Wednesday, November 28, 2012

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ አውሮፕላን ውስጥ ተደብቆ ጀርመን ገባ


በኢትዮጵያ አየር መንገድ ‹‹ግራውንድ ሃንድሊንግ›› ዲፓርትመንት ውስጥ በሻንጣ ጫኝና አውራጅነት ሲሠራ የቆየ አንድ ሠራተኛ ሰሞኑን አውሮፕላን ውስጥ ተደብቆ ጀርመን መግባቱ ታወቀ፡፡ ለጊዜው ስሙ ያልታወቀው የ24 ዓመት ወጣት የሆነው ግለሰብ፣ ህዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም. የተሳፋሪዎችን ሻንጣና ሌሎች ቁሳቁሶችን በአውሮፕላኑ ሆድ ውስጥ ከሚገኘው የጭነት ክፍል ውስጥ ካስገባ በኋላ እዚያው ተደብቆ ቀርቷል፡፡

በመሆኑም ግለሰቡ ከዕይታ ውጭ ሆኖ አውሮፕላኑ ጉዞውን ከአዲስ አበባ ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት ያደርጋል፡፡



ከዘጠኝ ሰዓታት በረራ በኋላ አውሮፕላኑ ፍራንክፈርት አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በጀርመን ፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ወደ አገሩም ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለበት የኢኮኖሚ ችግር የተነሳ መኖር እንደማይችል፣ ቢመለስ ደግሞ ለባሰ ችግር እንደሚጋለጥ በመጥቀስ ጥገኝነት ጠይቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአውሮፕላን ማረፊያው ትራንዚት ተርሚናል ውስጥ በመሆን ላቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በወቅቱ በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ የነበሩ የፀጥታ ሠራተኞች ላሳዩት ቸልተኝነት አየር መንገዱ ጥያቄ ያቀረበባቸው መሆኑን ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ ከአየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ የጀርመን መገናኛ ብዙኅን በጉዳዩ ላይ ሰሞኑን ተመሳሳይ ዘገባዎችን አውጥተዋል፡፡

ከዚህ ቀደምም እ.ኤ.አ. በ2009 አንድ የአየር መንገዱ ሠራተኛ ወደ አሜሪካ ተደብቆ መሄዱ ይታወሳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment