Wednesday, August 17, 2011

                                 የረመዳን በረካ
             ‹‹ከረመዳን ደስታ ጋር የሚሰማን ትልቅ ደስታ አጋጥሞናል የቀደምት ኢትዮጵያውያን ተግባራትና የአሁኑን ያስተሳሰረ ነገር አይተናልና፡፡››
(ሪፖርተር) በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለአምስት ቀናት ሲካሔድ በሰነበተው የእስላማዊ ቅርሶች ዐውደ ርዕይና ባዛር በተጠናቀቀበት ነሐሴ 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ያገኘናቸው ሐጂ መሐመድ ኑር ጅላሎ፣ ባዩት ነገር ስለመደሰታቸው ያካፈሉን ሐሳብ ነበር፡፡


‹‹የሀገራችንን እስላማዊ ቅርሶች በመጠበቅ ለቱሪዝም ዕድገት እንትጋ›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው አራተኛው ዙር እስላማዊ ዐውደ ርዕይና ባዛር፣ ነውን ከነበር ያስተሳሰረ፤ ወቅትን ከክሥተት ያመሳከረ ሆኖ አልፏል፡፡


ዐውደ ርዕዩ ካለፉት ሦስት ዓመታት በተለየ መልኩ አገር አቀፍ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ከአርጎባ፣ ሐረር፣ ጂማ፣ ከሚሴ፣ ቃጥባሬ አካባቢ የመጡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሎችን የሚያመለክቱ ቅርሶች፣ የብራና ታሪካዊ መጽሐፎችና ፎቶግራፎች ለእይታ በቅተዋል፡፡


የንጉሥ አሕመድ ነጋሽ (አስሃማ ነጃሼ) ታሪክ በሰሌዳዊ ጽሑፍ በቀረበበት ዐውደ ርዕይ፣ ንጉሡ በዚያን የስደት ዘመን በ7ኛው ምእት ዓመት ከለላ ፈልገው ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የነቢዩ መሐመድ ወገኖች በተቀበሉበት ጊዜ የተናገሩት ኃይለ ቃል በጉልህ ይነበባል፡፡ ‹‹በኔ ግዛት ጥብቆች ናችሁ፡፡ አንድም ሰው በክፉ ቢደርስባችሁ ቅጣት ደንግጌበታለሁ፡፡ በፈለጋችሁት ስፍራ ኑሩ፡፡›› ሌሎች መልእክቶችም በዐውደ ርዕዩ ለእይታ በቅተውበታል፡፡


ሐበሻን ከሙስሊሙ ዓለም ልዩ ከሚያደርጋት ተብለው ከተዘረዘሩትም ነቢዩ መሐመድ፣ ‹‹ከእናቴ በኋላ (ሁለተኛ) እናቴ ነች›› ማለታቸውና ‹‹የመጀመርያው ሙአዚን የቢላሉል አል ሐበሽ ወገን መሆናችን የእስልምና የዓለም ባለውለታ የሆኑ ሙስሊሞች ሀገር ናት›› ተብሎም ተጠቅሷል፡፡


‹‹ወደ ሀበሻ ተሰደዱ፤ በእርሷ ዘንድ አንድ ንጉሥ አለ፡፡ እርሱ ዘንድ ማንም ተበዳይ አይሆንም›› ባሉት መሠረት፣ በመጀመርያው ስደት (615 ዓ.ም.) 12 ወንዶችና 4 ሴቶች፤ በሁለተኛ ስደት 83 ወንዶችና 18 ሴቶች ወደ ሐበሻ መጥተዋል፡፡


ዐውደ ርዕዩ ከዑደተ እስልምና ሌላ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ስለተቋቋሙት እስላማዊ ሱልጣኔት (መንግሥታት) ያወሳል፡፡ ከ9ኛው እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ስለነበሩት ሱልጣኔቶች የሚያወሳ ክፍልም አለው፡፡


ከእነርሱም መካከል የሸዋ ማኽዙማይት ሱልጣኔት በጥንታዊ የሃርላ (ሐረር አካባቢ) ምድር፣ የአዳል ሱልጣኔት፣ የይፋት ወላስማ ሱልጣኔት ይገኙባቸዋል፡፡ ከምጣኔ ሀብት አኳያም ሱልጣኔቶቹ የመገበያያ ገንዘብና ሳንቲም እንደነበራቸውም በዐውደ ርዕዩ ተጠቁሟል፡፡


እስላማዊ ሥነ ሕንፃና የከተማ ንድፍ፣ ስለእምነት ሥነ ልቦና፣ ዕውቀት፣ ስለቤተሰብ አመሠራረትና የሴቶች ስፍራም ተመልክቷል፡፡


በሰሌዳው ላይ ከተለጠፉት ጥቅሶች መካከል አንዱ የሴቶችን ጉልህ ቦታ ያጎላል፡፡ እርሱም፣ ‹‹ከእናንተ መካከል በላጫችሁ ለሴቶቻቸው ይበልጥ ደግ የሆኑት ናቸው›› የሚለው ነው፡፡


ከብራና መጻሕፍቱ መካከል ከ200 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ይገኙባቸዋል፡፡ እነርሱም የመድኃኒት፣ የአስተዳደር፣ የሕግና የሥነ ፈለክ ጉዳዮችንም የሚዘረዝሩ ናቸው፡፡


ዐውደ ርዕዩ ታዋቂዎችንም ያስተዋውቃል፡፡ በሃይማኖት እንዲሁም በቀለም ትምህርታቸው ስኬትን ከተጎናጸፉና በተምሳሌትነት ከቀረቡት ኢትዮጵያውያን መካከል ዳውድ ኢብን አቡበከር አንዱ ናቸው፡፡ በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው፣ ኢትዮጵያዊው ሙፍቲ ዳውድ ለመጀመርያ ጊዜ የማተሚያ መሣርያ ለአገሪቱ ያበረከቱ፣ የመንገድ ቅያስና የሥነ ፈለክ ተመራማሪ እንደነበሩም አስፍሯል፡፡


ሼህ አሕመዲን ሸህ አብዱላሂ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ለ4ኛው እስላማዊ ዐውደ ርዕይና ባዛር ያስተላለፉት መልእክት በመጽሔቱ ሰፍሯል፡፡ በዚያም እስላማዊ ቅርሶች የእስላማዊ አስተምህሮ አካል በመሆናቸው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሊንከባከባቸውና ከትውልድ ትውልድ እንዲዘልቁ፣ ብሎም ለአደባባይ እንዲበቁ ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህን በማድረግ በኩል ከምክር ቤታችን ጋር በመሆን ይህን ዐውደ ርዕይ ያዘጋጀው ማኅበር መልካም አርአያ በመሆኑ ሙስሊሞች ፈለጉን ሊከተሉ ይገባል፤›› በማለትም አሳስበዋል፡፡


እነዚህን ቅርሶች በተደራጀ መልኩ በማስቀመጥና ከአገሪቱ አልፎ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እይታና እውቅና እንዲበቁ፣ ከዚያም አልፎ ለቱሪስት መስህብ በመሆን የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ሼህ አሕመዲን ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡


ዐውደ ርዕዩን ከረመዳን ደስታ ጋር ያያዙት ሐጂ መሐመድ ኑር፣ የዘንድሮው ዐውደ ርዕይ ካለፉት ዝግጅቶች በይዘትም፣ በአደረጃጀትም ከአካባቢያዊ ስፋትም አኳያ የተሻለ በመሆኑ በቀጣይ ያልተዳሰሱ አካባቢዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ከመጠቆም አልተቆጠቡም፡፡  


ዓመት እየተጠበቀ ብቻ ዐውደ ርዕይ ከማሳየት ባሻገር፣ በቋሚነት የሚታይበት ሙዚየም ቢቋቋም ጠቀሜታ ይኖረዋልም ብለዋል፡፡ ዐውደ ርዕዩንና ባዛሩን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከአሕመድ አል ነጃሺ ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment