Sunday, July 20, 2014

በጋዜጠኞቹና በጦማሪያኑ ላይ የቀረበው ክስ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አስነሳ

‹‹የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ስለተጠቀሰ ብቻ ሽብር ተፈጽሟል ማለት አይቻልም›› የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች
ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ የቀረበባቸው ክስ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ዋስትና የማግኘት መብት የሚጋፋ በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤትን ጠየቁ፡፡ 
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ዋስትና ማግኘት መብት መሆኑን ደንግጎ ሳለ፣ በጠቅላላው በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ በመሆናቸው ዋስትና አይፈቀድላቸውም ማለት፣ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር ስለሚቃረን ወይም ስለሚጣረስ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መላክ እንዳለበት ጉዳዩን ማየት ለጀመረው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ጠበቆቹ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ 
በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 20(5) በሽብርተኝነት የወንጀል ክስ የቀረበበት አካል፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን ሰምቶ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ተከሳሹ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ የሚደነግግ ቢሆንም፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበው ክስ ግን የሽብርተኝነት ወንጀል የሚጠቅስ ባለመሆኑ ዋስትና ሊከበርላቸው እንደሚገባ ጠበቆቹ ተከራክረዋል፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀጽ 3 ድርጊቶችን ዘርዝሮ ያስቀመጠ መሆኑን ማለትም መደራጀት፣ ማቀድ፣ መፈጸምና ሌሎች ነጥቦችንም ያካተተ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አንቀጽ 4 ከመጥቀስ ሌላ፣ ተጠርጣሪዎቹ ምን እንዳደረጉ ጠቅሶ ያቀረበው ነገር ስለሌለ ዋስትና ሊከለከሉ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ጠቅሶ ክስ ስለመሠረተ ብቻ ሽብር ተፈጽሟል ማለት እንደማይቻል ጠበቆቹ በተደጋጋሚ ጠቅሰው፣ የተጠርጣሪዎቹ ዋስትና እንዲከበር የጠየቁ ቢሆንም ዓቃቤ ሕግ ግን ተቃውሟል፡፡
ዓቃቤ ሕግ የጠበቆቹን አቤቱታ የተቃወመው በሕገ መንግሥቱ ዋስትና መብት መሆኑ የተደነገገ ቢሆንም፣ ዋስትና የሚከለከልበትን ድንጋጌም መሥፈሩን በማስረዳት ነው፡፡ አንዱ ዋስትና የሚከለክለው በሽብርተኝነት ወንጀል መሳተፍ መሆኑን ያስረዳው ዓቃቤ ሕግ፣ ተጠርጣሪዎቹም ክስ የተመሠረተባቸው በሽብርተኝነት ተግባር ላይ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑን ጠቁሞ ዋስትናቸውን ተቃውሟል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስማት ለሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹም እስከዚያው ድረስ የተነበበላቸውን ክስ በደንብ ተረድተው፣ ክሱን መቃወም ወይም አለመቃወማቸውን ለመግለጽ በቀጠሮው ቀን እስከሚቀርቡ ድረስ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ከተጠርጣሪ ሶሊያና ሽመልስ በስተቀር ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች ማለትም ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬ፣ እንዲሁም ጦማሪያን ዘለዓለም ክብረት፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፍ ብርሃኔና አቤል ዋበላ ሚያዝያ 17 እና 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ጊዜ ፖሊስ ስለተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሲያስረዳ የነበረው መደበኛ የወንጀል ሕጉን በመጥቀስ ነበር፡፡ ከሁለት ቀጠሮዎች በኋላ የምርመራ ሒደቱ ወደ ሽብርተኝነት የሚወስድ በመሆኑና በተጠርጣሪዎቹ ላይ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ መሠረት ምርመራ መካሄድ እንዳለበት ፖሊስ ገልጾ፣ የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ በወቅቱ ተጠርጣሪዎቹ በሦስት የምርመራ መዝገቦች ተለያይተው ይቀርቡ ስለነበር፣ ጉዳዩንም ሲመለከቱ የነበሩት ሁለት ዳኞች ነበሩ፡፡ አንደኛው ዳኛ 28 ቀናት ሲፈቅዱ ሌላኛው ዳኛ 15 ቀናት ፈቀዱ፡፡ ቅዳሜና እሑድ ይታይ የነበረው የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ በቀጣይ ሁለተኛ ቀጠሮ በሁሉም መዝገቦች ላይ 28 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቀዱ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ መዝገቡ ሲቀርብ ወደ 14 ቀናት ዝቅ በማለቱ የነበራቸው ሰፊ የቀናት ልዩነት ማጥበብ ተችሎ ወደ አንድ ቀን ዝቅ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም፣ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ባይቀርብም ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቦ ምርመራውን ማጠናቀቁን በመግለጽ፣ የምርመራ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ ተዘግቶለታል፡፡ ከስድስት ቀናት ቆይታ በኋላ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. አንድ ተጠርጣሪ በሌለችበትና ዘጠኙ ባሉበት የተመሠረተባቸው የሽብርተኝነት ክስ ተነቦላቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ያነበበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ በህቡዕ ተደራጅተዋል፡፡ የህቡዕ ቡድኑ ሊቀመንበር፣ የውጭ ጉዳይ ክፍል፣ የሕዝብ ግንኙነት፣ የዘመቻና ምርምር አስተባባሪዎች በሚል የሥራ ክፍፍል አድርገዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብርና አመፅ ተግባር ለማስወገድ ስትራቴጂ ቀርፀዋል፡፡ ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸውን በማደራጀት ከግንቦት 2004 ጀምሮ፣ የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ባመቻቸው የህቡዕ አመራሮችና ቡድንን መልዕክቶች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ከአገር የመገናኛ አውታሮች ውጪ ማስተላለፍ የሚቻልበትን ዘዴ መቀበላቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
የአመጽ አመራርና የሕዝብ ቅስቀሳ ዘዴዎች፣ የተቀጣጣይ መሣሪያዎች አሠራርና አጠቃቀም ሥልጠና በመውሰድና በመስጠት የድርጅቱ ሁለንተናዊ የትግል አማራጭን የራሳቸው ስትራቴጂያዊ አማራጭ በማድረግ፣ ከግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ግንኙነት መፍጠራቸውም በክሱ ተካቷል፡፡
በግንቦት 7 መመርያ የግንቦት 7 ዕጩዎች በግንኙነት ወቅት መከተል ስለሚገባቸው ተግባርና ‹‹እኔ የግንቦት 7 አባል ነኝ›› የሚል የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን መግለጫንና የሽብር ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች፣ የግንቦት 7 ልሳን ለሆነው ኢሳት ሬዲዮ ጣቢያና ቴሌቪዥን ሪፖርት ማድረጋቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ኦነግ ከሚባለው አሸባሪ ድርጅት የፖለቲካ ፕሮግራሙንና ዓላማውን ለማሳካት ያወጣውን ዕቅድ መመርያ በማድረግና በመንቀሳቀስ ተሳታፊ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment