ዋና ኢንስፔክተሩ፣ መፍትሔውን አስመልክቶ ላቀረብነው ጥያቄ ‹‹ያ የእኔና የእሷ ውሳኔ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የአትሌቷ ወንድም ሕጋዊ ጋብቻ የላቸውም ብለው ላነሱት ነጥብም የተናገሩት አለ፡፡ ‹‹ሕጋዊ የጋብቻ ውል ባይኖረንም፣ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ አብረን እየኖርን ስለመሆኑ የማያውቅ የለም፡፡ ለሁለታችን መለያየት ሌት ከቀን የሚንቀሳቀሱ የፈጠሩት ተንኮል አለ፡፡ ቡዜ አሁንም ረጋ ብላ እንድታስብ ዕድሉ አላት፡፡ ከቤት ወጥታ የሄደችው በሌለሁበት ነው፡፡ ይኼ በራሱ በሕግ ፊት አያስኬድም፡፡››
የአትሌቷ ወንድም ‹‹አብሮ ለመኖር መፈቃቀድን ይፈልጋል›› ለሚለው አስተያየታቸውም፣ ‹‹አትሌቷን ከልጅነቷ ጀምሮ በባዶ እግሯ አምጥቼ ለትልቅ ደረጃ በማድረሴ ይኼ ሁሉ ነገር ይደርስብኛል የሚል እምነት ስለሌለኝ የቃላት ስንጠቃ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ማረጋገጥ የምችለው እኔና ቡዜ በመካከላችን ምንም ዓይነት አስገዳጅ ነገር ሳይኖር ከሦስት ዓመት በላይ በአንድ ቤት ኖረናል፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ይህም ለእሷም ሆነ ለቤተሰቦቿ ይጠፋቸዋል ብዬ አላስብም፤›› ብለዋል፡፡
አትሌት ቡዜ እየደረሰባት ባለው ማስፈራራትና ዛቻ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ለብሔራዊ ቡድን ብትጠራም፣ ያለመገኘቷ ሰበብ አሠልጣኙ ነው ለሚለው የወንድምየው አገላለጽንም አጣጥለውታል፡፡ ‹‹ደግሜ ደጋግሜ ማረጋገጥ የምችለው እኔና ቡዜ ከሁለት አንዳችን በውስጣችን የመፈቃቀድ አመለካከት ባይኖር ኖሮ ይህን ያህል ዓመት አብረን ባልኖርን ነበር፡፡ እርግጠኛ ነኝ ውሳኔው የእሷ አይደለም፡፡ ማስፈራራት ስለሚባለው አስፈራርቻት አላውቅም፣ አላደርገውምም፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዳለ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ብሔራዊ ስለተባለው ጉዳይ እኔን አይመለከትም፡፡ የእኔ ድርሻ የቀረበልኝን አትሌት ማሠልጠን ነው፡፡››
አሠልጣኙ አስረግጠው እንደሚናገሩት፣ ቡዜ ‹‹የእኔ ሚስት እኔም ባሏ ስለመሆኔ በትልልቅ የሽልማት መድረኮች ላይ ሁለት ጊዜ የመኪና ሽልማት ሲሰጣት በሥነ ሥርዓቱ ታድሜያለሁ፡፡ የውጪ ማናጀሮች ሳይቀር የሚያውቁት ይህንኑ ነው፤›› ሲሉም የግንኙነታቸውን መጠን ያጠናክራሉ፡፡
በአትሌቷና በአሰልጣኙ መካከል የተፈጠረውንና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቀረበለትን አቤቱታ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ብልልኝ መቆያ የመለሱት ‹‹የግለሰቦች የግል ጉዳይ በፌዴሬሽኑ እንደማይፈታ›› በመግለጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አትሌቷ የብሔራዊ ቡድን ተመራጭ በመሆኗ በዝግጅት ላይ እያለች ለሚደርስባት ማናቸውም ነገሮች ግን ተቋሙ የሚመለከተው ከሆነ አትሌቷ ቀርባ ለማስረዳት ፈቃደኛ ከሆነች እንደሚታይላትም ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸው፣ ‹‹አትሌቷ ደርሶብኛል ስለምትለው ማስፈራራትና ዛቻ ቀርባ ሪፖርት አላደረገችም፡፡ ችግሩን አስመልክቶ ጥያቄው ለፌዴሬሽኑ የቀረበው በወንድሟ በኩል ነው፡፡ ነገር ግን አትሌቷ ቀርባ እውነትም እየደረሰባት ያለው ማስፈራራትና ዛቻ ለፌዴሬሽኑ አቅርባ ፌዴሬሽኑም የሚመለከተው ከሆነ ውሳኔ የማይሰጥበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም አትሌቷን ተቋሙም ሆነ አገሪቱ የሚፈልጓት ነች፡፡ ወጣት አትሌትም ነች፡፡ መታየት ያለበት ግን ምን ዓይነት የዲሲፕሊን ችግር ነው በፌዴሬሽኑ በኩል መፍትሔ የሚያገኘው የሚለው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሪፖርተር አትሌት ቡዜ አስተያየትዋን እንድትሰጥ በስልክ በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ከከተማ ውጭ በመሆኗ ለማግኘት አልተቻለም፡፡
No comments:
Post a Comment