Wednesday, July 30, 2014

በረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ ላይ ምስክሮች ተሰሙ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን የበራራ ቁጥሩ ET-702 ቦይንግ 767 አውሮፕላንን የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. በመጥለፍ ወንጀል በሌለበት ክስ የተመሠረተበት ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ ላይ፣ ዓቃቤ ሕግ ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ምስክሮቹን አሰማ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በረዳት አብራሪው ላይ የመሠረተውን የአውሮፕላን መጥለፍ ወንጀልና የአውሮፕላንን ደኅንነት አደጋ ላይ መጣል ወንጀል ክስ በመመርመር ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛ ወንጀል ችሎት፣ ጣሊያናዊውን ዋና አብራሪ ሚስተር ፓትሪዚዮ ባርቤሪንና በወቅቱ የበረራ አስተናጋጅ ኃላፊ የነበሩትን ጨምሮ የስምንት ምስክሮችን ቃል ሰምቷል፡፡
የዓቃቤ ሕግ የመጀመርያ ምስክር የሆኑት ዋና አብራሪ ሚስተር ፓትሪዚዮ ባርቤሪ ሲሆኑ፣ አውሮፕላኑን ከኢትዮጵያ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ እስካረፈበት ያለውን ሒደት አስረድተዋል፡፡
ዋና ፓይለቱ ለፍርድ ቤቱ እንደመሰከሩት መነሻቸው አዲስ አበባ ሆኖ ከሌሊቱ ለሰባት ሰዓት ሃያ ጉዳይ ነው፡፡ ከነበረራ አስተናጋጆች 202 መንገደኞችን ይዘዋል፡፡ መድረሻው ጣሊያን ሮም በመሆኑ ጉዞአቸውን በሰላም መጀመራቸውን፣ አንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃም መጓዛቸውንና የበረራ መስመራቸው በሱዳን ካርቱም አድርጎ ወደ ጣሊያን ሮም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹መፀዳጃ ቤት ደርሼ መጣሁ ብዬው ሄድኩኝ፡፡ ወዲያው የመፀዳጃ ቤቱን በር ከውጭ ቆለፈው፡፡ በመቀጠልም የአየር እጥረት ሲከሰት በመንገደኞች ላይ በሚታይ የመድከምና የመጨናነቅ ስሜት ጊዜ የሚደረገውን የኦክሲጂን ጭንብል መንገደኞች እንዲያደርግ ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን  ትዕዛዝ አስተላለፈ፤›› ያሉት ዋና አብራሪ ፓትርዚዮ፣ እሳቸውም መፀዳጃ ቤት እንደሆኑ ጭንብሉን ማድረጋቸውን  ገልጸዋል፡፡ ኃይለ መድኅን ጭንብል እንዲያደርጉ ያዘዘው እውነትም የአየር እጥረት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ፣ ከፍተኛ የአየር ድምፅ ይኖር ስለነበር መሰማማት እንደማይቻል ተናግረው፣ እሱ ግን ዝም ብሎ በመናገሩ ምንም ድምፅ እንዳልነበረ አስረድተዋል፡፡

የመፀዳጃ ቤት ከውስጥ በሚቆለፍ ጊዜ አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች ብቻ የሚያውቁት ከውጭ መክፈቻ (ኮድ) እንዳለ የገለጹት ዋና አብራሪው፣ ወደ ሮም የሚሄድ በቢዝነስ ክላስ ውስጥ የነበረ ሌላ አብራሪ ስለነበር እሱን ጠርተው እንዲከፍተው  ሲጠይቁት፣  ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን ግን ይኼንን ሁሉ በመቆጣጠር ኮዱን ቀይሮ ዘግቶት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ዋና ፓይለቱ የመፀዳጃ ቤቱን በር በኃይል በእርግጫ ሲመቱት በአማርኛ ‹‹ብታርፉ ይሻላችኋል፣ እከሰክሰዋለሁ፤›› ሲል ሁሉም ፀጥ ማለታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ ለአምስት ሰዓታት ብቻውን እያበረረ እያለ ጥገኝነት ይጠይቅ እንደነበር ያስረዱት ዋና አብራሪው፣ የስዊዘርላንድ ጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ ተቆጣጣሪዎች ሲጠይቃቸው እንዲያርፍ እንደፈቀዱለት አስረድተዋል፡፡ ለ40 ደቂቃ ያህል በስዊዘርላንድ አየር ላይ ማንዣበቡንና የጫነው 1.2 ቶን ነዳጅ ሊያልቅ ሁለት ደቂቃ ብቻ ቀርቶት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ጄኔቭ ካረፉ በኋላ ለ1፡40 ሰዓት አውሮፕላን ውስጥ ቆይተው የጄኔቭ ፖሊሶች ገብተው ‹‹እጅ ወደላይ›› ሲሏቸው ረዳት አብራሪው ኃይለ መድኅን በአብራሪው በኩል ባለው በር በገመድ ወርዶ እጁን መስጠቱን ዋና አብራሪው በአስተርጓሚ የሰጡትን ምስክርነታቸውን አስረድተዋል፡፡
የበረራ አስተናጋጆች ኃላፊዋ በበኩላቸው በሰጡት የምስክርነት ቃል፣ ዋና አብራሪው ወደ መፀዳጃ ቤት እንደገቡ ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን እራት በልቶ እጁን ሊታጠብ ከገባ በኋላ በሩን ቆልፎ አልከፍት ማለቱን ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡ አራትና አምስት ጊዜ ቢደውሉ ሊከፍትላቸው እንዳልቻለ የተናገሩት ኃላፊዋ፣ ራሱ ደውሎ፣ ‹‹ስሚ እኔ ነኝ ወደ ሮም ይዣችሁ የምሄደው፣ ፓይለቱ እንዳይታይ ደብቂው አለኝ፤›› ካሉ በኋላ፣ አውሮፕላኑን እንዳወዛወዘው ገልጸዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ደውለው ወደ ሚላን ሂድ እንዳሉትም እንደነገሯቸው ምስክሯ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለ40 ደቂቃ በአየር ላይ ሲሽከረከር ደውዬ ምን መሆንህ ነው ስለው ሴኩሪቱ ቦታ ስለሌለና ማረፊያ እስከሚለቀቅለት በአየር ላይ እንዲጠብቅ እንዳዘዙት ምላሽ ሰጥቶኛል፤›› በማለት መስክረዋል፡፡ ሌሎቹ ምስክሮች በወቅቱ በአውሮፕላኑ ውስጥ ስለነበረው ፍርሐትና ድንጋጤ ጨምሮ፣ ተመሳሳይነት ያለው ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
በረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን ድንገተኛ ጠለፋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሰበት ኪሳራ 253,336 ዩሮ መሆኑ በክሱ እንደተጠቀሰ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com