Wednesday, August 17, 2011




አሜሪካ በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል አለበት አለች

(ሪፖርተር) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኤርትራና የሶማሊያ አጣሪ ቡድን ኤርትራ በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወቅት ፍንዳታዎችን ለማድረስ ሙከራ አድርጋ እንደነበር ማረጋገጡን ተከትሎ፣ አሜሪካ በኤርትራ ላይ የበለጠ ጫና መደረግ እንዳለበት ግፊት እያደረገች ነው፡፡
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሱዛን ራይስን የጠቀሰው ኤኤፍፒ፣ አሜሪካ የኤርትራ ጉዳይ ያሳሰባት መሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹አሜሪካ የኤርትራ ጉዳይ በጣም፣ በጣም ያሳስባታል፤›› ያሉት አምባሳደር ራይስ፣ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ የምትፈልገው ኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል አለበት ብለዋል፡፡

‹‹
እርግጥ ነው አሜሪካ በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲደረግባት ትፈልጋለች፡፡ ይህም ማዕቀብ እንዲጣል በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ መነጋገር ይኖርብናል፡፡ ከአሜሪካ ዕይታ አንጻር ማዕቀቡን ለመጣል አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው፤›› ብለዋል አምባሳደሯ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገሮች በቅርቡ በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል መወሰናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የተመድ አጣሪ ቡድንም ኤርትራ ከሶማሊያው ጽንፈኛ ቡድን አልሸባብ ጋር ግንኙነት እንዳላት ማስረጃ በመያዝ ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ፍንዳታዎችን ለመፈጸም ተንቀሳቅሳ እንደነበር ሪፖርት አቅርቦባታል፡፡

የተመድን አጣሪ ቡድን ሪፖርት በመጥቀስ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ራይስ፣ በፕሬዚዳንት ቡሽ ዘመን ኢራቅን ለመውረር በአንድነት የተሰለፈው ማኅበረሰብ አባል የነበረችው ኤርትራ አሁን ደግሞ ጎረቤቶቿን ለመበጥበጥ ዘመቻ እያደረገች ነው ብለው፣ በአሜሪካ በሽብርተኝነት ከተፈረጀውና በረሃብ በተመታችው ሶማሊያ ውስጥ ረሃብተኞች የዕርዳታ ምግብ እንዳያገኙ ላደረገው አልሸባብ ድጋፏን ትሰጣለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአምባሳደር ራይስ መግለጫ ከወጣ ወዲህ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች አሜሪካ ከተጨማሪ ማዕቀቡ በላይ በተለይ በሥልጣን ላይ ያሉ የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናትን በአሸባሪነት ልትፈርጅ ትችላለች በማለት መላምታቸውን ይናገራሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥት አሜሪካ በሽብርተኝነት ከፈረጀችው የአልቃይዳው ወዳጅ አልሸባብ ጋር መጎዳኘቱ የአሜሪካን ቁጣ የበለጠ ሊያንረው ይችላል ሲሉም ይሰማሉ፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተውን ድርቅና ረሃብ አስመልክቶ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጁቡቲና ሶማሊያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በይፋ የዕርዳታ ጥሪ ሲያቀርቡ፣ ኤርትራ ግን እስካሁን የምግብ ዕርዳታ አያስፈልገኝም በማለቷ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በጥርጣሬ እየታየች ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በኤርትራ በተከታታይ ዓመታት በቂ ዝናብ ባለመታየቱ ምሥራቅ አፍሪካን የመታው ድርቅ እሷንም ጎብኝቷታል ይላሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥት የተከሰተውን ድርቅ በመደበቅ ዜጎቹን እያስራበ መሆኑን በድፍረት እየተናገሩ ነው፡፡ በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት፣ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን የሚጎርፉት ስደተኞች ኤርትራ ውስጥ ረሃብ ለመከሰቱ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

አምባሳደር ራይስ በኤርትራ ላይ የሚጣለው ተጨማሪ ማዕቀብ ማነጣጠር ያለበት በኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ መሆን እንዳለበትና በምንም ዓይነት ሁኔታ የኤርትራን ሕዝብ መጉዳት የለበትም ብለዋል፡፡ ‹‹የኤርትራ ሕዝብ እስካሁን የደረሰበት ሰቆቃ ይበቃዋል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ኤርትራ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ከዓለም ዲፕሎማሲ እየተገለለች ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚታወቁ እጅግ በጣም ሚስጥራዊ ከሚባሉ አገሮች ተርታም ስሟ ይነሳል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሽብርተኝነት ለተፈረጀው አልሸባብ በድብቅ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓ በተመድ ሪፖርት መረጋገጡ የበለጠ መገለልንና ተጨማሪ ቅጣትን ሊያስከትልባት እንደሚችል እነዚሁ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በሶማሊያ ውስጥ በፈጸሙት ጣልቃ ገብነትና በተመድ የተጣለውን ማዕቀብ በመተላለፍ የጦር መሣርያ በማቅረቧ ምክንያት ኤርትራ በተመድ ማዕቀብ ተጥሎባት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ማዕቀቡ ኤርትራ ከውጭ የጦር መሣርያ እንዳታገኝ፣ የፖለቲካና ወታደራዊ ባለሥልጣናቷ የጉዞ እቀባ ሲደረግባቸው ሀብት እንዳያንቀሳቅሱ ታግደዋል፡፡ ለፀጥታው ምክር ቤት በቀረበው የአሁኑ ጥሪ መሠረት ተጨማሪው ማዕቀብ ከተጣለባት ይኼኛው ለሁለተኛ ጊዜ ይሆናል ማለት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment