Monday, August 22, 2011




ሳብ ሚለርና ሳውዝ ዌስት አዲስ ቢራ ፋብሪካ ሊገነቡ ነው(ሪፖርተር ጋዜጣ)




ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ ቢራ ጠማቂ ኩባንያ ሳብ ሚለርና ሳውዝ ዌስት ዲቨሎፕመንት የተባለ ኢትዮጵያዊ የኢንቨስትመንት ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ በ60 ሚሊዮን ዶላር አዲስ የቢራ ፋብሪካ ሊገነቡ እንደሆነ ታወቀ፡፡ ለፕሮጀክቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲሱ የቢራ ፋብሪካ የሚገነባው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ አቅራቢያ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ መሬቱን ተረክበዋል፡፡

ፋብሪካው በዓመት 500,000 ሔክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም ሲኖረው፣ ግንባታው በ2004 ዓ.ም. መጀመርያ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፋብሪካውን ለመገንባት 18 ወራት ብቻ እንደሚወስድ የገለጹት ምንጮች፣ ለማምረት የታቀደውን የቢራ ዓይነት ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የቢራ ፍጆታ በዓመት አራት ሊትር ብቻ ቢሆንም፣ የቢራ ፍላጐት በዓመት 20 በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡ በቢራ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ለሪፖተር እንደገለጹት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በማደግ ላይ በመሆኑና የሕዝቡም የመግዛት አቅም የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ስለሆነ የተለያዩ የውጪ ቢራ ጠማቂዎች ቀልብ ኢትዮጵያ ላይ አርፏል፡፡ በቅርቡ ሄኒከን የሐረርና የበደሌ ቢራ ፋብሪካዎችን የገዛ ሲሆን፣ ቡሩቴክ የተባለው የጀርመን ቢራ ጠማቂ ራያ ቢራ ላይ አክሲዮን ለመግዛት ተስማምቷል፡፡ የጆኒዎከር ውስኪ አምራች ዲያጂኦ የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ለመግዛት በመጫረት ላይ ነው፡፡

ሳብ ሚለርና ሳውዝ ዌስት ዲቨሎፕመንት በጋራ የአምቦ የማዕድን ውኃ ፋብሪካን ከኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በመግዛት ፋብሪካውን በማስተዳደር ላይ ሲሆኑ፣ ፋብሪካውን ለማስፋፋት 21 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርገዋል፡፡

No comments:

Post a Comment