Wednesday, August 31, 2011

ኤርትራ በዲፕሎማቷ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ዛቻ ፈጽሟል አለች


‹‹በድርጊታቸው ማፈር የነበረባቸው እነሱ ናቸው›› የኢትዮጵያ መንግሥት

(ሪፖርተር)ኤርትራ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ስብሰባ ወቅት፣ በዲፕሎማቷ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት ዛቻና ማስፈራሪያ ተፈጸመበት ስትል ወነጀለች፡፡ የኢትየጵያ መንግሥት በበኩሉ በዲፕሎማቱ ላይ የተፈጸመ አንዳችም ነገር አለመኖሩን በመግለጽ፣ ‹‹በድርጊታቸው ማፈር ነበረባቸው›› ብሏል፡፡

የኤርትራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፣ የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ አባል ሆኖ በአዲስ አበባ በሚገኘውና በኢጋድ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በተገኘው ዲፕሎማቷ ላይ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የዲፕሎማቲክ ሕግን የጣሰ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደተፈጸመበት አሳውቋል፡፡

‹‹ኤርትራ ወደ ኢጋድ ለመመለስ ምንም ዓይነት ተጨማሪ አካሄድ አይጠበቅባትም፤›› የሚለው የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ የኤርትራ ጉዳይ ከአዲሷ ደቡብ ሱዳን ወደ ድርጅቱ የመቀላቀል ሒደት ጋር መነፃፀሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራዊው ዲፕሎማት ላይ የፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊት ለመሸፋፈን የተደረገ ሻጥር ነው ብሎታል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ቀደም ሲል ወደ ኢጋድ መመለሱን ያሳወቀ መሆኑን በማስታወቅ፣ ከዚያ ቀን ጀምሮ ኤርትራ የድርጅቱ አባል መሆኗን ያመለከተ ሲሆን፣ ‹‹ኤርትራ ወደ ኢጋድ እንድትመለስ የኢትዮጵያን ፈቃደኝነት መጠየቅ አያስፈልግም፤ የኢጋድ ቻርተርም ምንም ዓይነት አካሄድ አይጠይቅም፤›› ይላል፡፡

ስብሰባው የተካሄደባት ኢትዮጵያ በኤርትራ ዲፕሎማት ላይ የፈጸመችው ሕገወጥ ድርጊት አሳፋሪ ነው ያለው የኤርትራ መንግሥት፣ የድርጅቱ አባል አገሮችም ለተፈጸመው ጥፋት ኢትዮጵያን ሊጠይቁ ይገባል ሲል ያሳስባል፡፡

‹‹እነዚህ ሰዎች በውሸት ላይ ውሸት እያቀነባበሩ ከሚኖሩ በፈጸሙት አሳፋሪ ድርጊት ማፈር በተገባቸው ነበር፤›› በማለት ለሪፖርተር የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው፡፡ ኢጋድ በመግለጫውም በዋና ፀሐፊውም በኩል የኤርትራን ድርጊት ኮንኗል ብለዋል፡፡

የኤርትራው ዲፕሎማት የኢጋድን ስብሰባ ለመበጥበጥ ቢሞክርም፣ በዲፕሎማቱ ላይ ምንም ዓይነት የቃልም ሆነ የአካል ጥቃት ሳይፈጸምበት በአግባቡ በሸራተን አዲስ የፀጥታ ሠራተኞች እንዲወጣ መደረጉን አክለው ተናግረዋል፡፡ እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣ ይህንን የኤርትራ መንግሥት አሳፋሪ ድርጊት ኢጋድ ያወገዘው ሲሆን፣ የኤርትራ መንግሥት ግን አሁንም ሌላ ውሸት እየጨመረ ይገኛል፡፡

የኤርትራ መንግሥትን በመወከል ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ በተካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ላይ ‹‹ካልተሳተፍኩ›› በማለት ቢንያም በርሄ የተባለ የኤርትራ ዲፕሎማት ስብሰባውን ማወኩን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት እንዳለው በሸራተን አዲስ የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች ዛቻም ሆነ ማስፈራሪያ ካለመፈጸማቸውም በላይ፣ በኢጋድ ዋና ፀሐፊና በተለያዩ ዲፕሎማቶች ለቢኒያም የተነገረው የኤርትራ የኢጋድ አባልነት አለመፅደቁን ነበር፡፡ ግለሰቡ ከስብሰባው ለመውጣት ፈቃደኛ ባለመሆኑ በመጨረሻ ተሰብሳቢዎች አዳራሹን እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ በሆቴሉ የፀጥታ ሠራተኞች ታጅቦ ከስብሰባ መውጣቱም ተዘግቧል፡፡ ኢጋድም ድርጊቱን ካወገዘ በኋላ ስብሰባው ለ30 ደቂቃዎች ያህል ዘግይቶ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡

No comments:

Post a Comment