Sunday, August 28, 2011

ያባታቸው ልጆች

                 by Eshete Bekele
 አል ሳዲ ጋዳፊ
ዘመኑ የፈረንጆቹ 2003 ነው፡፡ሃገሩ ሊቢያ…በአለም የእግር ኳስ መድረክ እምብዛም ስሟ የማይታወቀው ሊቢያ ከ ካናዳ ጋር የወዳጅነት ጨዋታዋን በሜዳዋ ታደርጋለች፡፡ከሊቢያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች መካከል አንዱ መቀየር ነበረበት…ረዳት ዳኛው የተቀያሪውን ማንነት እንዳሳወቁ ተቀያሪው ተጨዋች ካናዳዎችን መሰናበት ጀመረ፡፡ሜዳ ውስጥ ከሚገኙት ተጨዋቾች መካከል በረኛውን ጨምሮ ዘጠኙን እየተንጎራደደ ጨበጠ፡፡ዳኛው፤ተመልካቾች እና የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች ይህን ድርጊት መታገስ ነበረባቸው፡፡ለአንድ ደቂቃ ከአስር ሰከንድ ያህል፡፡ተጨዋቹን ሜዳ በፍጥነት እንዲለቅ ማናቸውም ማስገደድ አይችሉም፡፡እርሱ ከሁሉም በላይ ነው፡፡ከሜዳ ሲወጣም አስገራሚው ድርጊት ቀጠለ፡፡የካናዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች፤ተጠባባቂ ተጨዋቾች እና የቡድኑን አባላት ሁሉ ጨበጠ፡፡ወደ ሊቢያዊ ፖሊስ ተጠግቶ እጁን ዘረጋ…እም…አሰበ …ክብሩ አይፈቅድለትም፡፡የተዘረጋው እጁ ከፖሊሱ እጆች ጋር ከመጨባበጡ በፊት ሰበሰበው፡፡

ይህ ሰው ማን መሰላችሁ…የሊቢያ ልዩ ሃይል አዛዥ፤የሊቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት፤በሊቢያው አልሃሊ እና የጣሊያኑ ጁቬንቱስ እግር ኳስ ክለቦች ባለድርሻ የሊቢያ ብሄራ
ዊ ቡድን 11 ቁጥር አጥቂ አል ሳዲ ጋዳፊ…አል ሳዲ ፕሮፌሽናልም ነው፡፡በፔሩጂያ፤ፓሌርሞ፤ዩዲኒዜ እና ጁቬንቱስ ከዋና ቡድኖች ጋር ልምምድ ሰርቷል፡፡ለእነዚህ ቡድኖች የፈረመው ተከፍሎት ሳሆን ከፍሎ ነበር፡፡ጣልያኖች ይህንን አጥቂ በጎሎቹ ሳይሆን ከፖሊስ ጋር በሚያደርገው ግብግብ፤በአደንዛዥ ዕፅ እና የመጠጥ ሱስ ያስታውሱታል፡፡ሳዒድ በፔሩጂያ ሳለ የክለቡ ባለቤት ሉቺያኖ ጉቺም ሆኑ አሰልጣኙ ሴርሴ ኮስሚ ሊያሰልፉት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡በአንድ ወቅት ታዲያ የሳኢድ በፔሩጂያ መሰለፍ አለመቻል የጣሊያን እና ሊቢያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊያሻክር ሆነ፡፡በዚን ጊዜ የክለቡ ባለቤት ሉቹያኖ ጉቺ በጣልያኑ ፕሬዝደንት የተሰጣቸውን ትዕዛዝ እንዲህ ያስታውሱታል፡፡“Berlusconi called me up and encouraged me. He told me that having Qaddafi in the team is helping us build a relationship with Libya. If he plays badly, he plays badly. So be it.” ከተቀያሪ ወንበር ሳይነሳ በተደረገለት የሽንት ምርመራ የአበረታች ዕፅ እንደተጠቀመ የተረጋገጠበት ሳዒድ የ3ወር እገዳም ደርሶበታል፡፡ሳዒድ በእግር ኳሱ ባይሳካለትም የአባቱን አምባገነንነት እና የሊቢያ ሀብት ተጠቆሞ በሊቢያ እና ጣሊያን እንደ ግል ጓዳው ሲፈነጭ ኖሯል፡፡ፓርቲ ወዳዱ ሳዒድ ቅንጡ የመኖሪያ ቤቱ ውድ መኪኖቹ በሊቢያ አብዮተኞች እንዳልነበር ሲሆኑ ግን የሚታደግበት አቅም አልነበረውም፡፡
           ሙአመር ጋዳፊ ከሁለት የትዳር አጋሮቻቸው ዘጠኝ ልጆችን አፍርተዋል፡፡አንድ ደግሞ በማደጎ አግኝተዋል፡፡ዛሬ በህይወት ያሉት ልጆች ከአባታቸው አምባገነንነትን እና ስግብግብነትን የወረሱ ይመስላሉ፡፡እርስ በርስ ጦር ከመማዘዝ አንዱም በሌላው ላይ ከማሴር ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡እ.ኤ.አ. በ1970 ከፈቷቸው ፋቲህ አል ኑሪ ካሊድ የተወለደው ሙሃመድ ሙአመር ጋዳፊ የመጀመሪያ ልጃቸው ሲሆን የሊቢያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን፤የኮምዩንኬሽን፤የፖስታ እና ቴሌኮም ኩባንያዎችን በበላይነት ይመራል፡፡የሊቢያ አማፅያን ማርከንዋል ብለው የነበረ ቢሆንም ውሎ ሲያድር ከእጃቸው እንዳልገባ ታውቋል፡፡
        
   ሳኢፍ አል ኢስላም 


የሙአመር ጋዳፊ ሁለተኛ ባለቤት ሳፊያ ፋራካሽ አል ባራሲ የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ምክትል ፕሬዝደንት እና የቡራቅ አየር መንገድ ባለቤት ናቸው፡፡የአባቱ ቀኝ እጅ እንደሆነ ሲነገርለት የቆየው ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ለሙአመር ጋዳፊ እና ሳፊያ ፋራካሽ የመጀመሪያ ልጅ ሆኖ ስድስት ወንድሞቹን እና ሁለት  እህቶቹን አስከትሏል፡፡”አንታገስም…እስከ መጨረሻ እንዋጋለን…በፍፁም አናፈገፍግም…’’በሚሉ ፉከራዎቹ የሚታወቀው ሳዒፍ በሊቢያ ፖለቲካ ከአባቱ ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው ነበር፡፡ሳዒፍ ኢንጂነር እና ፖለቲከኛ ሲሆን ከ3 አመት በፊት "The role of civil society in the democratisation of global governance institutions: from 'soft power' to collective decision-making?" በሚል ርዕስ ባቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ የለንደን ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቶታል፡፡
አምባገነኑን የሊቢያ መሪ ሲያንቆለጳጵሱ የኖሩት አሜሪካና አውሮፓውያንም በሳዒፍ ተስፋ ነበራቸው፡፡የአባቱን መንበር ለመረከብ ቅርብ የነበረው ሳዒፍ ለአሜሪካ እና አውሮፓውያን ዲሞክራት ነበር፡፡ያሰቡት ሳይሆን ሳዒፍ ቆዳውን ቀይሮ አባቱን መሰለ የሊቢያም ህዝብ ትዕግስቱ አለቀ፡፡አስገራሚው ነገር የእንግሊዝ ምሁራን እና የትምህርት ተቋማት ምስጋና ያዥጎደጎዱለት ጥናታዊ ፅሁፍ በራሳቸው በእንግሊዞቹ ቻናል 4 ኩረጃ በዝቶበታል ተብሎ መዋረዱ ነው፡፡ሳዒፍ ብዙ ጊዜውን ከአባቱ እግር ስር ቢያሳልፍም የሊቢያ ብሄራዊ ኢንጂነሪንግ አገልግሎት እና እቃ አቅራቢ ኩባንያን፤የኢንቨስትመንት እና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣኑን እንዲሁም ባባቱ ስም የተሰየመውን የበጎ አድራጎት ተቋም በበላይነት ይመራል፡፡ሳዒፍ በሎከርቢ ሰማይ ለፈነዳው አውሮፕላን ተጎጂዎች የተደረገውን የካሳ ክፍያ እና ፍንዳታውን አቀነባብሯል ለተባለው አብዲልፋሴት አል መግራሂ መፈታት የተደረጉትን ድርድሮች እንዳካሄደ ይነገራል፡፡ከመንግስት ካዝና የፈለገውን ያህል የማፈስ ስልጣን የነበረው ሳዒፍ በ2008 ከአሁን በኋላ በሊቢያ ፖለቲካ ጣልቃ አልገባም ሲል ቢደመጥም በአባቱ መንበር ላይ በተነሱት ሊቢያውን ላይ ተኩስ ማለቱን አላቆመም፡፡አማተር ሰዓሊው እና አደን ወዳዱ ሳዒፍ ከእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብ እና ፖለቲከኞች ጋር የነበረው የጠበቀ ወዳጅነት እንኳን የቤተሰባቸውን ስልጣን ለመታደግ ቀርቶ በለንደን ያለውን የመኖሪያ ቤት ከጥቃት ለመጠበቅ ሳያስችለው ቀርቷል፡፡በሊቢያ አብዮት እንደ ቃል አቀባይ ከፊት ሆኖ ነበር፡፡
       አል ሙታዚም ቢላህ አል ጋዳፊ


 በአንድ ወቅት በአባቱ ላይ መፈንቅለ መንግስት ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በሙአመር ጋዳፊ ይቅር ባይነት የደህንነት አማካሪ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡የሙኣመር ጋዳፊ ሶስተኛ ልጅ አል ሙታዚም ቢላህ አል ጋዳፊ- እንደወንድሞቹ የራሱ ጦር ሰራዊት የሚፈልገው ሙታዚም ከብሄራዊየነዳጅ ድርጅቱ 1.2 ዶላር ጠይቆ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ሙታዚም የመደራደር፤የመነጋገርም ሆነ የማማከር አቅም ባይኖረውም ሊቢያ ከአሜሪካን ጋር ያቋረጠችውን ወዳጅነት ለማደስ ለምታደርገው ድርድር የአባቱ ልጅ መሆኑ ብቻ በቂ ነበር፡፡የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄላሪ ክሊንተን፤ሴናተሮቹ ጆን ማኬይን እና ጆ ሊበርማንን ባነጋገረበት ወቅት የራሱን የጦር ሃይል ለመገንባት የሚያስችለው ገንዘብ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አላለም፡፡ለአል ሙታዚም አልጄሪያ፤ግብፅ፤አውሮፓውያን እና አዋሳኝ የአፍሪካ ሃገሮች ሁሉ ለሊቢያ ጠላቶች ነበሩ፡፡ሙታዚም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ከሊቢያ የማባረሩን ሃላፊነት ወስዶም አስፈፅሟል፡፡ለአባቱ አስተዳደር ከሊቢያ ጎረቤቶች ይልቅ ሊቢያውያን የጎን ውጋት ሆኑና ሙታዚምን በብሬጋ እና አካባቢው ጦር መዘዙበት፡፡አሁንም በሊቢያ ከአባቱ ደጋፊዎች ጋር ሆኖ አልተሸነፍንም፤አንሸነፍም እያለ ተዋግቶ ያዋጋል፡፡
    
 ሃኒባል ጋዳፊ 

ሃኒባል ጄኔቫ በእስር ላይ
          በፓሪስ ነፍሰጡር ሚስቱን ደብድቧል፡፡በጄኔቫ ሁለት ሰራተኞቹን በማንገላታቱ በፖሊስ እጅ ወድቋል፡፡እርሱ ከጄኔቫ እስር ቤት ሲደርስ አባቱ በሊቢያ የሚገኙ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎችን ከሃገራቸው አባረዋል፡፡የስዊዘርላንድ ዜግነት ያላቸውን ሁለት ሰዎች አስረዋል፡፡የልጃቸው ክብር የተነካው ሙኣመር ጋዳፊ በዚህ ብቻ አላበቁም ሃገራቸው ወደ ስዊዘርላን የምትልከውን ነዳጅ አቋርጠዋል፡፡በስዊዝ ባንክ የነበራቸውን ወደ 5 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ አውጥተዋል፡፡ስዊዘርላንድ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባልነቷ እንድትታገድ አመልክተውም ነበር፡፡ሳይሆን ቀረ እንጂ…ስዊዘርላንድ ታዲያ ሙኣመር ጋዳፊን ከሚያህል የሃገር መሪ እና  የንግድ አጋር ጋር መቃቃር ስላላዋጣት ይቅርታ እስከመጠየቅ ደርሳለች፡፡ይህ ሁሉ የሃኒባል ጣጣ ነው፡፡ ይህ ሰው የሙኣመር ጋዳፊ ልጅ የሊቢያን ነዳጅ ለውጭ ሀገሮች በማቅረብ የሚታወቀው የሃገሪቱ የመርከብ ትራንስፖር ድርጅት አማካሪ ሃኒባል ጋዳፊ ነው፡፡ሃኒባል ቢዮንሴ ኖውልስን እና ባለቤቷን ጄይዚን ለአንድ ሰዓት ኮንሰርት በ2ሚሊዮን ዶላር ተከራይቷቸው ነበር፡፡(መቼም ከፍሏቸው ነበር ማለት ሳይከብድ አይቀርም፡፡)
     
አይሻ አል ጋዳፊ


   አይሻ አል ጋዳፊ…የሰላም ልዕልት…ይህ ለሙኣመር ጋዳፊ ብቸኛ ሴት ልጅ በስሟ የተጻፈ መጽሃፍ ነው፡፡በአንድ ወቅት በሊቢያ የሚገኘውን የመኖሪያ ቤቷን ለማስፋት ከአጠገቧ የሚገኘውን ክሊኒክ አስፈርሳለች፡፡በሊቢያ ጦር ሰራዊት የሉቴናንት ጄኔራል ማዕረግ ያላት አይሻ ሳዳም ሁሴንን ለመታደግ ሰራዊቷን እየመራች ባግዳድ ደርሳ ነበር፡፡በሙያዋ ጠበቃ የሆነችው አይሻ የአባቷን የቅርብ ዘመድ ያገባች ሲሆን ወንድሟ ሃኒባል በስዊዘርላንድ ሲታሰር የማስፈታት ድርድሩን አካሂዳለች፡፡አይሻ የራሷ የበጎ አድራጎት ድርጅት ያላት ሲሆን የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ሊቢያ ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት በበላይነት እየመራች ኑሮዋ በአውሮፓ ነው፡፡የሚገርመው ነገር ዛሬ የአይሻን አባት በአምባገነንነት የሚፈርጀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርጓት ነበር፡፡የሊቢያዋ ክላውዲያ ሼፈር የሚል ቅፅል የተሰጣት አይሻ ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገች ቃለምልልስ ” የአሜሪካዋ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄላሪ ክሊንትን ባለቤት ቢል ክሊንተን ከሞኒካ ሊውኒስኪ ጋር ሲቀብጡ ለምን ትዳራቸውን አላፈረሱም ስትል ለመሳለቅ ትሞክራለች፡፡አይሻ ይህንን ጦርነት እናሸንፋለን ብትልም ማታ ማታ ለ ሶስቱ ወንድ ልጆቿ ስለሞት እነድምታጫውታቸው ተናግራለች ምክንያቱም መቼ ሮኬት ሊመታህ እንደሚችል አታውቅም እና የአይሻ መልስ ነው፡፡
     ሙኣመር ጋዳፊ ከእነዚህ በተጨማሪ በዚህ አመት ሞቱ ያልተረጋገጠው ካሚዝ ጋዳፊ፤በኔቶ ጥቃት ህይወቱ እንዳለፈ የሚገመተው ሳዒፍ አል አረብ ጋዳፊ ከ1986ቱ የአሜሪካን ግድያ ሙከራ የታደጋቸው እና የማደጎ ልጃቸው ሚላድ አቡዝታያ ጋዳፊ እና በዚሁ ጥቃት ህይወቷ ያለፈው ሃና ጋዳፊ ሌሎች ልጆቻቸው ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment