Thursday, December 27, 2012

የልጆቹን እናት በጥይት ደብድቦ ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ ክስ ተመሠረተበት


“ድርጊቱን አልፈጸምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” ተጠርጣሪ የወንድወሰን ይልማ

በታምሩ ጽጌ

ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 20/20 ልዩ ሥፍራው ካርቱም ሬስቶራንት ኦሎምፒያ አካባቢ የልጆቹን እናት ከ10 በላይ ጥይቶች ተኩሶ ግፍ በተሞላበትና በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ የወንድወሰን ይልማ፣ በከባድ የሰው መግደል ወንጀልና የሰው መግደል ሙከራ ወንጀል ክስ ተመሠረተበት፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ኅዳር 25 ቀን የተጻፈ የክስ ማመልከቻ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን የተመለከተው ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡

ተጠርጣሪው ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰሌዳ ቁጥሩ 2-75991 የሆነ መኪና እያሽከረከረ ባምቢስ አካባቢ ሲደርስ፣ ሟችና የሁለት ልጆቹ እናትን ወይዘሮ ፍሬሕይወት ታደሰን የሰሌዳ ቁጥሩ 2-76225 እያሽከረከረች ይመለከታታል፡፡
በመከታተል ኦሎምፒያ ካርቱም ሬስቶራንት አካባቢ ሲደርስባት፣ ይዞት በነበረው የውግ ቁጥሩ 0740722 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከአሥር በላይ ጥይቶች ተኩሷል፡፡ በተኮሳቸው ጥይቶች ሟችን ደረቷን፣ ጭንቅላቷን፣ ግንባሯን፣ ሆዷን፣ ጀርባዋን፣ ሁለቱንም ታፋዎቿን፣ እጆቿንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿን በመምታት ጨካኝና ነውረኛነቱን በሚያሳይ ሁኔታ እንደገደላት የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪው በወቅቱ ጉዳት ያደረሰው በሟች ፍሬሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ አብረዋት በነበሩትና ወይዘሮ ተናኘ ኃይለማርያም የተባሉ ግለሰብ፣ ከመኪና ወርደው ሲሸሹ ደጋግሞ ቢተኩስባቸውም እንደሳታቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ ተጠርጣሪው በሥፍራው የነበረ የግል ተበዳይ ሙሉጌታ ልንገረው የተባለን ግለሰብ በአምስት ጥይት የቀኝ ክንዱን፣ የቀኝ ታፋውን ሁለት ቦታ ላይና የቀኝ እጁን መምታቱን፣ ገብረተንሳይ ወልደማርያም የተባለን ግለሰብ ደግሞ በአንድ ጥይት የግራ እግሩን በመምታት ማቁሰሉንም የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ታረቀኝ አበራ የተባለውን ግለሰብ ደግሞ ጀርባውን በመምታት በአራቱም ግለሰቦች ላይ የመግደል ሙከራ ወንጀል መፈጸሙን አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪው ይዞት በነበረው መሣርያ ሟች ታሽከረክረው የነበረው የሰሌዳ ቁጥር  2-76225 መኪና በመምታት የ33,600 ብር የንብረት ጉዳት በማድረሱም ተከሷል፡፡

ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ቀርቦ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም፣ ወንጀለኛም አይደለሁም፤” ብሎ ክዶ በመከራከሩ፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም. አቅርቦ እንዲያስመሰክር ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
http://ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment