Sunday, November 18, 2012

የዓድዋ ፊልም በ35 ሚሊዮን ብር በጀት ሊሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ፕሮጀክቱን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በበላይ ጠባቂነት ይዘውታል፡፡

መራሔ ተውኔት አባተ መኩሪያ 

-    አሉ የሚባሉ የአገሪቱ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል

በጥበበሥላሴ ጥጋቡ

ታሪካዊውን የዓድዋ ድል የሚተርክ ፊልም 35 ሚሊዮን ብር በሚገመት በጀት ሊሠራ ነው፡፡ በመራሔ ተውኔት አባተ መኩሪያ የተጻፈው ፊልም ፕሮጀክትን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በበላይ ጠባቂነት ይዘውታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የታሪክ አቅጣጫውን እንዳይስትና ነባራዊ ሁኔታንም ፊልሙ ውስጥ ለማካተት የታሪክ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴንም ለማካተት በድርድር ላይ መሆኑን የፊልሙ ፕሮዲውሰር ማሳ ኮሙዩኒኬሽንና ኤቨንትስ አክሲዮን ማኅበር አስታውቋል፡፡

የማኅበሩ ዳይሬክተር አቶ ዓባይነህ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ፊልም ላይ የተለያዩ ባለሙያዎች ከአገር ውስጥ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚሳተፉበት ሲሆን እንዲሁም ከታዋቂው የህንድ ፊልም ኢንዱስትሪ ቦሊውድ የሚመጡ የፊልም ባለሙያዎችንም ለማሳተፍ ጫፍ ላይ ደርሰዋል፡፡35 ሚሊዮን ብር በጀት የሚያዝለት ዓድዋ ፊልም በባለሙያዎች መገምገሙንና በጀቱን ለማግኘት አቅጣጫ መቀየሱን ያወሱት ዳይሬክተሩ፣ አንዱ መንገድ የአክሲዮን ሽያጭ መሆኑን ሥራውም የአንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን ከማኅበረሰቡም  ገቢ ሊገኝ እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምን ያህል አክሲዮን እንደሚሸጥ ገና ያልተወሰነ ሲሆን የሚወሰነውም በፕሮጀክቱ አካሔድ እንደሚሆን አቶ አባይነህ አስታውቀዋል፡፡ ስም ለመጥራት ጊዜው ገና ቢሆንም የተለያዩ አካላት ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

አግባብ ባለው መንገድም እንዲጓዝና ይዘቱን እንዳይለቅ ጥንቃቄ ስለሚያስፈልገው ከዚህ በፊት በርካታ ቴአትሮችን የዓድዋን ትርኢት ጨምሮ በማዘጋጀት የሚታወቁት አባተ መኩሪያ ለዚህ ሥራ ዋነኛውና ቁልፍ ሰው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮጀክቱ አሁን ባለበት ደረጃ ድርሰቱ መጠናቀቁና ወደ ቀረጻው ከመገባቱ በፊት ግን ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች ይጠናቀቃሉ፡፡ በጽሑፍ ሥራው ላይ ከአባተ መኩሪያ በተጨማሪ የተለያዩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተባብረውበታል፡፡

የፊልሙ ታሪክ የትኛው የዓድዋ ክፍል ላይ እንደሚያተኩር ባለሙያዎች እንዳልተወያዩበትና ዋና ገጸ ባሕሪ ማን ሊሆን እንደሚችልም አልታወቀም፡፡ ታሪኩ የተፈጸመበት ዓድዋና አዲስ አበባን በሚያካትተው ፊልም ላይ ከአምስት ሺሕ በላይ ተዋናዮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹በ35 ሚሜ ፎርማት የሚሠራው ዓድዋ ፊልም የተለያዩ አካላትን ጥምረት ይጠይቃል፡፡ ብዙ ባለሙያዎችም ይሳተፉበታልም ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በፊልም አንቱታ ያገኙት ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ናቸው፡፡ በዚህ ሥራ እንዲተባበሩን ጥሪ አድርገናል፡፡ ፍጻሜው ግን ገና አልታወቀም፤›› ብለዋል፡፡

የዓድዋ ፊልም ደራሲው መራሔ ተውኔት አባተ መኩሪያ በሀገር ፍቅር ቴአትር፣ በብሔራዊ ቴአትርና በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የቴአትርና ባህል አዳራሽ በአዘጋጅነት ካቀረባቸው አያሌ የሙሉ ጊዜ ተውኔቶች መካከል በኢትዮጵያ ታሪክ ሁነኛ ስፍራ ያላቸው ‹‹ቴዎድሮስ›› እና ‹‹አሉላ አባነጋ›› ይገኙበታል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከ26 ዓመት በፊት በእቴጌ ጣይቱና በዳግማዊ ምኒልክ የተመሠረተችበትን 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓሏን ስታከብር የዓድዋ ዘመቻ ክተትን የሚያሳይ ትውፊታዊና አስደናቂ ትርኢት በዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ ማሳየታቸውም ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ዝና ያበቃትን የዓድዋ ድል በወራሪው የኢጣልያ ሠራዊት ላይ ያስመዘገበችው በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል፡፡ (ለዚህ ዜና ሔኖክ ያሬድ አስተዋጽዖ አድርጓል)
http://www.ethiopianreporter.com/