Tuesday, December 18, 2012

‹‹በ1953 ዓ.ም. የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አሜሪካኖች ደግፈውት ነበር››

ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ፣ የቀድሞ የጠቅላይ ግዛት እንደራሴና ረዳት ሚኒስትርደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በረዳት ሚኒስትርነት፣ በዋና ዳይሬክተርነት፣ በጠቅላይ ግዛት እንደራሴነትና በአውራጃ ገዥነት አገራቸውንና ወገኖቻቸውን ለ23 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡

በሥራ ላይ በቆዩበት ዘመን ያካበቱትንም ልምድና ዕውቀት አስመልክቶ ለአሁኑ ትውልድ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ይህንንም ያደረጉት ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል አዳራሽ ባካሄደው ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ደጃዝማች ወልደሰማዕት በሕዝብ አገልግሎት ሥራ ላይ ሆነው ከፈጸሟቸውና ለወጣቱ በገለጻ ካስረዱት የአስተዳደርና የልማት ሥራዎች መካከል በጥቂቶቹ ላይ ከታደሰ ገብረማርያም ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ጭሰኞችን ባለርስት ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተካሒዶ ነበር ይባላል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ቢያብራሩልን፡፡ደጃ/ወልደሰማዕት፡- ለጭሰኞችና በገጠርም ሆነ በከተማ ለሚገኙ ሌሎች ወገኖች ሁሉ በነፍስ ወከፍ ግማሽ ጋሻ (20 ሔክታር) መሬት በርስትነት እንዲሰጠው መሬቱንም ማልማት እንዲችል ለአምስት ዓመት ግብርና አስራት እንዳይከፈል የሚገልጽ አዋጅ በ1945 ዓ.ም. ወጣ፡፡ ይህም በሆነ በዓመቱ ማለትም በ1946 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ 100 ኪሎ ሜትር ዙርያ  የሚገኙ አንድ ሺሕ ጭሰኞች አዋጁ የሚፈቅድላቸውን የእርሻ መሬት ለማግኘት እንዲያስችላቸው ተመዘገቡ፡፡ ተመዝጋቢዎችም በከፋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ርስት እንዲሰጣቸው ተደረገ፡፡ ወደተጠቀሰው ጠቅላይ ግዛት ከመንቀሳቀሳቸው አስቀድሞ ሚያዝያ 9 ቀን 1946 ዓ.ም. ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ቀርበው ተሰናበቱ፡፡ ጭሰኞቹ መሬት በርስትነት እንዲያገኙ እንጂ ከነበሩበት ቦታ ተነስተው ቢያንስ የአንድ ወር የእግር ጉዞ ለሚያስፈልገውና መሬቱ ወደተሰጣቸው ጠቅላይ ግዛት ሲሔዱ በቅድሚያ ሊሟላላቸው የሚያስፈልጉ ነገሮች መኖሩን የተገነዘበ ሰው አልነበረም፡፡ አዲስ በሚሰፍሩበትም ቦታ እንደ ክሊኒክ፣ ውኃና መጠለያ የመሳሰሉ አስፈላጊ ዝግጅቶች እንዲሁም መሬቱ ከተሰጣቸው በኋላ ስንቅ፣ የእርሻ መሣሪያና ምርጥ ዘር እንዲቀርብላቸው የተደረገ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የተጠቀሱትን ዝርዝር ነገሮች ለጭሰኞቹ ሊቀርቡላቸው እንደሚገባ ከታወቀ በኋላ ይህንኑ ለማሟላት ምን ዓይነት ጥረት ነው የተደረገው?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- አፄ ኃይለ ሥላሴ ጭሰኞችን ካሰናበቱ ከአንድ ወር በኋላ ጭሰኞቹን ለማስፈር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚረዳ የዕርዳታ ገንዘብ ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓና ሌሎች አገሮች ግንቦት 10 ቀን 1946 ዓ.ም. ተጓዙ፡፡ ሁለት ወር ተኩል የወሰደባቸው የዚሁ አድካሚ ጉዞና ጉብኝት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ዕርዳታ ከመጠየቅ ባሻገር ኢትዮጵያን ከጎበኙዋቸው አገሮች ጋር የማስተዋወቅ፣ በቅኝ ግዛት ስር የሚገኙትን የአፍሪካ አገሮች ነፃ የሚወጡበትንና ስለ ዓለም ሰላም በመነጋገር ላይ ያለመ ነበር፡፡ በዚህም ጉዞአቸው ላይ አሜሪካን፣ ካናዳን፣ ሜክሲኮን፣ ግሪክንና ዩጎዝላቪያን ጎብኝተዋል፡፡ ከዩጎዝላቪያ መሪ ማርሻል ብሮንዝ ቲቶ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከመመስረታቸው በስተቀር የጓጉለትና ለልማት የሚውል የገንዘብ ዕርዳታ ሳያገኙ ሐምሌ 28 ቀን 1946 ዓ.ም. ባዶ እጃቸውን ተመልሰዋል፡፡ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጡ ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ መስከረም 25 ቀን 1947 ዓ.ም. ወደ አውሮፓ አገሮች ጉዞ ጀመሩ፡፡

በዚህ ጉዞ ጉብኝታቸውን በእንግሊዝ አገር ጀምረው የአውሮፓን ዘጠኝ አገሮች እስከ ኅዳር 25 ቀን 1947 ዓ.ም. ከጐበኙ በኋላ አሁንም ለአስፈላጊ የልማት ሥራ የሚውል ዕርዳታ ሳያገኙ ተመለሱ፡፡ በ1951 ዓ.ም. ደግሞ ማርሻል ብሮንዝ ቲቶ ኢትዮጵያን ለሰባት ቀናት ያህል ጐብኝተው የካቲት 5 ቀን ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ ማለትም ሰኔ 17 ቀን 1951 ዓ.ም. በግብፅ ጉብኝት አደረጉ፡፡ ይህንን ጉብኝት ያደረጉበትም ምክንያት ግብፅ ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ጋር ተቀራርባ ስላገኘችው ጥቅም የሚያስገነዝብ ዕውቀት ለመገብየት ነበር፡፡ የግብፅ ጉብኝታቸው እንዳጠናቀቁ ሶቭየት ኅብረት፣ ቼኮዝላቫኪያን፣ ዩጎዝላቪያን፣ ፈረንሣይን፣ ቤልጅንግንና ፖርቱጋልን ጐበኙ፡፡ ሦስቱን ምዕራባውያን አገሮችን የጎበኙበት ዋና ዓላማ በአፍሪካ ስለነበሩዋቸው የቅኝ ግዛቶች ነፃ መውጣት ለመነጋገር ብቻ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከሶቭየት 400 ሚሊዮን ሩብልስ ብድር አገኙ፡፡ በአነስተኛ ወለድ በረጅም ጊዜ የሚከፈለው ብድሩም የሚውለው ጭሰኞችን ባለርስት ለማድረግ ለተጀመረው ሥራ ማከናወኛና ለሌሎች የልማት ተግባራት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ብድር ደግሞ የምዕራብ አገሮችን ያሸበረና ያርበተበተ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ መገኘቱን ሕዝቡ እንዲያውቀው ተደርጓል?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሶቭየት ኅብረት ብድሩን አግኝተው ወደ አገራቸው የተመለሱት ነሐሴ 18 ቀን 1951 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያውያን ተባብረው ለልማት እንዲንቀሳቀሱ ያነሳሳ በአንጻሩ ደግሞ የምዕራቡን ዓለም ያስደነገጠ በታሪካቸው ዘመን ውስጥ ረጅም የተባለለትን ንግግር ነሐሴ 22 ቀን 1951 ዓ.ም. ማታ በሁለት ሰዓት በሬዲዮ ለሕዝባቸው አሰሙ፡፡ በዚሁ ንግግራቸው ላይ ሕዝቡ ተባብሮና በርትቶ ከሠራ ጓዳው፣ ደጁ፣ ጓሮው፣ ሜዳው፣ ሸለቆው፣ ጋራውና ሸንተረሩ ሁሉ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት እንደሚገኝበት በዚህም የተነሳ በዋዛ ፈዛዛ ጊዜን ሳያባክን በየልማት ዘርፉ ላይ ተሰማርቶ እንዲሠራ ቀስቅሰዋል፡፡ በሳምንቱ መስከረም 7 ቀን 1952 ዓ.ም. ቀን በስምንት ሰዓት ለሁለተኛ ጊዜ ለሕዝባቸው በሬዲዮ ባሰሙት ንግግር ላይ ደግሞ ጭሰኞችን ለማንቀሳቀስና ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሚውል በአነስተኛ ወለድና በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚከፈል በቂ ገንዘብ መገኘቱን አበሰሩ፡፡ ስለሆነም መሬት ለሌለው መሬትና መሬቱን ለማልሚያ በአነስተኛ ወለድ የገንዘብ ብድር፤ መሬት ኖሮት ገንዘብ ለሌለው በአነስተኛ ወለድ የገንዘብ ብድር፣ መሬትና ገንዘብ ኖሮት ልማት ላይ ለማዋል ዕውቀቱ ለቸገረው የባለሙያዎች ዕርዳታ የሚሰጥ መሆኑንም አሳወቁ፡፡  

ሪፖርተር፡- የብድሩ መገኘት የአውሮፓ አገሮችን ያሸበረውና ያርበተበተው ለምንድን ነው?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሶቭየት ዩኒየን ለልማት የሚውለውን ከፍ ያለ ገንዘብ በብድር ማግኘታቸውና ገንዘቡንም ሥራ ላይ አውለው ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ ቆርጠው መነሳታቸውን ከንግግራቸው የተገነዘቡት ምዕራባውያን ኃያላን መንግሥታት እንቅስቃሴው ስላስደነገጣቸው እና ስላልተዋጠላቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹እስቲ ይህን ገንዘብ ስትጠቀሙበት እናያለን›› በሚል ማስፈራሪያና ዛቻ በኢትዮጵያ ላይ ከባድ የፖለቲካ ጫናና አለመረጋጋት ለመፍጠር ተባበሩ፡፡ ዛቻቸውንም በግልጽና በሕቡዕ ለመፈጸም ተንቀሳቀሱ፡፡ በተለይም በሐረር የእንግሊዝ ቆንሲል የነበረው ኮሎኔል ፒንክ ‹‹ኃይለ ሥላሴ ከመስኮብ ያመጣውን ገንዘብ ለአማራው ባለርስት ለመስጠትና እናንተን የአማራውን ጭሰኞች ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ለአማራው ባለርስት ተገዢ ሊያደርጋችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ገንዘብ አይሰጣችሁም›› እያለ አብዛኛው ጭሰኛ ወደ ሆነውና በደጋው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ለሚኖረው ኅብረተሰብ ፕሮፖጋንዳውን አስፋፍቶ ቅስቀሳውን አጧጧፈው፡፡

ሪፖርተር፡- በብድር የተገኘውን ገንዘብ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ለሕዝቡ በሬዲዮ ያሰሙትን ንግግር ሥራ ላይ ለማዋል ምን ዓይነት ዕርምጃ ነው የተወሰደው?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- የተጠቀሱትን ጉዳዮች ከየጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴዎች ጋር ሆነው ተግባራዊ የሚያደርጉ 13 ሰዎች ተመረጡ፡፡ ለታሰበው የልማት ሥራ በተፈጥሮ ችሎታቸውና የሥራ ልምዳቸው ብቃት ከተመረጡትም መካከል አቶ ዮሐንስ ጽጌ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር (በኋላ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር) ዶክተር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ የውኃ ልማት ዋና ዳይሬክተር (በኋላ የሥራ ሚኒስትር ቀጥሎም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ)፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ንርአዮ ወልደ ሥላሴ፣ ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት የሕዝብ ደህንነት ዳይሬክተር ወዘተ ናቸው፡፡ አሥራ ሦስታችንም በ1952 ዓ.ም. ጥቅምት መጀመሪያ ሳምንት ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠርተን ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የሥራ መመሪያ ተቀብለናል፡፡ መመሪያውም ‹‹ከአገር ገዥዎች ጋር ሆናችሁ በሕዝብ የሚመረጡ አባሎች የሚገኙበት የልማት ምክር ቤት በየጠቅላይ ግዛቱ እንድታቋቋሙ፣ ለጭሰኞችና ሌሎች መሬትና ሥራ ለሌላቸው ሰዎች መሬትና ለማልሚያ የሚውል ብድር እንድትሰጡ፤ ለዚህም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ መኮንን ሀብተወልድን ሰብሳቢ አድርገን ሰጥተናችኋል፣ ለእንቅስቃሴያችሁ የሚረዳ መመሪያ በጋራ ሆናችሁ አዘጋጁ፡፡›› የሚል ነው፡፡ ሰብሳቢያችን ግን እኛን ሲያወያዩ ብድር የሚሰጥበትን መመሪያ አዘጋጁ፡፡ በመመሪያውም መሠረት ‹‹ገንዘቡ በብድር የተገኘና የሚከፈል ስለሆነ ጭሰኞች ሳይከፍሉ ቢቀሩ አገሪቷ ባለዕዳ እንዳትሆን ጭሰኛው ባለርስቱን ዋስ እየጠራ ብድር እንዲሰጠው›› የሚል ነው፡፡

‹‹ጭሰኛው ባለርስቱን ዋስ እየጠራ›› የሚለው ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ነሐሴ 22 ቀን 1951 ዓ.ም. መስከረም 7 ቀን 1952 ዓ.ም. ለሕዝባቸው በሬዲዮ ካደረጉት ንግግር፣ ለአሥራ ሦስታችን ከሰጡን መሪ ቃል ጋር የማይገናኝ ከመሆኑም ሌላ ሁለት ዓበይት ችግሮችን ያስከትላል፡፡ አንደኛው ችግር ጭሰኛውን በበለጠ ለባለርስቶች ተገዥ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ኮሎኔል ፒንክ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ኅብረተሰቡን ለመቀስቀስና ለሚያካሂደው ፕሮፖጋንዳ አመች ይሆንለታል፡፡

ሪፖርተር፡- መመሪያው ምን ደረጃ ላይ ደረሰ?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- ሁላችንም መመሪያውን ይዘን ወደ የተመደብንበት ጠቅላይ ግዛት ተንቀሳቀስን፡፡ እኔም የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛትን ድርሻ ይዤ ወደ ሐረር አቀናሁ፡፡ እንደደረስኩም መመሪያውን በወቅቱ የጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ለነበሩት ለደጃዝማች ክፍሌ እርገቱ አስረከብኩ፡፡ ወዲያውኑ የአውራጃና የወረዳ ገዥዎች ታላላቅ የአገር ሽማግሌዎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተጠሪዎች የተሳተፉበት ስብሰባ ተካሂዶ መመሪያው በንባብ ተሰማ፡፡ ሐሳብም እንዳቀርብ ተጋበዝኩ፡፡ በዚህም ጊዜ እኔ ይህንን መመሪያ ስለማልስማማ ሪፖርቴን ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ እሄዳለሁ ብዬ ተናገርኩ፡፡ ስብሰባው ከሰዓት በኋላ እንዲቀጠል ተቀጥሮ እንደራሴው ይዘውኝ ወደ ቢሮአቸው ወሰዱኝና ‹‹እንዴት አልስማማም ትላለህ? ትክክል አይደለህም? ስለዚህ ከሰዓት በኋላ ለምናደርገው ስብሰባ ላይ ታረም›› አሉኝ፡፡ እኔም ከሰዓት በኋላ ስብሰባውን ሳልቀጥል አዲስ አበባ መጥቼ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ሪፖርት አደረግኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ጭሰኞችን ባለርስት የማድረግ ብቻ ነበር የወቅቱ የትኩረት አቅጣጫ ወይስ ሌላ የተከናወነ የልማት እንቅስቃሴ አለ?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- አገሪቱ በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ነበረች፡፡ ከእንቅስቃሴዎችም መካከል በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኘው 500 ጋሻ መሬት ላይ ሰፋፊ የመንግሥት እርሻ ልማት ተካሄደ፡፡ የተትረፈረፈ ምርትም ተገኝቶ ነበር፡፡ በርካታ ትራክተር፣ ግሬደርና ሎደር የመሳሰሉና ለእርሻ አገልግሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችና መሣሪያዎች ከዩጎዝላቪያ መጥተው ሐዋሳ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የዩጎዝላቪያ ኤክስፐርቶችም በብዛት ነበሩ፡፡ ሐዋሳ ላይ ይህ እንዲሆን የተደረገው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው በማሠልጠኛ ጣቢያነት እንዲያገለግልና በዚያው ልክ ደግሞ የእርሻ ልማቱ በይበልጥ እንዲስፋፋ ለማድረግ ነበር፡፡ የተረሱና ወደ ኋላ የቀሩ ሕዳጣን ብሔረሰቦችን የልማቱ ተቋዳሽ ለማድረግ እንዲችል በማጀቴ፣ በዝዋይ፣ በገዋኔ፣ በጋምቤላ፣ በማንዱራ ከተሞች የትምህርት፣ የጤናና ሌሎችም የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተቋቋሙ፡፡ ለዚህም እውን መሆን የአውራጃዎች የውስጥ አስተዳደር አዋጅ ወጣ፡፡

ጭሰኞች፣ መሬት የሌላቸውና ሥራ አጥ ወገኖችን ለእርሻ የሚውል መሬትና ገንዘብ በብድር እየሰጡ የማስፈሩ ሥራ በስፋት ቀጥሏል፡፡ በርካታ ባለሙያዎችም ወደ እስራኤልና ሕንድ ተልከው ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ወደ እስራኤል የሔዱት ባለሙያዎች የሠለጠኑት በኅብረት፣ ወደ ሕንድ ያቀኑት ደግሞ በማኅበረሰብ ሥራ ላይ ትኩረት ያደረገ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡ ሌላው መዘንጋት የሌለበት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በሚያደርጉት ንግግሮች ላይ የኅብረት ሥራና ሶሾሊዝም የሚሉ ቃላትን ሳይጠቅሱ አያልፉም ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገራቸው ግን በአውሮፓ አገሮችና በአሜሪካኖች ዘንድ አልተወደደም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ለምንድነው ያልተወደደው?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- ከቲቶ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ማጠናከራቸው፣ ከሶቭየት ዩኒየን ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው፣ በዚህም ያልተጠበቀ ብድር ማግኘታቸውና ከሚካሄደው የልማት እንቅስቃሴ አንጻር አገሪቱ ከሶቭየት ብሎክ ወይም ከሶሻሊስት ጎራ ልትቆራኝ ትችላለች ከሚል ስጋት ይመስለኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣናቸው ወይም ከዙፋናቸው የሚወርዱበትን ቀን በናፍቆት ሲጠባበቁ እንደቆዩ ነው የተረዳኝ፡፡ ይህም ሆኖ ከዙፋናቸው ለማውረዳ የሚያስችል መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በ1953 ዓ.ም. ታህሳስ ላይ ተካሄደ፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎች በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሲመካከሩ አማካሪው የአሜሪካ አምባሳደር ነበሩ፡፡ ይህም ሊታወቅ የተቻለው ሻምበል ደረጀ ኃይለ ማርያም ባለጎማ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ እየነዳ የቤተ መንግሥቱን አጥር በር ሰብሮ ሲገባ አምባሳደሩ እዚያው ነበሩ፡፡ በመካከሉ ተኩስ ሲከፈት የአምባሳደሩ ሾፌር ሲሸሽ አምባሳደሩ ግን በእግራቸው ወደ ኤምባሲያቸው ሔዱ፡፡ ከዚህ አንጻር ሲገመገም የ1953ቱን መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አሜሪካኖች ደግፈውት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን እንዴት ሊደርሱበት ቻሉ? በዚያን ጊዜ የእርስዎ የሥራ ድርሻና ኃላፊነት ምን ነበር፡፡

ደጃ/ወልደሰማዕት፡-  እኔ በዚያን ወቅት የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ረዳት ሚኒስትር ነበርኩ፡፡ ቀደም ሲልም የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት የሕዝብ ደህንነት ዳይሬክተር ነበርኩ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ከሶቭየት ኅብረት በተገኘው ብድር ጭሰኞችን ባለርስት ለማድረግ በተካሔደው እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ በዚህና በሌላም ባለኝ ተደራሽነት አማካይነት ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የወላይታ አውራጃ ገዥ ለምን ሆንኩ ብለው ሸፍተው ነበር ይባላል፡፡ ለመሆኑ የት ነው የሸፈቱት?

ደጃ/ ወልደሰማዕት፡- በመጀመሪያ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በሦስት ሰዓት እንድትገኝ ተብሎ ተነገረኝ፡፡ እኔም ንጉሠ ነገሥቱ ዘወትር እንደሚያደርጉት የኤግዚቢሽን ዝግጅት ምን ላይ እንደደረሰ ሊጠይቁኝ ነው የሚል ሐሳብ አደረብኝ፡፡ በዚህም የተነሳ የዝግጅቱን ሂደት የሚያሳዩ ወረቀቶች ይዤ ስሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መልካም ፈቃድ የወላይታ አውራጃ ገዥ ሆነሃል ብለው ነገሩኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን ከነገሩኝ በኋላ ፈገግ ብለው ሊጨብጡኝ የዘረጉትን እጅ መዳፍ ሳልነካ ለጊዜው ለጊዜው ስሜቴ ስለተነካ ገልምጫቸው ወደኋላዬ ተመለስኩና ከግቢው ወጣሁ፡፡ ወዲያው ኮተቤ አካባቢ ወደሚገኘው ለገጣፎ ወንዝ በመሄድ ለሁለት ሌሊትና ለአንድ ቀን ተኩል ያህል ሸፈትኩ፡፡ እልሄ በርዶልኝ ወደ ቤቴ ስመለስ ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ቀርቤ ከባድ ተግሳጽ ከተቀበልኩ በኋላ አዲሱን ሥራዬን ሄጄ ጀመርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ዕድሜዎ ስንት ነው?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- 88 ሆኖኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ምግብ ነው የሚመገቡት?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- የቀረበልኝን ሁሉ በትንሽ ትንሹ እበላለሁ፡፡ ቆሎ በጣም እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአልኮል መጠጥስ?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- ዊስኪ ትንሽ ፉት እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ስፖርት ያዘወትራሉ?

ደጃ/ወልደሰማዕት፡- በእግር መሄድን ነው የማዘወትረው፡፡ እንዳያሰንፈኝ ብዬ መኪናዎቼን ሁሉ ሸጬ ጨርሼያለሁ፡፡ ስለሆነም የትም ብሄድ በእግር ጉዞ ነው የምጠቀመው፡፡

http://www.ethiopianreporter.com