Wednesday, July 16, 2014

ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የምርመራ መዝገቡ መዘጋቱ ሕገወጥ አካሄድ መሆኑ ተገለጸ

-‹‹አሁን ታስረው የሚገኙበት ሁኔታ ሕገወጥና አደገኛ ነው›› የተጠርጣሪዎች ጠበቃ
በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በክስ ላይ የሚገኙት ሦስት ጋዜጠኞችና ስድስት ጦማርያን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ፖሊስ ‹‹ምርመራዬን ስለጨረስኩ መዝገቡ ይዘጋልኝ›› በማለት መዝገቡ እንዲዘጋ ማድረጉ ሕጉን ያልተከተለና አደገኛ መሆኑን ጠበቃቸው አስታወቁ፡፡
ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬና ጦማሪያንና የሕግ መምህር ዘለዓለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃኔ ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የሚቀርቡበት ዕለት ነበር፡፡ እንደወትሮው ሁሉ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ ጓደኞቻቸውና የተለያዩ የችሎት ታዳሚዎች በጠዋት ማልደው በፍርድ ቤት ግቢ የተገኙ ቢሆንም፣ እስከ ቀኑ 5፡30 ሰዓት ድረስ ፖሊስም ሆነ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ችሎቱ አልመጡም፡፡ ከ5፡30 ሰዓት በኋላ ሌሎች ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ተጠርጣሪዎቹና ፖሊስ ችሎት ቆይተው ሲወጡ፣ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን፣ ደንበኞቻቸው ፍርድ ቤት መቅረብ አለመቅረባቸውን ለማጣራት የዕለቱን ተረኛ ዳኛ ለማነጋገር ገቡ፡፡ ጠበቃው ስለደንበኞቻቸው ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ፣ ፖሊስ ምርመራውን መጨረሱን በማሳወቅ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ መዘጋቱን ሲያስረዳቸው፣ ‹‹እንዴትና በምን ሁኔታ?›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ከመዘጋቱ ውጪ ምንም ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
እስረኛ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የምርመራ መዝገቡ ሊዘጋ እንደማይችል የሚናገሩት ጠበቃ አመሐ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ መሆናቸው፣ በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ምንም ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ በመሆኑ ድርጊቱ ሕገወጥና አደገኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ፖሊስ ምርመራውን ካጠናቀቀ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ይዞ በመቅረብ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳትና ክስ እስከሚመሠረትባቸው ድረስ በዋስ እንዲቆዩ ወይም የሕግ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት ስለሚቆዩበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠት እንደነበረበት አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ባልሰጠበት ሁኔታ ተጠርጣሪዎቹ ባሁኑ ወቅት የት እንዳሉ እንደማይታወቅ የሚናገሩት ጠበቃው፣ በወንጀል ሕጉና በሕገ መንግሥቱ በተጠሰው አካልን ነፃ የማውጣት መብት (ሐቢየስ ኮርፐስ) ክስ ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
በሌላ የምርመራ መዝገብ የተካተቱት ጦማሪያን ማህሌት ፋንታሁን፣ አቤል ዋበላና በፈቃዱ ኃይሉ ደግሞ ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዎቹም ሆኑ መርማሪ ፖሊስ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡
ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች ‹‹የመብት ተሟጋች ነን›› ከሚሉ የውጭ ኃይሎች ጋር በሙሉ ሐሳብና ገንዘብ በመስማማት ሕዝብን የማተራመስ፣ አገርንና መንግሥትን የማፍረስ ዘገባ በኢንተርኔትና በተለያዩ ድረ ገጾች ያልሆነ መረጃ ሲያስተላልፉ ተገኝተዋል በሚል ፖሊስ ሚያዝያ 17 እና 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ለሁለት ጊዜ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ከተፈቀደለት በኋላ፣ በሦስተኛው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ውስብስብና ድርጊቱም የሽብርተኝነት ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀን እንዲፈቀድለት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን በመጥቀስ ተፈቅዶለት መመርመር ላይ መሆኑን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ 78 ቀናት ሞልቷቸዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment