Sunday, December 2, 2012

አዲስ አበባ በአማርኛ ሥነ-ግጥም- ብርሃኑ ገበየሁ /ረዳት ፕሮፌሰር/


አዲስ አበባ

ምክንያቱን ጠይቆና መርምሮ መድረስ ያልቻለ አንድ ግጥም ነክ ጥያቄ፣ ‹‹ሸገር አዲሳባ ገጣሚዎቻችንን ምን ያስቀየመቻቸው፣ የነፈገቻቸው ነገር ቢኖር ነው? ማሕሌተ ሸገር፣ ማሕሌተ አዲስ ይሉ ቅኔ የሌለው፤ ጠላ እንኳን ወግ ደርሶት በየአድባራቱ ስንት እልፍ ደብተራ ማሕሌተ ገንቦ በሚዘርፍበት አገር›› የሚል ነው፡፡

የከተማ ውበት በነዋሪው ሰው ልብና ቀልብ በሚፈስ ቅኔ፣ ከአንደበታቸው በሚንፎለፎል መወድስ ወይም ማሕሌት ይገለጣል፤ ከብርቅ ሕንፃዎቹ፣ ከማራኪ መንገዶቹና ከሐውልቶቹ በተጨማሪ፡፡ እናም ታላላቆቹ ከተሞች ከባለቅኔዎቻቸው ምናብና ብዕር በተጠለቁ፣ ትውልድ ሁሉ በሚዘምራቸው ቅኔያት ሞገሳቸው ይልቃል፣ ዝናቸው ይነገራል፡፡ ጥቂት ይባሉ እንጂ አዲስ አበባም ይህን ወግ አላጣችውም፤ በየዘመኑ የመጡ ገጣምያን ለአድናቆትም ለትዝብትም ተቀኝተውባታል፡፡

እንጦጦ ላይ ሆኜ አዲስን ሳያት
ባለፈርጥ ኮከብ መስላ አገኘሁዋት፡፡ 
(በእምነት ገብረ አምላክ)

የዚህ መንቶ ደራሲ፣ የአዲሳባ፣ የሚያውቃት አዲሳባ ውበት በድንገት ያነቃው ያነሆለለው ባለቅኔ ነው፡፡ ከግጥሙ ዓውደ ንባብ ተነስተን ስናሰላስል፣ የገጣሚው አድናቆት የመነጨው ከምሽት ትዕይንት ነው ማለት ይቻላል፤ ለምን ቢሉ አንድም ለአድናቆቱ ማንጸሪያ፣ ለአድናቆቱ መያዣ የመረጠው ምስል ‹‹ባለፈርጥ ኮከብ›› ነውና፤ አንድም ኮከብ በምናባችን የሚከሰተው የብርሃን ምሥል ነውና፡፡ አገላለጹ ውብ ነው፤ ምስሉም የተባና የደመቀ፡፡ እናም በእነዚህ ስንኞች ‹‹አዲስ›› ለገጣሚው ብቻ ሳይሆን ለተደራሲውም አዲስ ውበት ትሆናለች፡፡

በአማርኛ ሥነ ግጥም የአዲስ አበባ ምስል ተደጋግሞና ተዘውትሮ የሚገኘው በትዝታና ናፍቆት ግጥሞች ውስጥ ነው፤ ወይም በስደት ግጥሞች ውስጥ፡፡ የሰው ልጅ ገነትም ሆኖ የትውልድ ቀየውን፣ በተራዘሚውም አገሩንና ወንዙን አይረሳም እንዲል ሐዲስ፤ የአማርኛ ገጣምያን ባሕር ማዶ ለትምህርት ወይ ለሥራ በስደት ሲኖሩ፤ ቃሉ ይለያይ እንጂ የዝማሬያቸው ቃና የቅኔያቸው መንፈስ፤


ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አገርም እንደሰው ይናፍቃል ወይ

የሚል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የልብና የቀልብ መሸፈት ከአያሌ ስሜቶች ሊቀሰቀስ ይችላል፤ ከናፍቆትና ከትዝታ፣ ከመከፋትና ከመገፋት፣ ከባይተዋርነትና ከብቸኝነት፣ ከማንሜነትና ከራስ ጥል፡፡ በዚህ ረገድ የመንግሥቱ ለማና የገብረክርስቶስ ደስታ ግጥሞች ሁነኛ የዘመናቸው ወኪሎች ናቸው፡፡

የኪነጥበብ መንገድ ብዙ ነው፤ የገጣሚያንም መንፈስና ስሜት እንዲሁ ከአያሌ ስሜቶች ይወለዳል፤ ከብዙ እውነቶች ይመነጫል፤ ብዙ ጊዜም የዘመን መንፈስ፣ አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም አንደበት ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ በጥቅሉ፣ በልቦለድና በግጥም በተለይ አዲሰ አበባ የማኅበረ ባህላዊ ቀውስ መገለጫ መቼት ሆና በተደጋጋሚ መሳሏ፡፡ ምናልባትም፣ ሥነ ጽሑፋችን እራሱን እንደ አንድ የጥበብ ዘርፍ አጎልምሶ በዘመናዊነት መንገድ መጓዝ በጀመረበት ዘመን የማኅበረሰባችን አስተዳደር፣ ወግና ልማድ የላሸቀበት ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር በዚያ ዘመን የነበሩት ደራስያንና ገጣምያን አዲስ አበባን ከውጫዊ ገጽታዋ ይልቅ በሰብዓዊና ማኅበራዊ እውነቷ የመግለጽ ዝንባሌ የበረታባቸው፡፡ ስለዚህም የ1950ዎቹና 1960ዎቹ ገጣምያን አዲስ አበባን በማኅበሩ ውስጥ የሚታዩ ቅራኔዎች፣ ድቀቶች፣ ቀውሶችና የሰብዕና መንጠፍ መናኸሪያና መገለጫ ደሴት አድርገው ስለዋታል፡፡ የዘመኑን ገጣምያን መንፈስና እውነት ሊወከሉ ከሚችሉ ግጥሞች መካከል ቀጥዬ ጥቂት ስንኞችን የምዘርፍበት የጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹አይ መርካቶ›› አንዱ ነው፡፡

ባለፀጋ እንደመረዋ ረብጣ አፍኖት ሲያጉረመርም 
የከሰረ እንደፈላስፋ በቀን ቅዠት ሲያጉረመርም
የኔ ብጤ ጠብሻን መትቶት በየጢሻው ሲያስለመልም
ቸርቻሪ ዝርዝሩን ቋጥሮ ቅንጣቢውን ሲቃርም
የወር ሸማች ስንቁን ጭኖ ሲመርቅና ሲረግም
ማጅራት መች ከሁዋላው ጢሻውን ዘሎ ሲያዘግም
ከዚህ ሰብሮ እዚያ ሰብሮ፣ ያዝ ሲባል ሲሸሽ ሲያጣጥር
ካማኑኤል ራጉኤል ሾልኮ ዶሮ ማነቂያ ዳር
ከመስኪድ እስከበረንዳ፣ ከአራተኛ እስከ ነፍስ ይማር
የኡኡታው የጡሩንባው፣ የጩኸቱ የፊሽካው ሳግ
የሰው የመኪና የከብት፣ የፍግ የቁሳቁስ ትንፋግ
ሲገፋተር ሲመዣረጥ፣ ላቦት ለላቦት ሲላላግ
ትንፋሽ ለትንፋሽ ሲማማግ
አባ ሽብሩ መርካቶ፣ ያለውን በገፍ አጣጥቶ

ግጥሙ ላይ ላዩን ሲታይ ለመርካቶ የተደረሰ መወድስ ይመስላል፡፡ ዳሩ ግን በቅርበት ሲመረመር ከመወድስነት ይልቅ ትዝብት ጠንከር ሲልም በማኅበሩ ባህልና አስተዳደር ላይ የተሰነዘረ ትችት መቼም መርካቶ በስመ ሃዳሪነት ሰዎቹን፣ ልማዳቸውንና ሥርዓታቸውን ይወክላልና መሆኑ ይገለጣል፡፡ መርካቶ ከፍ ብለን በጠቀስናቸው ስንኞች ከሰለጠነ የገበያ ማዕከልነት ይልቅ ሥርዓትና ደንብ የሌለበት የትያትር መድረክ፣ የአእምሮ ሚዛናቸውን የሳቱ ሰዎች የሚተራመሱበት መንደር፣ የቆሻሻ መጣያ፣ የከብቶች ማጎሪያ ገሃነም ምስል ነው የሚያመጣው፡፡ ይህ ገሃነማዊ ምስልም የከተማና በውስጡ የሚኖር ሥልጡን ሕዝብ ባህልና አኗኗር መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡

ምክንያቱን ባላውቀውም፣ ከ1960ዎቹ ወዲህ ላነበብናቸው ብዙ የአገራችን ገጣምያንም አዲስ አበባ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ መዲናነቱዋ፣ ከንግድና ዲፕሎማሲያዊ መናኸሪያነቷ ይልቅ በውስጡዋ አፍና የያዘችው መጢቃ ሥልጣኔ፣ ማኅበራዊ ደዌና ሰብዓዊ ድቀት እጅጉን ገዝፎ ይታያቸዋል፡፡ ግጥሞቻቸውም ይህንኑ አሉታና ስሞታ ያስተጋባሉ፡፡ ምናልባት ይህ ሁኔታ ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ በኢትዮጵያውያን ልብና ልቡና ነግሶ የነበረው ፍርሃት፣ ተስፋ ቢስነትና ምሬት መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ የዚህ ዘመን ግጥሞች መራራ ማኅበረ-ባህላዊ ሂሶች፣ ራስ ወቀሳዎች ይበዙበታል፡፡ ጨለማማውን ክፍል ያገዝፋሉ፤ ቀርነቱን ያተኩራሉ፤ ድቀቱን ያንራሉ፤ ይህ በመሆኑ ገጣሚዎቹ ሊወቀሱ አይገባቸውም አንድም ያልኖሩትን አልጻፉምና ሀቅን አልሸፈጡምና አንድም ወቀሳቸው ወደ ውጭ የተሰነዘረ ስሞታ ሳይሆን የራስ ለራስ ሂስ ነውና፤ አንድም መልኩና መገለጫው ልዩ ልዩ ቢሆንም የሁሉም ድምጸትና መንፈስ ከአንድ የስሜትና የአተያይ ምንጭ የተጨለፈ ነውና፡፡ አነዚህን መሰሎቹ ስሜቶችና እውነቶች ከተገለጡባቸው ማኅበረ-ባህላዊና ሰብዓዊ ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ፤ ሴተኛ አዳሪነትና ጎዳናዊነት፤ የነዋሪዎቹ ጋጠ ወጥነትና ሕገ ወጥነት፣ የንጽህናና ጥዳት ጉድለት፤ ወዘተ ይገኙባቸዋል፡፡ የሚከተሉት ከልዩ ልዩ ገጣምያን ሥራዎች የተመዘዙ ጥቂት ስንኞች ይህንን እውነት ያሳያሉ፡፡

ኮረኮንች፤ ጉድጓድ የውኃ ቋት፤
የአዲስ አበባ አስፓልት
(አለሚቱ ደመና፣ ‹‹የአዲሳባ አስፋልት››) 

የከተማችን ሰው አውቄአለሁ ይላል
በየመንገዱ ዳር ሲከፍል ይታያል    

****************

ማዘጋጃ ቤቱ ፊት ለፊቱ አግጦ
እዩት ማህል ፒያሳ ገልቦ ተቀምጦ?
(ሊቁ ወንድሙ፣ ግጥም ‹‹73››

አንች የፈጠርሻቸው፤
የመንገድ ልጆችሽ፤ ኗሪ በርቃናቸው፣ በባዶ ሆዳቸው፤
ካንቺው ጋር ሲባዙ፣ ሲያቃስቱ ከርመው፣
(ፈቃደ አዘዘ፣ ‹‹ፈንጭ አዲስ አበባ!!››)

አየኋት አዲሳባ ቀሚሷን አሳጥራ 
በመሰላል ጫማ በጥልፍ ተገፍትራ
አየኋት አፍሪካ አዳራሽ፣ ቁማ በጨለማ
አየኋት ፍል ውሃ በብርድ ተኮራምታ
ኃላፊ-አግዳሚ ሽንጥ ገዛ ብላ
ዲቃላ አጥብቃ ራት ልታበላ
(ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ‹‹ባላሳየኝ››)

አዲስ አበባ በዘመናዊው አማርኛ ሥነ ግጥም ውስጥ ይዛ የምትገኘው ምስል በድርበቡ ይህን ይመስላል፡፡ መቼም ሰው የሚኖረው በተስፋም ጭምር ነውና በመጪው ጊዜ ከገጣሚዎቻችን ምናብና ብዕር እንደ ናርዱስ የሚጣፍጥ መዐዛ ያላት፣ በጥበብ የተጌጠች ውብና ስያሜዋን የምትመስል አዲስ አበባን ምስል እናገኝ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡-
ሐቻምና ያረፉት ጸሐፊው ነፍስ ኄር አቶ ብርሃኑ ገበየሁ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ሺሕ ዓመት ስትቀበል “አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሌኒየም” በተሰኘው መድበል ላይ ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡
http://ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment