Thursday, December 6, 2012

የዲቪ ሎተሪ እንዲቆም ተጠየቀ


በዘካሪያስ ስንታየሁ

የአሜሪካ ምክር ቤት ዓመታዊው የዲቪ ሎተሪ እንዲቆም ለመጠየቅ የሚያስችለው ሕግ ባለፈው ዓርብ አፀደቀ፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለሁለተኛ የምርጫ ዘመን ከተመረጡ በኋላ ስደተኞችን በሚመለከት ለመጀመርያ ጊዜ የወጣው ይህ ሕግ፣ 245 የድጋፍ ድምፅ ሲያገኝ 139 ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ ይህ ሕግ የዲቪ ሎተሪ ሙሉ ለሙሉ ቀርቶ በምትኩ በአሜሪካ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተርስና ከዚያ በላይ ባሉ የትምህርት ደረጃዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምሕንድስናና በሒሳብ የትምህርት ዘርፎች ብቻ ትምህርት የቀሰሙ በዕድሉ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ነው፡፡



በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አንድ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሜሪካ ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያላቸው ሪፐብሊካን ወግ አጥባቂዎች በመሆናቸው ይህን ሕግ አውጥተውታል፡፡ ነገር ግን ይህ ሕግ ከፍተኛ የመወሰን ሥልጣን ባለው ሴኔት መፅደቅ እንደሚጠበቅበት የተናገሩት የሥራ ኃላፊው፣ በሴኔቱ ቢፀድቅ እንኳን አሁን የጉዞ መርሐ ግብር በጀመሩ ዜጐች ላይ ተፅዕኖ እንደማይኖረው ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው አክለው አብዛኞቹ የሴኔቱ አባሎች ዲሞክራት በመሆናቸው ሕጉ በሴኔቱ ላይፀድቅ እንደሚችል ግን ያላቸውን ግምት ተናግረዋል፡፡

ይህ ስቲም (STEM) የተባለውን ሕግ 218 ሪፐብሊካንና 27 ዲሞክራቶች ደግፈው ድምፅ ሲሰጡበት፣ 134 ዲሞክራቶችና አምስት ሪፐብሊካን ተቃውመውታል፡፡ ሕጉ በየዓመቱ ይወጣ የነበረውን 55 ሺሕ የዲቪ ሎተሪ ዕጣ በማስቀረት ሙሉ ዕጣው በከፍተኛ ደረጃ ለተማሩ ዜጐች እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡

የዲቪ ሎተሪ ዕጣ ሙሉ ለሙሉ መሰረዙ ለዲሞክራቶቹ ባይዋጥላቸውም፣ ሪፐብሊካኑ በአዲሱ ሕግ መሠረት የሚመጡ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ከአንድ ዓመት በኋላ ማምጣት እንዲችሉ ይደረጋል በማለት ለማግባባት እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ዲሞክራቶቹ ይህን ሕግ በማውጣት የዲቪ ሎተሪ ፕሮግራምን ማስቀረት ተገቢ አለመሆኑን ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፡፡

የሕጉ አርቃቂው ላማር ስሚዝ፣ ‹‹በዓለማችን ያሉ በርካታ ጐበዝ ተማሪዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምሕንድስናና በሒሳብ የትምህርት ዘርፎች ለመማር ወደ አሜሪካ ይመጣሉ፡፡ በመሆኑም በአሜሪካ ያሉ ቀጣሪዎች እነዚህን የተማሩ ሰዎች በመቅጠር የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ ሆኖም ይህ ሕግ በዲሞክራቶቹ በኩል ክፉኛ እየተተቸ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ዲሞክራቱ ሉዊስ ጉተሬዝ አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹ይህን ሕግ መደገፍ ማለት የተወሰኑት ስደተኞች ከተቀሩት የተሻሉ ናቸው ማለት ነው፤ የተወሰነ የትምህርት ዘርፍ ከቀሪው የትምህርት ዘርፍ ይሻላል ማለት ነው፤ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ከሌሎቹ ይሻላሉም እያልን ነው፤›› ያሉት ጉተሬዝ፣ ይህ የአሜሪካ እሴትን የሚያፈርስ ነው ብለዋል፡፡

መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ብሔራዊ የስደተኞች ፎረም ዋና ዳይሬክተር አሊ ኖራኒ፣ ‹‹ሁለቱም ፓርቲዎች የስደተኞች ጉዳይ ለአሜሪካ ምን ማለት መሆኑን በመገንዘባቸው ተደስተናል፡፡ በመሆኑም በአሜሪካ የሚገኙ 11 ሚሊዮን ሕገወጥ ስደተኞችን ችግር የምንፈታበት ሌላ አማራጭ ያስፈልገናል፤›› ብለዋል፡፡ የአሜሪካ ኢኮኖሚ የተማረ ገበሬም ሆነ የተማረ መሐንዲስ ያስፈልገዋል ያሉት ኖራኒ፣ ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ሐሳብ ሁለቱም ፓርቲዎች ሊያፈላልጉ ይገባል ብለዋል፡፡

የዲቪ ሎተሪ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1990 የአየርላንድን ስደተኞች መጠንን ለመጨመር ሲሆን፣ ከዚያም የቀድሞዋን የሶቪየት ኅብረትን እንዲሁም አሁን አፍሪካን ተጠቃሚ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ለአፍሪካ 25 ሺሕ ቪዛ ሲሰጥ፣ ለእስያ ዘጠኝ ሺሕ እንዲሁም ለአውሮፓ 16 ሺሕ ቪዛ ተሰጥቷል፡፡

ይህ ሕግ በሴኔቱ ድጋፍ አግኝቶ ከፀደቀ በተለይ በአፍሪካ የሚገኙ የዕድሉ ተጠቃሚዎችን እንደሚጐዳ ተጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያም በዚሁ የቪዛ ፕሮግራም በርካታ ዜጐቿን ወደ አሜሪካ በመላክ በተለይ በውጭ ምንዛሪ ገቢ እየተጠቀመች መሆኑ ይታወቃል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment