Wednesday, December 11, 2013

በዲዛይን ለውጥ ለባቡር መስመር የተገነባ የኮንክሪት ግንባታ ፈረሰ



Ethiopian Reporter 
በአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚዘረጋው የባቡር መስመር የመጨረሻ መዳረሻ ቃሊቲ አደባባይ አካባቢ፣ ለባቡር መስመሩ የተገነባ ከአንድ መቶ ሜትር በላይ የሚገመት ግንባታ እንዲፈርስ ተደረገ፡፡

ቃሊቲ አደባባይ አካባቢ ለቀላል ባቡሩ መስመር ዝርጋታ ዳርና ዳር ተሠርቶ የነበረው ይህ ኮንክሪት እንዲፈርስ የተደረገው በዲዛይን ለውጥ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓርብ ጀምሮ እስከ እሑድ ድረስ በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች በመታገዝ ጭምር ሲፈርስ የነበረውና ከተገነባ የወራት ዕድሜ ያለው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ክፍል ጥልቅ መሠረት እንዲይዝ ተደርጐ የተሠራው ይህ ግንባታ ቀላል የማይባል ወጪ የወጣበት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ድንገት እንዲፈርስ በመደረጉ ብዙዎችን አስደምሟል፡፡

ጉዳዩን በማስመልከት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ኃላፊ ኢንጂነር በኃይሉ ስንታየሁ እንደገለጹት፣ በቃሊቲ አካባቢ ከተገነባ በኋላ ኮንክሪቱ እንዲፈርስ የተደረገው መጠነኛ የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ ነው፡፡


በግንባታ ፕሮጀክት እንዲህ ዓይነት የዲዛይን ለውጥ የሚያጋጥም እንደሆነ የገለጹት ኢንጂነር በኃይሉ፣ 34 ኪሎ ሜትር ርዝመት ካለው ፕሮጀክት አንፃር ሲታይ የፈረሰው አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

የዲዛይን ለውጥ በማስፈለጉ በተወሰደው የማፍረስ ዕርምጃ ኃላፊነት የሚወስደው ጥቅል ፕሮጀክቱን ሥራ የተረከበው የቻይናው ኩባንያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር በኃይሉ ገለጻ ፕሮጀክቱ ‹‹ኮንትራት ተርንኪ›› (ከዲዛይን ጀምሮ ለግንባታ የሚሆነውን ግብዓት በማቅረብና ሙሉ ግንባታውን በማካሄድ ማስረከብ) በመሆኑ፣ ለሥራው አመቺ በሆነ መንገድ ዲዛይኑን ለመለወጥ ሥራውን የማከናወን ኃላፊነት የቻይናው ኩባንያ ነው፡፡ የፈረሰውንም ግንባታ የሚያስወጣው ወጪ ካለ ታሳቢ የሚደረገው የፕሮጀክቱን ሥራ በተረከበው ኮንትራክተር ላይ ነው ብለዋል፡፡

አንዳንዴ የዲዛይን ለውጥ ሲደረግና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ኃላፊነት የሚወስደው ይኼው ኮንትራክተር እንደሆነ ጠቁመው፣ በመንግሥት ወጪ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ የቀላል የባቡር ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደሚጠናቀቅና በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ ሥራው መገባደዱ ይታወቃል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚዘረጋው መስመር የደቡብ ክፍሉ የባቡሩ መድረሻና መነሻ ጣቢያ ቃሊቲ ከኮሜት ትራንስፖርት ይዞታ ጐን ግንባታው መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ በሚዘረጋው መስመርም ሃያት አካባቢ የመነሻና የመድረሻ ጣቢያ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ኢንጂነር በኃይሉ አስረድተዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment