Sunday, December 9, 2012

ሚድሮክ ተሰጥቶት የነበረውን 6,400 ካሬ ሜትር መሬት ነጠቀ


በውድነህ ዘነበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ለሚገኘው ሁዳ ሪል ስቴት ሰጥቶት የነበረውን ሰፊ የግንባታ መሬት ነጠቀ፡፡ ቦታው የሚገኘው ሜክሲኮ አደባባይ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ ነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በ1997 ዓ.ም. ለሁዳ ሪል ስቴት ኩባንያ ከፍታቸው ከ20 ፎቅ በላይ የሆኑ መንትያ ሕንፃዎች እንዲገነባ 6,400 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቶት ነበር፡፡ ነገር ግን ሁዳ ሪል ስቴት ባለፉት ስምንት ዓመታት ግንባታውን ባለመጀመሩና የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኩባንያው ግንባታውን እንዲጀምር ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ግንባታው ሊጀመር ባለመቻሉ፣ ባለፈው ማክሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2005 ዓ.ም. መሬቱን ነጥቆታል፡፡



የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮው በጻፈው ደብዳቤ ሁዳ ሪል ስቴት በገባው ውል መሥሪያ ግንባታ ባለመጀመሩ ለቦታ ባለቤትነት የተሰጠው ካርታ መምከኑን አስታውቋል፡፡

ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ ለሁዳ ሪል ስቴት የተሰጠው መሬት ቀደም ሲል የመኪና መለማመጃ ነበር፡፡ ሁዳ ቦታው ከተሰጠው በኋላ ለዓመታት አጥሮ ያስቀመጠው ሲሆን፣ አልፎ አልፎ የሚድሮክ ፋውንዴሽን የግንባታ ማሽኖች መሬቱን ለመቆፈር ሲንቀሳቀሱ ይስተዋል ነበር፡፡

ነገር ግን ቁፋሮው በሚገባ ተከናውኖ ሕንፃውን መገንባት ባለማስቻሉና አስተዳደሩ በኩባንያው ተግባር ትዕግሥቱ በመሟጠጡ ዕርምጃ መውሰድ እንደቻለ የቢሮው የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሁዳ ሪል ስቴት መንትያ ሕንፃ ዲዛይንን የሠራው ናሽናል ኮንሰልት ኩባንያ ነው፡፡ ግዙፉና ውበት የተላበሰው የሕንፃ ዲዛይን መሬት ላይ ባለማረፉ ፕሮጀክቱ እንዲመክን ተደርጓል፡፡

ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ በሚድሮክ ኢትዮጵያ፣ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕና በደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ሥር በርካታ ኩባንያዎች አሏቸው፡፡ በእነዚህ ግሩፖች ሥር ሁዳ ሪል ስቴት፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን፣ ሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና ሚድሮክ ፋውንዴሽን በኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

ሁዳ ሪል ስቴት በሚረከባቸው ቦታዎች ላይ ሚድሮክ ኮንስትራክሽንና ሚድሮክ ፋውንዴሽን የግንባታ ሥራዎችን የሚሠሩ ቢሆንም፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን በሥራው ውጤታማ ባለመሆኑ ካለፉት ወራት ወዲህ ግንባታውን የማካሄዱን ሥራ ተነጥቆ በደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ሥር ለሚገኘው ሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እየተሰጠ ነው፡፡

ለሁዳ ሪል ስቴት የተሰጠው መሬት መነጠቁንና በቀጣይነት ሁዳ ሪል ስቴት ስለሚወስደው ዕርምጃ የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፍጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ቢጠየቁም፣ ከከተማ ውጭ በመሆናቸው ጉዳዩን እንዳልሰሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሁዳ ሪል ስቴት የሜክሲኮ አደባባይን ፕሮጀክት መሬት የነጠቀው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ ሁዳ ሪል ስቴት በመሀል ፒያሳ ከከተማው አስተዳደር ሕንፃ ፊት ለፊት የተሰጠውን መሬትም እንደሚነጥቅ በቅርቡ አስጠንቅቋል፡፡

ኩባንያው ከ15 ዓመታት በፊት በመሀል ፒያሳ 36 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ቢሰጠውም በገባው ውል መሠረት ልማቱን ማካሄድ አልቻለም፡፡ በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው የከተማው አስተዳደር ሥልጣኑን እንደተረከበ ቦታውን ለመንጠቅ ሙከራ ቢያደርግም፣ ከንቲባ ኩማና የወቅቱ የከተማው አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ መኩርያ ኃይሌ ከሼክ አል አሙዲ ጋር ባካሄዱት አንድ ሰዓት የፈጀ ውይይት፣ ኩባንያው በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ግንባታውን እንዲጀምር ስምምነት ላይ ተደርሶ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ግንባታውን አጓትቷል ከተባለው ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱ ተነጥቆ ለሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተሰጥቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ከዓመታት በኋላም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በተደረገው ስምምነት መሠረት ግንባታውን ሊያከናውን ባለመቻሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አምባዬ ኩባንያው ዕርምጃ ሊወስድበት እንደሚችል ፍንጭ መስጠታቸውን ባለፈው ረቡዕ ዕትም መዘገባችን ይታወሳል፡፡  
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment