Monday, December 23, 2013

አሠልጣኝ ሰውነት የቻን ቡድናቸውን አሳወቁ -አበባው ቡጣቆና ሲሳይ ባንጫ አልተካተቱም

-የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝርዝርም ይፋ ሆኗል

በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በይፋ ይጀመራል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው የተጨዋቾቻቸውን ዝርዝር ይፋ አድርገዋል፡፡ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ከሁለት ዓመት በላይ ቆይታ ካላቸው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አበባው ቡጣቆና የደደቢቱ ሲሳይ ባንጫ በምርጫው አልተካተቱም፡፡

በዋና አሠልጣኙ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ተጨዋቾች ከቅዱስ ጊዮርጊስ አሉላ ግርማ፣ ሳላዲን ቤርጌቾ፣ ደጉ ደበበ፣ ምንያህል ተሾመ፣ አዳነ ግርማ፣ ኡመድ ኡክሪ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስና ምንተስኖት አዳነ ሲሆኑ፣ ከደደቢት ታሪኩ ጌትነት፣ ሥዩም ተስፋዬ፣ ብርሃኑ ቦጋለ፣ ታደለ መንገሻ፣ ሽመክት ጉግሳ ናቸው፡፡


ከኢትዮጵያ ቡና ጀማል ጣሰው፣ ቶክ ጅምስ፣ ኤፍሬም አሻሞና ፋሲካ አስፋው ሲሆኑ፣ ከዳሸን ቢራ ደረጀ ዓለሙ፣ ዓይናለም ኃይሉ፣ አስራት መገርሳ፣ ከአርባ ምንጭ ገብረ ሚካኤል ያዕቆብና ሙሉዓለም ያዕቆብ፣ ከመከላከያ ማናዬ ፋንቱ፣ ከንግድ ባንክ መሐሪ መናና ከሲዳማ ቡና ሞገስ ታደሰ መሆናቸው ታውቋል፡፡ አበባውና ሲሳይ በዲሲፕሊን ምክንያት አለመካተታቸውም ታውቋል፡፡

ከሊቢያ፣ ኮንጐ ብራዛቪልና ጋና ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን ጨዋታ ጥር 5 ቀን፣ ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ጥር 9 ቀን እና የመጨረሻውን የምድብ ድልድል ጨዋታ ጥር 12 ቀን እንደሚያከናውንም የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአሠልጣኝ ሰውነት የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማምራቱ በፊት የሚያደርገውን አጠቃላይ ዝግጅትና ተያያዥ መረጃዎችን በተመለከተ ከዋና አሠልጣኙም ሆነ ከፌዴሬሽኑ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ምንም ዓይነት የተሰጠ ማብራርያ የለም፡፡ ከዚህም በላይ በኬንያ አስተናጋጅነት በተከናወነው የምሥራቅና መካከለኛ አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) እግር ኳስ ዋንጫ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ውድድሩን አጠናቆ አገሩ ከገባ በኋላ ቡድኑ የነበረው ጠንካራና ደካማ ጐን ምን እንደሚመስል አልተገመገመም፡፡ ይኼ ባልሆነበት ደግሞ ለቻን እንዲዘጋጅ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውና ቡድናቸው እንዲገመገም የሚጠይቅ አካል ስለመጥፋቱም እኚሁ አመራር ይተቻሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ሉሲ) በ2007 ዓ.ም. ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት የተመረጡ ተጨዋቾች ዝርዝር ታውቋል፡፡

የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አቶ ሥዩም ከበደ ሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለዝግጅቱ ጥሪ የተደረገላቸው ተጨዋቾች ከደደቢት ሊያ ሽብሩ፣ መስከረም ኮንታ፣ ትበይን መስፍን፣ ኤደን ሽፈራው፣ ቅድስት ቦጋለ፣ ብሩክታዊት ግርማና ሰናይት ቦጋለ ሲሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ንግስቲ መዓዛ፣ ብዙሐን እንዳለ፣ ሕይወት ዴንጌሶ፣ አትክልት አሸናፊ፣ አዳነች ጌታቸው፣ ጥሩአንች መንገሻ፣ ዙሊካ ጅሃድ፣ ሽታዬ ሲሳይ፣ ረሒማ ዘርጋውና ብዙነሽ ሲሳይ ናቸው፡፡ ከሁለቱ ክለቦች በተጨማሪ ከመከላከያ ዮዲት ጌታቸው፣ ከዳሸን ቢራ ማርታ በቀለ፣ ብርቱካን ገብረ ክርስቶስና ቱቱ በላይ፣ ከሐዋሳ ከነማ ዙላ አበራ፣ ከቅድስት ማርያም መዲና አወል መሆናቸው ታውቋል፡፡

እንደ ዋና አሠልጣኙ ገለጻ፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከነገ በስቲያ ጀምሮ ዝግጅት ይጀምራል፡፡ የግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሐሳቡን ካልቀየረ ታኅሣሥ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ካይሮ አምርተው የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. በናምቢያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ለመካፈል ሉሲዎቹ የመጀመርያውን ማጣርያ የካቲት 6 ቀን ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ጋር በአዲሰ አበባ ስታዲየም ተጫውተው፣ በደርሶ መልሱ ጨዋታ አሸናፊ መሆን ከቻሉ የመጨረሻውን ማጣሪያ ደግሞ ከጋናና ቡርኪና ፋሶ አሸናፊ ጋር በግንቦት ወር ይጫወታሉ፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment