Wednesday, July 30, 2014

‹‹ዶ/ር ኢንጂነር›› በሚል ሐሰተኛ ማዕረግና ማጭበርበር የተጠረጠሩት አቶ ሳሙኤል ከኬንያ ተላልፈው ተሰጡ

‹‹ዶ/ር ኢንጂነር›› እንደሆኑ በመግለጽና በማሳሳት እንዲሁም በዚህ ሐሰተኛ የትምህርት ማዕረግ ተጠቅመው ባለሀብቶችን በማጭበርበር የተጠረጠሩት አቶ ሳሙኤል ዘሚካኤል፣ ኬንያ ውስጥ ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ ማክሰኞ ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
አቶ ሳሙኤል የተያዙት በኬንያ የፀጥታ ኃይሎች በዋና ከተማዋ ናይሮቢ  መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ግለሰቡ ሊያዙ የቻሉት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለፌደራል ፖሊስ በጠየቀው መሠረት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ የዓለም አቀፍ ወንጀሎችና የኢንተርፖል መምርያ ከኬንያ አቻው ጋር ባደረገው ግንኙነት አቶ ሳሙኤል ተይዘው ተላልፈው መሰጠታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
አቶ ሳሙኤል የተጠረጠሩበት የማጭበርበር ወንጀል ይፋ ከተደረገ በኋላ በግለሰቡ መበደላቸውን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያሳወቁት ግለሰቦች መኖራቸውን፣ በወቅቱም ግለሰቡ ከአገር እንዳይወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የቦሌ ቅርንጫፍ ደብዳቤ ተጽፎ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪው ግለሰብ ግን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ሳይሆን በየብስ ትራንስፖርት በድንበር አቋርጠው ሳይወጡ እንዳልቀረ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡
በግለሰቡ የማጭበርበር ወንጀል ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጹ ታዋቂ ባለሀብቶችና ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቃላቸውን እንደሰጡም ምንጮች አስረድተዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል ዘሚካኤል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙና በመቀጠልም አውስትራሊያ ከሚገኘው ካምቤራ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መቀበላቸውን፣ ከአሜሪካ ዝነኛው ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በምህንድስና ዘርፍ ማግኘታቸውን በተደጋጋሚ ጊዜ ለተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎችና በተገኙባቸው መድረኮች ገልጸዋል፡፡
ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ የማነቃቂያ ንግግሮችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመገኘት ሲያቀርቡ እንደነበርና በዚህም ለበርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አርዓያ ሆነው ለመታየት ሲሞክሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የንግድ ፈጠራ ውድድር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚያስተላልፈው የፈጠራ ውድድር ፕሮግራም ላይ ዳኛ በመሆን ሥራ ፈጣሪዎችን ሲዳኙ መቆየታቸውም አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሬዲዮ የግለሰቡን የኋላ የትምህርት ታሪክ በማጥናትና የተማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎችን በመጠየቅ ግለሰቡ ሐሰተኛ የትምህርት ደረጀና ስያሜ ለራሳቸው በመስጠት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ነው ግለሰቡ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ሳይሰጡ ከአገር የወጡት፡፡ ይሁን እንጂ የኬንያ ፖሊስ ከሳምንት በላይ ካሰራቸው በኋላ ለኢትዮጵያ ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment