Sunday, November 4, 2012

ከአሥር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ 15 ቢሊዮን ዶላር መውጣቱ ተረጋገጠ:: ካቻምና ብቻ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ታጥቷል




በአስራት ሥዩም

እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ሕጋዊ በሆነና ባልሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ተደርጎ ወደ ውጭ ገበያዎች ማምራቱን በቅርቡ ይፋ የሆነ ሪፖርት አመለከተ፡፡ ይህ ችግር በመላ አፍሪካ ትኩረት እየሳበ እንደመጣ ታውቋል፡፡

የፋይናንስ ምንጭ በእጅጉ ከሚያስፈልጉዋቸው ታዳጊ አገሮች ወደ ሌሎች አገሮች ገንዘብን በማዘዋወርና በሕገወጥ የፋይናንስ ግብይት እየወጣ ያለውን ሀብት በተመለከተ እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ ሲወጡ የነበሩ ሪፖርቶች የሚያረጋግጡት፣ ክስተቱ ትኩረት እየሳበ መምጣቱን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን ውስን የውጭ ምንዛሪ መጠን ይኼው ከፍተኛ የካፒታል ማዛወር ወይም ማሸሽ ተግባር በእጅጉ እየታየባት በመምጣቱ፣ የመነጋገርያ አጀንዳ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
Download “Capital Flight from Sub-Saharan African Countries: Updated Estimates, 1970 – 2010”



ተሻሽለው የወጡ አኀዞች እንደሚያመለክቱት፣ እ.ኤ.አ. ከ1970 እስከ 2010 በነበሩት ሰላሳ ዓመታት 24 ቢሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ እንዲሸሽ ተደርጓል፡፡ ገንዘብ በከፍተኛ መጠን እየሸሸ መሆኑ ከተመዘገበባቸው ጊዜያት ትልቁን ድርሻ መያዝ የጀመረው እ.ኤ.አ ከ2000 በኋላ ያለው ሲሆን፣ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2010 ብቻ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በአገሪቱ ኢንቨስት ያደረጉ የውጭ ባለሀብቶች ያሸሹት ገንዘብ (ካለፈው ዓመት ኅዳር ወር አኳያ ከአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት በላይ ሆኖ ተመዝግቧል) በከፍተኛነቱ ሲጠቀስ፣ ከዚህ መጠን ቀጥሎ የተመዘገበው ከፍተኛ የገንዘብ ማሸሽ እ.ኤ.አ. በ2002 የታየው የ3.1 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ በሪፖርቱ የቀረቡት መረጃዎች ሲፈተሹ፣ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የካፒታል ማሸሽ የተመዘገበባቸው ጥቂት ዓመታት ሆነው ይገኛሉ፡፡

ካፒታል የማሸሽ መጠኑ እ.ኤ.አ. ከ2001 ጀምሮ በ2.1 ቢሊዮን ዶላር እየተመነደገ መምጣት ሲጀምር፣ 2002፣ 2003፣ 2004፣ 2007፣ 2009 እንዲሁም 2010 ላይ በእያንዳንዱ ዓመት የ1.4 ቢሊዮን ዶላር መጠን የመዘገበበት የገንዘብ መጠን ከአገሪቱ ወጥቷል፡፡

ሪፖርቱ ያካተታቸው ጊዜያት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የመጨረሻዎቹ አራት ዓመታት፣ እንዲሁም የደርግን የመጨረሻዎቹ አሥር ዓመታት ሲሆን፣ በእነዚህ ጊዜያት ከተመዘገበው የገንዘብ ማሸሽ በልጦ የተገኘው ግን ባለፉት አሥር ዓመታት የተመዘገበው መጠን ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1982 ከአገሪቱ የወጣው የገንዘብ መጠን 2.8 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛው በመሆን ተመዝግቦ የቆየ መጠን ነበር፡፡ ይህ ቢባልም በ1981 1.5 ቢሊዮን ዶላር፣ በ1985 1.3 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ1987 1.9 ቢሊዮን ዶላር በመውጣቱ ይህንን ጊዜ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከአገሪቱ የሸሸበት ሁለተኛው ዘመን እንዲሆን አስችሎታል፡፡  

ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገሮች 33 አገሮች በአጠቃላይ 814 ቢሊዮን ዶላር የሸሸ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 591 ቢሊዮን ዶላሩ በዚሁ ቀጣና ከሚገኙ ነዳጅ አምራች አገሮች እንዲወጣ የተደረገ ነው፡፡ ይህን ያህል መጠን ካፒታል እየሸሸ የሚገኘው ደግሞ የአገሮቹ የነዳጅ ገቢ እያደገ በመጣበት ጊዜ ሆኖ ሲመዘገብ፣ በተለይ ናይጄሪያ 311.4 ቢሊዮን ዶላር የሸሸባት ትልቋ አገር ሆኖ ተገኝታለች፡፡

ሪፖርቱ አስገራሚ የሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ እየሸሸ የሚገኘው ካፒታል በቀጣናው በይፋ የተሰጠውን 659 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከውጭ በቀጥታ ከተገኘው የ306 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በልጦ መገኘቱ ነው፡፡ ይበልጡን አስገራሚ የሆነው ደግሞ ከሰሐራ በታች ያለው አካበቢ ለተቀረው ዓለም አበዳሪ ሆኖ የተገኘበት አጋጣሚ ሲሆን፣ እየሸሸ ከሚገኘው ከፍተኛ ገንዘብ በተፃራሪ የቀጣናው የዕዳ መጠን 189 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

ይህ ሪፖርት ከሌሎች በካፒታል ሽሽት ላይ ከተደረጉ ጥናቶች የተለየ እንዲሆን ካደረጉት ነጥቦች መካከል ያለደረሰኝ የሚካሄዱ የንግድ ልውውጦችን፣ እንዲሁም የሐዋላ ገቢዎች በአገሪቱ ኦፊሴላዊ የሒሳብ መዛግብት ውስጥ ተካተው አለመገኘታቸው የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ማካተቱ ነው፡፡

ያለደረሰኝ የሚካሄዱ የወጪና ገቢ ንግድ ጉዳቶች ላኪዎች ሆነ ብለው ከገዙበት ዋጋ በታች ደረሰኝ ማቅረባቸው፣ እንዲሁም አስመጪዎች ከገዙበት ዋጋ በላይ የሚያሳይ ደረሰኝ ማምጣታቸው፣ ከአገሪቱ ለሚያፈተልከው ካፒታል ዓይነተኛው መሣርያ ስለመሆኑ ሪፖርቱ በጥልቀት ቃኝቶታል፡፡ በአንፃሩ የተገላቢጦሹን ማለትም ላኪዎች ከገዙበት ዋጋ በላይ፣ አስመጪዎችም ከገዙበት ዋጋ በታች አግባብነት የሌለው የግብይት ደረሰኝ ቢያቀርቡ ግን የወጣውን ካፒታል መልሶ ለማግኘት እንደሚረዳ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ አግባብነት በሌላቸው የግብይት ደረሰኞች ከመጎዳት ይልቅ ተጠቃሚ የሆነችበት አጋጣሚ መፈጠሩ የተመለከተው 7.1 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገሪቱ ገቢ መሆኑን የሚያመላክት መረጃን በማስደገፍ ሲሆን፣ አጋጣሚው የተፈጠረውም ለወጪ ንግድ ከመሸጫ ዋጋ በላይ ለገቢ ንግዱም ከመግዣ ዋጋ በታች ደረሰኞች ለግብይት በመዋላቸው ነው፡፡ በተለይ ከተገዙበት ዋጋ በታች የሚቀርቡ ደረሰኞች ዋና አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ በተጨማሪም አገሪቱ በይፋዊ የክፍያ ሚዛኗ (የአገሪቱ ብድር ዕዳና ያበደረችው መጠን) ባታሳየውም ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐዋላ ተመልሶ ወደ አገሪቱ መግባቱ ተጠቅሷል፡፡

ጥናቱን ያካሄደው የማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምርምር አንስቲትዩት እንደሚያብራራው፣ የካፒታል ሽሽትን በሚመለከት ከዚህ ቀደም በተደረጉ ጥናቶች የቀረቡ አኀዞች መሠረታውያኑን የተዛቡ የንግድ ግብይት ሰነዶችን እንዲሁም ሐዋላን ያላካተቱ በመሆናቸው ትክክለኛውን አኀዝ አያመለክቱም፡፡ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች ከአንድ አገር በሚወጣውና በሚገባው የካፒታል ፍሰት መጠን መካከል ያለውን ልዩነት መሠረት አድርገው ይቀርቡ የነበሩ በመሆናቸው፣ ኦፊሴላዊ ባልሆነ መንገድ በመካሄድ ከሰሐራ በታች ባሉ አገሮች ቁልፍ ሚና ያላቸውን የሐዋላና አግባብነት የጎደላቸው የግብይት ሰነዶችን በካፒታል ፍሰቱ ውስጥ አለማካተት የቀደምት ጥናቶች ደካማ ጎን መሆኑን ተቋሙ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment