Friday, November 23, 2012

በአሥር ዓመቷ ብላቴና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ‹‹የአባቴን ፍቱልኝ›› የተማፅኖ ግጥም አንድምታው ምን ይሆን?


በፍቅር ለይኩን

በታሪካዊው፣ የአፍሪካ ሕዝቦች ሥልጣኔ መሠረትና ሕያው የዘመናት አሻራ በሆነው በታላቁ ወንዛችን በዓባይ ላይ በመገንባት ላይ ያለውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተመለከተ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ ምስጋናና የማበረታቻ ሽልማት ለመስጠት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በሚሊንየም አዳራሽ በጠራው ደማቅ ዝግጅት ላይ ለመገኘት ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ የውበት ካባን በእጥፍ የደረቡ የሚመስሉ፣ ከአገርኛው ቋንቋ ይልቅ አውሮፓዊው ቋንቋ የሚቀናቸው እንስቶችና ወጣቶችን በብዛት ታስተናግድ የነበረችው ቦሌ፣ ያውም በቅዳሜ ዕለት ፈርሶ እየተሠራ ባለው መንገዷ ምክንያት የቆንጆዎች ድርቅ እንደመታት ታዘብኩ፡፡ ቦሌና ቦሌዎች ግድየለም ነገም ሌላ ቀን ነው፣ የቀደመው ውበታችሁና ክብራችሁ በእጥፍ ይመለስላችኋል አልኩ በውስጤ፡፡

የውቦችና የኢትዮጵያዊ ኩራት መገለጫ የሆነው የአየር መንገዳችን መናኸሪያ ውቧ ቦሌን ‹‹አይዞን!›› በማለት ማጽናናት በሚመስል አኳኋንና ትዝብት የትናንትናዋን በዓይነ ኅሊናዬ እያመላለስኩ፣ አቧራና ፍርስራሽ ከዋጠው መንገድ ፊት ለፊት ወደሚገኘው የሚሊንየም አዳራሽ በዝግታ አመራሁ፡፡በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማችንና እንዲሁም በህዳሴው ግድብ ምሥል ያሸበረቀውን የጥሪ ካርድ በማሳየት ወደ አዳራሹ ቅጥር ግቢ ገባሁ፡፡ ወደ ዋናው አዳራሽ ለመግባት ያለውን ጥብቅ የሆነ በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘውን ፍተሻ አልፌ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ፡፡ ‹‹ዓባይ፣ ዓባይ፣ ዓባይ ወንዛ ወንዙ…›› የሚለውን የእውቋንና በእጅጉ የማደንቃትን የባለ ቅኔዋንና የድምፀ ሸጋዋን የእጅጋየሁ ሽባባውን (የጂጂን) ውብ ዜማ በኅሊናዬ እያመላለስኩና በለሆሳስ እያንጎረጎርኩ ነበር፡፡

በአዳራሹ መግቢያ ግራና ቀኝ በአገር ባህል ልብስ የደመቁና ውብ ፈገግታን በሚረጩ የአገሬ ቆነጃጅት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበልና ድንቅ የአበባ ስጦታ በምስጋና ተቀብዬ ወደፊት አመራሁ፡፡ ወደ ዋናው አዳራሽ መግቢያ በስተቀኝ በኩል በታላቁ ወንዛችን በዓባይ ላይ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚገነባውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያሳዩ መጠነኛ የፎቶግራፍ ትዕይንቶችን ዞር ዞር ብዬ ከተመለከትኩ በኋላ ወደ አዳራሹ በመግባት መቀመጫ ያዝኩ፡፡ አዳራሹ ቀስ በቀስ በሰው ተሞላ፡፡ የሃይማኖት መሪዎችና ተወካዮች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የየክልሉ ርእሰ መስተዳድሮች፣ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ሰዎች አዳራሹን ግጥም አደረጉት፡፡

የፕሮግራሙን መጀመር ለአንድ ሰዓት ያህል ዘግይቶ የዕለቱ የክብር እንግዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ደሳለኝ ኃይለ ማርያም፣ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአዳራሹ ከታደሙ በኋላ ዝግጅቱ በይፋ መጀመሩ ተበሰረ፡፡

በዕለቱ የዝግጅቱ የመድረክ መሪዎች ዓባይ ወንዛችንን ከኢትዮጵያዊ ክብር፣ ነፃነት፣ አንድነት፣ ማንነትና ኩራት አፍሪካንና አፍሪካውያንን እንዲሁም መላውን የጥቁር ዘር ሕዝቦችን ሁሉ ወኔ፣ ክብርና ታላቅነት ከፍ ካደረገው የዓድዋ ድል ጋር በማነፃጸር ያቀረቡት መነባንብ መሰል ቀስቃሽ ገለጻ የሕዝቡን ስሜት በእጅጉ ቆንጥጦ የያዘ ነበር፡፡

ይህ መድረክ አዳራሹን በኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ክብርና ከፍተኛ ስሜት የሞላ፣ ኢትዮጵያዊነት በሺሕ ዘመናት የታሪክ፣ የጀግንነትና የነፃነት ክብር የደመቀ፣ ኢትዮጵያዊነት የቀደሙ አባቶቻችን ዘር፣ ሃይማኖት፣ ወንድ፣ ሴት፣ ወዘተ ሳይሉ በከፈሉት ታላቅ የደም መስዋዕትነት ውብ ሆኖ የተሸመነ የአንድነትና የኩራት ጥበብ ምንጭ መሆኑ የተገለጸበት ነበር፡፡

የኢትዮጵያዊነትን ታላቅ ክብርና ብሔራዊ ኩራት ያደመነውን ለዘመናት የተጫነን የድህነት ቀንበር ለመስበር ኢትዮጵያውያን ለጋራ ጥቅም ክንዳቸውን በዓባይ ላይ የሚያሳዩበትን ታሪክ ሠርተው ለቀጣዩ ትውልድ ሕያው የሆነ አሻራ የሚያቆዩበት ታላቅ የታሪክ አጋጣሚ እንደሆነ ነበር በመድረኩ ላይ የተነገረው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ንግግርም ይህንን እውነታ የሚያጠናክር ነበር፡፡

በዚህ በቅዳሜ ምሽት በሚሊንየም አዳራሽ በተደረገው ዝግጅት ላይ ለሁለት ተከታታይ ሰዓታት በላይ ከቀረቡት ዝግጀቶች መካከል በእጅጉ ልቤን የነካኝ በግምት ዕድሜዋ አሥር ዓመት የሚሆናት ከመካኒሳ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት የመጣች ታዳጊ ሕፃን፣ ‹‹ዓባይ የት ነበረ?›› በሚል እጅግ በሚመስጥ የድምፅ ቅላፄና የሰውነት እንቅስቃሴ ጋር ያቀረበችው ግጥም አንዱ ነበር፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ዋንኛ ምክንያት የሆነኝ የዚህች ታዳጊ ሕፃን ከዓባይ የት ነበረ ግጥሟ አስከትላ፣ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበችው ስሜት ኮርኳሪና በእጅጉ አንጀትን የሚያላውስው ግጥሟ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ታዳጊዋ በቅድሚያ ባቀረበችው ግጥሟ በዓባይ ላይ የተጀመረውን የታላቁን የህዳሴውን ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በፍቅር ክንዱን አስተባብሮ ድህነት ታሪክ ለማድረግ ተባብረን መሥራት እንደሚያስፈልገን የገለጸችበትን ግጥም አቅርባ ከጨረሰች በኋላ፣ ‹‹አሁን ደግሞ›› አለች ያች ታናሽ ብላቴና በሚኮላተፍና በጣፋጭ አንደበቷ፡፡ ‹‹አሁን ደግሞ ይህን ግጥም የማቀርበው ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ነው›› ስትል፣ አዳራሹን የሞላው ሕዝብ በግርምትና ምን ልትላቸው ይሆን በሚል ጉጉት ዓይኑን ወደ ልጅቱና ግጥም ሊበረከትላቸው ወዳሉት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ የሁሉም ዓይኖች ተፈተለኩ፡፡

በራስ የመተማመን መንፈስ፣ ከሕፃንነት ንፁህ ልብ ከሚመነጭ ፍቅር፣ ርኅራኄንና ምሕረትን በሚጠይቁ ዓይኖቿ አንዴ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን አንዴ ደግሞ ሕዝቡን እየቃኘች በቦሌው የሚሊንየም መድረክ ‹‹የምሕረት ያለህ! የይቅርታ ያለህ! አባቴን አስፈቱልኝ/ፍቱልኝ… እባክዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር…›› በሚል ተማፅኖ መድረኩን የተቆጣጠረችው ሕፃን፣ ‹‹ይህ ግጥም እውነተኛ ታሪክ ነው፣ ግጥሙ ከእውነተኛ ታሪኬ በመነሳት የጻፍኩት ነው፤›› በማለት ምሽቱን በዓባይ ልማት ላይ ስናወራ በአንድነት የሚያስተሳስረን የፍቅርና የእርቅ ልማት በኢትዮጵያችን ይቅደም፣ ይምጣ፣ አሁን ይሁን… በሚል ስሜት በአዳራሹ ውስጥ የፍቅርንና የእርቅን አዋጅ አወጀችበት፡፡ መድረኩ ለአፍታ ምሕረትን፣ ይቅርታን በሚሻው በብላቴናዋ ተማፅኖ ድባቡ የተቀየረ መሰለ፡፡

ይህ ድምፅ ከምሕረትና ከእርቅ ይልቅ ጥላቻና ጠላትነት ለነገሠበት የኢትዮጵያችን የፖለቲካው መድረክ፣ መለያየት፣ ጠብና መከፋፈል ላየለባቸው የዕምነት ተቋማት፣ በዘር ፖለቲካ ቁም ስቅሏን ለምታየው እናት ምድራችን በዚህች ታናሽ ብላቴና አማካይነት የታወጀ የእርቅና የምሕረት አዋጅ መስሎ ተሰማኝ፡፡

በሕፃኗ የአነጋገር ብስለት፣ አንደበተ ርዕቱነትና ድፍረት የተመሰጡ በአዳራሹ በተሞሉ እንግዶች በአድናቆትና በግርምት ፈገግታ አዩዋት፡፡ ጥቂት ቆየት ብሎም በሐዘኔታ መንፈስ የታጀበችው ሕፃን ከእሷ የሚወጣ በማይመስል አስገምጋሚ የፍቅር ነጎድጓድ ድምፅ ‹‹እባክዎ አባቴን ፍቱልኝ/አስፈቱልኝ›› ስትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን በግጥሟ መልእክት ዜማና በዓይኖቿ መማፀንና መሟገት ያዘች፡፡

‹‹አባባ ልጅህ አድጌልሃለሁ፣ በትምህርቴም ጎብዤያለሁ፣ ትልቅ ሰው ሆኜ ስምህን አስጠራዋለሁ፡፡ አ…ባ…ባ… አ…ባ…ብ…ዬ…ዬ…ዬ… በጥፋትህ እንደተፀፀትህ አውቃለሁ፡፡ ነገ ከእስር ቤት ወጥተህ ጥፋትህን በሚልቅ ካሳ ለሕዝብና ለአገር ባለውለታ እንደምትሆን አስባለሁ፣ አ…ባ…ባ…፣ አ…ባ…ብ…ዬ… ናፍቀኸኛል እኮ አባቢ! እንደ ሁሌው ሁሉ እስር ቤት መጭቼ አይሃለሁ… አንተም እንደምትናፍቀኝ አውቃለሁ፣ አባቢዬ…ዬ…ዬ!›› እንደዚህ ባሉ እጅግ ስሜትን በሚነኩ፣ የዓይኖቻችንን የእንባ ምንጮች ሁሉ ለመንደል ኃይል ባላቸው፣ ጨካኝ የተባለን ሰው ልብ እንኳ ሊያርዱ በሚችሉና ነፍስ ድረስ ዘልቆ በሚሰማ ኃይለ ቃል በተሞሉት ግጥሟ ‹‹እባክዎ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አባቴ ያስፈትሉኝ፣ አባቴን መንግሥትዎ ይቅርታ ያድርግለት!›› አለች፡፡ የብላቴናዋ ተማፅኖ ለአፍታ በልቤ ውስጥና በሚሊንየሙ አዳራሽ መድረክ ላይ የነገሠች ብቸዋ እርቅን ሰባኪ በእጅጉ መላው ስሜቴን ተቆጣጠረችው፡፡

ለወላጅ አባቷ መንግሥት ምሕረት ያደርግለት ዘንድ አጥብቃ የምትሻ፣ ጥላቻና ቂም በቀል ባየለባት ምድረ በዳ የበቀለችና ያበበች የፍቅር፣ የእውነት ምስክር ቡቃያ መስላ በዓይነ ኅሊናዬ ገዝፋ ታየችኝ፡፡ አዳራሹን ካስዋቡት የተለያዩ ሐምራዊ ቀለሞችን ከሚረጩት የመድረኩ አምፖሎች አሥር እጅ ደምቃ፣ አብርታና ጎልታ ደመቀችብኝ፡፡ ይህች ትንሽ ግን ፍቅር ድፍረትና ኃይል የሆናት ታላቅ የምሽቱ ብላቴና ጀግና፡፡ የዚያች ትንሽ ብላቴና የተማፅኖ ግጥም አንጀትን የሚያንሰፈስፍ፣ ሁለንተናን የሚያርድ፣ ውስጥን የሚበረብር፣ አባባና እማማ የሚሏቸው ልጆች ላላቸው ወላጆች ሁሉ ልብን በሐዘን በሚሰብር ቅላጼና ተማፅኖ የቀረበው ግጥም በእውነት ለመናገር በእጅጉ ነበር ልቤን የነካው፡፡

እንዲህ ዓይነቱን የተማፅኖ ግጥም እየሰሙ ያሉት በአባትነት ፍቅር፣ በመልካም ሥነ ምግባር ልጆቻቸውን አሳድገው በማስተማር ላይ ያሉት የኢትዮጵያችን ጠቅላይ ሚኒስትር በዛች ምሽት እንዲያ በመድረኩ ላይ ‹‹እባክዎ አባቴን ይፍቱልኝ›› እያለች ፊት ለፊታቸው ቆማ በኮልታፋ አንደበቷ ዓይኗን እያንከራተተች ስትማፀናቸው ምን ሊሉ እንደሚችሉ ባላውቅም፣ የብላቴናዋ ግጥምና ተማፅኖ ግን በእጅጉ ልባቸውን ሊነካቸው እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱስ ሲባል ጠቅላይ ሚኒስትር በስስትና በፍቅር የሚመለከቷቸውና የሚሳሱላቸው አባባ፣ አባብዬ የሚሏቸው ልጆች አላቸውና፡፡

የቅዳሜዋ ምሽት የሚሊንየም አዳራሽ ዝግጅት በድንገት የተሰማው የምሕረት ጥያቄና የአባቴን ይፍቱልኝ ነፍስና አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማው የብላቴናይቱ የተማፅኖ ድምፅ ያለ ጥርጥር ፍትሕንና እርቅን የተራቡ የብዙዎች ወገኖች ድምፅ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ይህ ድምፅ ከምሕረትና ከእርቅ ይልቅ ጥላቻና ጠላትነት ለነገሠበት የኢትዮጵያችን የፖለቲካ መድረክ፣ መለያየት፣ ጠብና መከፋፈል ላየለባቸው ለዕምነት ተቋማት፣ የጥላቻ ፖለቲካ ቁም ስቅላቸውን ለሚያሳያቸው ፖለቲከኞች ትልቅ መልዕክት አለው፡፡ በዚህች ታናሽ ብላቴና የዋህ ልብና ንፁህ መንፈስ የታወጀ የእርቅና የምሕረት አዋጅ መስሎ ቢሰማኝ ብዕሬን በማንሳት እንዲህ ስሜቴን ላጋራችሁ ወደድሁ፡፡

መንግሥት በቅርቡ የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናትንና በተለያዩ የወንጀል ምክንያቶች ለረጅም ጊዜያት በእስር  ቤት የቆዩ ወገኖችን በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች አደራዳሪነት ይቅርታ በማድረግ ምሕረት መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በይቅርታ የተፈቱ ሰዎችም በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ኑሮ በመኖር ላይ መሆናቸውንም አውቀናል፣ አይተናልም፡፡ ይህንን ዓይነቱን ይቅርታ የሚፈልጉ በርካታ ዜጎች አሁንም አሉ፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት የሚቃወመውንና ከእኔ ወገን ካልሆንክ ከጠላቴ ወገን ነህ በሚል ጭፍን አካሄድ የገዛ ሕዝቡን በማሸማቀቅ ሊያሳቅቅ አይገባውም፡፡ ከሕዝብ ጋር ተኳርፎና ተራርቆ፣ የገዛ ወገንን አስጠብቦና አስጨንቆ በመያዝ ፈጣን የሆነ ልማት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያችን ለዘመናት ካስነከሳት የረሃብና የእርስ በርስ እልቂት ወጥታ፣ ቁስሏ ሽሮ፣ ስብራቷ ተጠግኖ አንገቷን ከደፋችበት ታሪኳ ቀና ትል ዘንድ፣ በልማትና በዕድገት ጎዳና ላይ ተራምዳ እንድናያት ይህ ትውልድ አጥብቆ ይሻል፡፡

ይህ ይሆን ዘንድ መንግሥት ልበ ሰፊ፣ ታጋሽና ሕዝቡን የሚወድና የሚያከብር፣ በተባበረ ክንድ ድህነትን እንድንበቀለው ሊያስተሳስረን የሚችልበት ሕዝባዊ የሆነ የፍቅር ገመድ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ በቅዳሜዋ ምሽት በሚሊንየም አዳራሽ የቀረበው በሕፃን መዓዛ የቀረበው የአቤቱታና ተማፅኖ ግጥም የበርካቶች እምቦቃቅላ ሕፃናትና ብላቴናዎች፣ እንዲሁም የሌሎች በርካታ ፍትሕን የሚሹ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ጭምር ጩኸትና ድምፅ እንደሆነ መንግሥት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ያሳሰበ የማንቂያ ደወል ይመስለኛል፡፡ ፍቅር፣ ሰላም፣ ፍትሕና ልማት ለኢትዮጵያችን ይሁን!
ሰላም! ሻሎም!
http://www.ethiopianreporter.com