Monday, December 16, 2013

መድረክ ለምርጫ 2007 ለኢሕአዴግ የእንደራደር ጥያቄ አቀረበ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ምርጫ 2007 ከመድረሱ በፊት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለመክፈት ከኢሕአዴግ ጋር መደራደር እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡ መድረክ ባለፈው ዓርብ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰበት በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

የመድረክ አመራሮች ኢሕአዴግ ምርጫ 97ን ተከትሎ የወሰዳቸው የአፈና ዕርምጃዎችና የፀደቁ አዋጆች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው፣ ኢሕአዴግ በዲሞክራሲያዊ ትግል የሚያምኑ ተቃዋሚዎች ወደሌላ የማይፈለግ አቅጣጫ እየገፋቸው ይገኛል ብለዋል፡፡

የግንባሩ የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ በአንድ ቡድን ቁጥጥር ሥር በወደቀ ቁጥር፣ የማይፈለግ ውጤት ማስከተሉ አየቀርም ብለዋል፡፡ ኢሕአዴግ ለምርጫ 2007 በተለያዩ አካባቢዎች ቅስቀሳ መጀመሩን የገለጹት ዶ/ር መረራ፣ በተለይ ‘አንድ ለአምስት’ የሚባለውን አደረጃጀት በመጠቀም ኅብረተሰቡን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ አካሄዱ ከዲሞክራሲያዊ ምርጫ መርህ የሚቃረን መሆኑን በማስረዳት፡፡ መንግሥት በድርጅቱ አባላት ላይ የማሰርና የአፈና ዕርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ገልጸው፣ ድርጅታቸው በዚህ ተስፋ እንደማይቆርጥ አስታውቀዋል፡፡


መድረክ በዚሁ መግለጫው ትኩረት የሰጠው ሌላ ጉዳይ በሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተፈጸመ የተባለውን ግፍ በተመለከተ ሲሆን፣ ተጠያቂው ደግሞ መንግሥት መሆኑን ገልጿል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ ዜጎች እዚህ አገር ሥራና መፈናፈኛ አጥተው የመጨረሻ አማራጭ በመውሰዳቸው ተጠያቂው መንግሥት ነው ብለዋል የመድረክ አመራሮች፡፡ ‹‹በሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመው ግፍ ብሔራዊ ውርደት ነው፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ መንግሥት ለዜጎቹ ግድ የለሽ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው የመድረክ አመራር አባል አቶ አስራት ጣሴ መድረክ በተደጋጋሚ ያቀረበው ሠልፍ የማድረግ ጥያቄ መታፈኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፓርቲው የመጨረሻ ዕርምጃ ምን ይሆናል?›› በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹በመጨረሻ የምናደርገው እምቢታ ነው፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት አልፈቅድ ካላቸው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ደጋፊዎቻቸውን ሠልፍ እንደሚጠሩ አስታውቀዋል፡፡

በአገሪቱ በ‘አንድ ለአምስት’ አደረጃጀትና በሌሎች መንገዶች እየተካሄደ ያለው አፈና መቆም እንዳለበት የገለጸው መድረክ፣ በተለይ ምርጫ 2007ን በተመለከተ ከወዲሁ ከኢሕአዴግ ጋር መደራደር እንደሚፈልግ ገልጾ፣ ይህ የማይሳካ ከሆነ ግን የአገሪቱ ዲሞክራሲ ከድጡ ወደ ማጡ ይገባል ብሏል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment