Wednesday, June 12, 2013

ተጠርጣሪዎች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የቀረጥ ነፃ ዕቃዎች ተጠቅመዋል ተባሉ

-እነ አቶ መላኩ ፈንታ ወደ ማረሚያ ቤት እንዛወር አሉ
-ከአንድ ተጠርጣሪ 1.3 ሚሊዮን ብር መያዙ ተገለጸ
-ሦስት ተጠርጣሪዎች ሲፈቱ ሁለት አዲስ ተጠርጣሪዎች ታሰሩ 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በሚገኙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ኃላፊዎችና ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ግምታቸው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ ለአሥር ሆቴሎች ግንባታ የሚውሉ ከቀረጥ ነፃ የግንባታ ዕቃዎች ለሌላ ዓላማ ውለው ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ 12 ተጠርጣሪዎች በሚገኙበት የምርመራ መዝገብ ላይ ሰኔ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. መርማሪ ቡድኑ ላለፉት 14 ቀናት በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሠራውን የምርመራ ሥራ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ አስረድቷል፡፡ 

የአቶ ገብረዋህድ ባለቤት የኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይ እህት ወ/ሮ ንግሥቲ ተስፋይና ልጃቸው አቶ ሀብቶም ገብረመድህንን በዋስ መፍታቱን ለችሎት የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ የምርመራ መረቡን ከአዲስ አበባና ከናዝሬት አርቆ በመዘርጋት በክልሎች ላይ ጭምር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ላለፉት 14 ቀናት በአራጣ ማበደር ምክንያት ክስ ተመሥርቶባቸው ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጓል ከተባሉት ሰነዶች ውስጥ የተወሰኑትን መሰብሰቡን፣ 10 ሆቴሎች ለመገንባት በሚል ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ አገር ውስጥ የገቡና ግምታቸው ከ50 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የግንባታ ዕቃዎችን ለሌላ ዓላማ መዋላቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማግኘቱን አስረድቷል፡፡ 
በተከለከለ ፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ ወደ አገር ውስጥ በገባ ሲሚንቶ ምክንያት ክስ ተመሥርቶባቸው እንዲቋረጥ የተደረገበትን ሰነድ፣ በኮንትሮባንድ ቀረጥ ሳይከፈልበት ወደ አገር ውስጥ የገባ የሕክምና መሣሪያ ተይዞ ክስ ቢመሠረትበትም፣ ክሱ እንዲቋረጥ መደረጉን ተከትሎ የተሰበሰቡ ሰነዶችንና ከቀረጥ ጋር በተያያዘ፣ ክስ ከተመሠረተባቸው በኋላ ክሱ እንዲቋረጥ ከተደረገባቸው 60 መዝገቦች ውስጥ 24ቱን መሰብሰቡንም መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ጨምሮ እንዳስረዳው፣ ከጥቆማ አበል ክፍያ ጋር በተያያዘ ያላግባብ የተመዘበረ የመንግሥት ገንዘብ የሚያሳይ የመንግሥት ሰነድ ሰብስቧል፡፡ ከምርመራ ሥራው ጐን ለጐን ቀጥታ የዓይን ምስክሮችን ቃል ተቀብሏል፡፡ 
ምርመራው ውስብስብ፣ ሰፊና እርስ በርሱ የተጠላለፈ በመሆኑ በተሰጠው ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ 36 ክስ የተቋረጠባቸው መዝገቦች፣ ለአምስት ሆቴሎች ከቀረጥ ነፃ የገቡ የግንባታ ዕቃዎችን ሰነድ፣ ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ዕቃዎች ቁጥጥር እንዳይደረግባቸው ትዕዛዝ ተላልፎላቸው የነበሩ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን ለመመርመር ክልል ድረስ በመሄድ በመሥራት ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ሰብስቦ ለተንታኝ ባለሙያ ቢሰጥም ውጤቱን አለመቀበሉን፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ሀብት ሕጋዊ አስመስሎ መያዝን በሚመለከት ከአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የሚሰበሰብ ማስረጃ እንደሚቀረው ቡድኑ ገልጿል፡፡ የአቶ ገብረዋህድ ባለቤት ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይን በሚመለከት ያሸሹት ሰነድ በከፊል የተያዘ ቢሆንም፣ በከፊል የሚገኝበት ፍንጭ በመገኘቱ ለመፈለግ ጊዜ እንደሚፈልግ፣ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ሰነዶች መሰብሰብ ስለሚቀረውና የምስክሮችን ቃል ጨርሶ ለመቀበል ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት መርማሪ ቡድኑ ለሦስተኛ ጊዜ ለችሎቱ አመልክቷል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ላለፉት 14 ቀናት በተጠርጣሪዎቹ ዙሪያ የሠራውን የምርመራ ሥራ ለችሎቱ ካስረዳ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ መርመሪ ቡድኑ ሠራሁ ባለው የምርመራ ሥራና ለቀሪው ሥራ ያስፈልገኛል ስላለው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ለተጠርጣሪዎች ዕድሉን ሰጥቷል፡፡
በጠበቃ የተወከሉት አቶ ገብረዋህድ መርማሪ ቡድኑ ሠራሁትና ይቀረኛል ባለው ላይ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ 90 በመቶ ሥራውን አከናውኗል፡፡ የቀረው የኦዲት ሪፖርትና ጥቂት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ማስረጃዎችንም ሊያጠፉበት የሚችሉበት ምንም ዓይነት መንገድ ስለሌላቸው በሚቀረው የምርመራ ቦታ እንዳይደርሱ ገደብ ተደርጐባቸው የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ጠበቃቸው ጠይቀዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ መሆናቸውን በመጠቆምም ፍርድ ቤቱ እልባት እንዲሰጣቸው ራሳቸው ጠይቀዋል፡፡
የወንጀለኛ ሕግ ቁጥር 59(2) የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ይቻላል ከሚል በስተቀር ምንም ዓይነት ገደብ እንዳልተጣለበት በመግለጽ፣ ሕግን የመተርጐም ሥልጣን የፍርድ ቤት በመሆኑ ሊተረጐም የሚገባው ተጠርጣሪውን በሚጠቅም መንገድ በጠባቡ መተርጐም እንዳለበት በማመልከት፣ በደንበኛቸው ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባና በዋስ ሊለቀቁ እንደሚገባቸው ለችሎቱ ያመለከቱት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኦዲተር የአቶ በላቸው በየነ ጠበቃ ናቸው፡፡
መርማሪ ቡድኑ የሕጉን ክፍተት በመጠቀም ዝም ብሎ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ መሆኑን የገለጹት ጠበቃው፣ ኦዲት ተጠናቆ ሪፖርት እስከሚቀርብ ድረስ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ፣ ተጠርጣሪ ደግሞ ዝም ብሎ በመታሠሩ የአዕምሮ መላሸቅና ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ ስለሚያደርስ፣ ቤተሰብ ወደመበተንና መልሶ ለመንግሥት ሸክም ሊያደርግ ስለሚችል ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ጉዳዩን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ ችግሮቹ የት የት እንዳሉ ለይቶ ማወቁን እንዳሳወቀ የጠቆሙት ጠበቃው፣ ደንበኛቸው ውጤቱ እስከሚታወቅ ድረስ ታስረው መቆየት እንደሌለባቸው በመግለጽ የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ 
   እሳቸው በማያውቁትና በማይመለከታቸው ጉዳይ መታሰራቸው አግባብ እንዳልሆነ፣ ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱት እሳቸው ብቻ መሆናቸውን በመጠቆም፣ መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ለሦስተኛ ጊዜ 14 ቀናት መጠየቁ አግባብ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል በማሳወቅ በዋስ ተለቀው ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል፡፡
ቀደም ባሉት ሁለት ቀጠሮዎች እናታቸው በጠና መታመማቸውን ለችሎት በማስረዳት በዋስ ሆነው እንዲያስታምሙ መጠየቃቸውን ያስታወሱት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ረዳት አቶ ተስፋዬ አበበ፣ እናታቸው ካረፉ አምስት ቀናት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡ የእናታቸውን መሞት ሲገልጹ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በመቃወም፣ ከምርመራው ጋር እንደማይገናኝና ተያያዥነት እንደሌለው በመግለጽ ችሎቱ እንዲያስቆምለት ጠይቋል፡፡
ችሎቱ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ተቃውሞን ካዳመጠ በኋላ፣ ‹‹ተጠርጣሪ ስለቤተሰቡ ሲያስረዳ በምርመራ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፣ ምርመራ ይደናቅፋል ካላችሁ፣ ከበድ ያለ ነገር ቢገጥማችሁ ምን ልትሆኑ ነው?›› በማለት ከጠየቀ በኋላ፣ የመርማሪ ቡድኑን ተቃውሞ ውድቅ አድርጐ ተጠርጣሪው ንግግራቸውን እንዲቀጥሉ አዟል፡፡ ተጠርጣሪው በእሳቸው ዙሪያ ያለው ቢሯቸውም ሆነ ቤታቸው መፈተሹን አስረድተው፣ መርማሪ ቡድኑ ቀረኝ ከሚለው ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው በማስረዳት፣ ንብረትና ቤተሰብ ያላቸው በመሆኑ በዋስ ተለቀው ሐዘናቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ በመታመማቸው በፖሊስ ሆስፒታል እየታከሙ መሆኑንና ቀደም ሲል ያክሟቸው የነበሩ ሐኪሞች ካላከሟቸው ከሕመማቸው ሊፈወሱ እንደማይችሉ ለችሎቱ ያመለከቱት የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት የአቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ጠበቆች ናቸው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ባለፉት ቀጠሮዎች ስለሠራቸውም ሆነ ይቀሩኛል ስላላቸው የተለያዩ ሥራዎች አቶ ነጋን የማይመለከቱ መሆናቸውን የገለጹት ጠበቆቻቸው፣ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ባሉት ችሎቶች ፍርድ ቤቱ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ የሠራውን ነጥሎ እንዲያቀርብ ያዘዘው ቢሆንም፣ አሁንም በጥቅሉ በመጥራት ማቅረቡንና አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ ‹‹ደንበኛችን የፈጸሙት ወይም የተጠረጠሩበት ወንጀል የትኛው ነው? የቀረበው በጥቅል በመሆኑ ለይተን ማወቅ አልቻልንም፤›› በማለት የጠየቁት የአቶ ነጋ ጠበቆች፣ ከቀረጥ ነፃ የግንባታ ዕቃ ከገባላቸው አሥር ሆቴሎች የአምስቱ ሰነድ መያዙንና አምስቱ መቅረቱን መርማሪ ቡድኑ ቢገልጽም፣ ከእሳቸው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለና እሳቸውም ሊያጠፉት እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡ 36 የተቋረጡ የክስ መዝገቦችንም በሚመለከት የሚገኙት በመንግሥት እጅ በመሆኑ ከአቶ ነጋ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
የሙያተኞች የትንተና ውጤት ይቀራል ከተባለ ሁሉም ሰነድ ተሰብስቦ ማለቁን የገለጹት የአቶ ነጋ ጠበቆች፣ ተጠርጣሪው በማንኛውም መልኩ እንቅፋት ሊሆኑ ወይም ሙያተኞቹን ሊያባብሉ እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡ የሰው ምስክሮች እነማንና በማን ላይ ምን እንደሚመሰክሩ መርማሪ ቡድኑ ግልጽ ያደረገው ነገር ስለሌለም ለማባበል፣ ለማስፈራራትም ሆነ ለማጥፋት እንደማይችሉም አክለዋል፡፡
አቶ ነጋ የልብ ሕመምተኛ በመሆናቸውና በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በመታመማቸው በፖሊስ ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ መሆኑን ደግመው ያስታወሱት ጠበቆቻቸው፣ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው በሆስፒታሉ ዶክተሮች ቢነገራቸውም፣ ሕመማቸውን በሚያውቁ ሐኪሞች ሳይሆን በሆስፒታሉ ሐኪሞች በድጋሚ እንዲታዩ ከማድረግ ውጪ፣ ሕመማቸውን በሚያውቅ ሐኪም አለመመርመራቸውን አስረድተዋል፡፡ ሕመማቸውን በሚያውቁ ሐኪሞች እንዲመረመሩና አስፈላጊውን መድኃኒት እንዲያገኙ እንዲታዘዝላቸው ለችሎቱ አመልክተዋል፡፡ መታገድ የሌለበትና አላግባብ የታገደ የባንክ ሒሳብም እንዲለቀቅላቸው የአቶ ነጋ ጠበቆች በተጨማሪ አመልክተዋል፡፡ 
‹‹በእርግጥ ተጠርጣሪው እሳቸው ናቸው? እኔ ሳነጋግራቸው ተፈጸመ ከተባለው ወንጀል ጋር እሳቸውን የሚያገናኛቸው ነገር የለም፤ እስካሁንም ቃላቸውን እንዲሰጡ የጠየቃቸው የለም፤›› ያሉት ደግሞ የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም የአቶ ምሕረተአብ አብርሃ ጠበቃ ናቸው፡፡ አቶ ምሕረተአብ ያላቸው አንድ የትራንስፖርት ተሽከርካሪ ብቻ መሆኑን፣ ከባለሥልጣኑ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ሲካሰሱ መቆየታቸውን፣ እሳቸውና ባለሥልጣኑ የሚተዋወቁት በመካሰስ መሆኑን የጠቆሙት ጠበቃው፣ ምናልባት በስመ ሞክሼ ሊሆን ስለሚችል ስማቸው ምሕረተአብ አብርሃ ሐጐስ መሆኑን በመግለጽ እንዲጣራላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ምሕረተአብ ሀብታም አለመሆናቸውንና መርማሪ ቡድኑ በሚያደርገው ምርመራ ላይ ምንም የሚያደርጉት ተፅዕኖ እንደሌለ በመግለጽ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስተዳድሩ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹14 ቀናት አይደለም 14 ወራት ቢፈቀድ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር የሚያገናኝ ምንም ነገር አይገኝም፤›› በማለት አቶ ምሕረተአብ ራሳቸው ተናግረው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ 
አቶ ሙሌ ጋሻው፣ አቶ አሞኘ አወቀ፣ ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይና አቶ ተወልደ ብርሃንም እንደሌሎቹ ሁሉ መርማሪ ቡድኑን ተቃውመው የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ሰኔ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀባቸው በአቶ መላኩ ፈንታ የምርመራ መዝገብ ሥር የሚገኙት ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡ መርማሪ ቡድኑ አቶ መላኩ ፈንታ፣ መርክነህ ዓለማየሁ፣ እሸቱ ወልደ ሰማያት፣ አስመላሽ ወልደማሪያም፣ ከተማ ከበደ (የኬኬ ባለቤት)፣ ስማቸው ከበደ (የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት) እና ዶክተር ፍቅሩ ማሩ (የአዲስ ልዩ የልብ ሕክምና ሆስፒታል ባለድርሻ) ላይ ባለፉት 14 ቀናት የሠራውን የምርመራ ሥራና የሚቀሩትን ሥራዎች (ከእነ አቶ ገብረዋህድ ምርመራ መዝገብ ጋር ተመሳሳይ ሥራ ነው) ለችሎቱ በመግለጽ ለቀሪ ሥራዎቹ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቋል፡፡ 
መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ ሪፖርቱን ካሰማ በኋላ፣ የተጠርጣሪ ጠበቆች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአቶ መላኩ ፈንታ ጠበቃ እንደተናገሩት፣ ከመርማሪ ቡድኑ ሪፖርት የተረዱት አቶ መላኩ ምንም የተጠረጠሩበት ወንጀል አለመኖሩን ነው፡፡ ምክንያታቸውም ባለፈው ቀጠሮ መርማሪ ቡድኑ ሁሉንም ነገር ማሰባሰቡን በመግለጹ ማድረግ የነበረበት ክስ መመሥረት ነው፡፡ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ መፍቀድ ሳይሆን ክስ እንዲመሠርት ማዘዝ እንዳለበት ጠበቆቹ አሳስበዋል፡፡
አቶ መላኩ በተደጋጋሚ ተጠይቀው ሁሉንም በመመለሳቸው መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ጥያቄ እንደሌለው የተናገሩት ጠበቆቹ፣ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ወይም ከማረፊያ ቤት ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ አቶ እሸቱ ወልደ ሰማያትም የአቶ መላኩን ክርክር በመደገፍ የሚፈለግባቸው የተጠርጣሪነት ቃል ብቻ መሆኑን ገልጸው ዋስትና ጠይቀዋል፡፡ 
አቶ መርክነህ ባለፈው ቀጠሮ ከተናገሩት በተጨማሪ ሌላ የሚናገሩት እንደሌላቸው ገልጸው፣ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ አቶ መርክነህ በወንድማቸው አማካይነት 1.3 ሚሊዮን ብር ወደ ደቡብ ክልል በመውሰድ መሬት ውስጥ ተቀብሮ መገኘቱን አሳውቋል፡፡
አቶ አስመላሽ ወልደማሪያም፣ የመርማሪ ቡድኑ ሪፖርት በጅምላ በመሆኑ ማን ምን እንደሠራና ምን እንደቀረበት ስለማይታወቅ፣ ፍርድ ቤቱ አንድ ቦታ ላይ ውሳኔ ካልሰጠ ዝም ብሎ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡ ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን ሳይቀሩ ከዓመት በላይ ጥናት የተደረገበት መሆኑን በገለጹበት ሁኔታ ለሦስተኛ ጊዜ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁን እንደማይቀበሉ ገልጸው ዋስትና ጠይቀዋል፡፡
የኬኬ ድርጅት ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ በቀን 11 ዓይነት የተለያዩ ኪኒኖችን እንደሚወስዱ ጠበቃቸው ገልጸው፣ የወንጀል ሕግ 59(2)ን ፍርድ ቤቱ ለተጠርጣሪው በሚጠቅም መልኩ በመተርጐም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ምክንያታቸውም ሕጉ ክፍተት ስላለበት የሚል ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ለይቶ ያቀረበው ዝርዝር ድርጊት ስለሌለ ዋስትና የማይፈቀድላቸው ከሆነ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
የኢንተርኮንቲኔንታል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ የተጠረጠሩት ለሆቴል ሥራ ከቀረጥ ነፃ በገቡ ቁሳቁሶች መሆኑንና ይኼንንም መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን ስላጠናቀቀ በዋስና እንዲፈቱ ጠበቃቸው ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ 
የአዲስ የልብ ሕክምና ሆስፒታል ባለድርሻ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ሲሚንቶ ከሚያስመጡ ነጋዴዎች ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ፣ ከማንም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው፣ ምርመራው የተጠናቀቀና በመንግሥት እጅ ያለ በመሆኑ፣ ዋስትና የሚያስነፍጋቸው ነገር ባለመኖሩ ተለቀው በሙያቸው ዜጐችን እንዲያገለግሉ ጠበቆቻቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በእነ አቶ መላኩ መዝገብ ያካተታቸውና ሰኔ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ወላይታ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው የተናገረው የአቶ መርክነህ ወንድም አርሶ አደር ብርሃኑ ዓለማየሁና እሳቸውን ተባብረዋል የተባሉ ዘመዳቸው አቶ ገተሮ ሀጥዬ ናቸው፡፡
መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ እንደገለጸው በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ዳሞት ሶሬ ወረዳ የሚገኙት የአቶ መርክነህ ወንድም ዘመዳቸው ከሆኑት የዳሞት ሶሬ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት የመንገድ ፕሮግራም የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ገተሮ ሀጥዬ ጋር በመሆን፣ ከ1.3 ሚሊዮን (1,3,000,090) ብር በላይ ጉድጓድ ምሰው ቀብረው መያዛቸውን በማስረዳት፣ ለቀሪ ምርመራ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡ የአቶ መርክነህ ወንድም የሚናገሩት በወላይትኛ ቋንቋ መሆኑን በማሳወቃቸው፣ ፍርድ ቤቱ አስተርጓሚ ተዘጋጅቶ በአዳሪ እንዲታይ በማዘዝ፣ የአቶ ገተሮን ክርክር አድምጧል፡፡
አቶ ገተሮ የአቶ ብርሃኑ ዘመድ በመሆናቸው ብቻ ከመያዛቸው በስተቀር፣ ምንም እንደማያገናኛቸውና አቶ ብርሃኑ ዘመዳቸው ማን እንደሆነ ሲጠየቁ የእሳቸውን ስም በማስመዝገባቸው ብቻ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰኔ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. በቤታቸው እንዳሉ በኮሚሽኑ ደኅንነቶችና በፌዴራል ፖሊስ መያዛቸውንና ቤታቸው መፈተሹን የገለጹት ተጠርጣሪው፣ ስለ ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኀን ከሚሰሙት ውጪ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በሕግ ባለሙያ እገዛ ተደርጐላቸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ 
መርማሪ ቡድኑ በእነ አቶ ገብረዋህድ መዝገብ የቀረቡ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የተቃውሞ አቤቱታ በመቃወም ድርጊቱን አባሪና ተባባሪ ሆነው መፈጸማቸውን፣ በርካታ ሰነዶች ቢሰበሰቡም በርካቶች እንደሚቀሩ ከባለሥልጣናቱ፣ ከነጋዴዎች፣ ከደላላዎችና ከትራንዚተሮች ጋር በመመሳጠር የፈጸሙት ድርጊት መሆኑን፣ አቶ ነጋ ሕክምና አለመጠየቃቸውን፣ አቶ ምሕረተአብን ያወቃቸው ገና በተያዙበት ዕለት መሆኑንና የተጠረጠሩትም በታክስ ስወራና ቀረጥ ጋር በተያያዘ መሆኑን፣ ሁሉም ተጠርጣሪዎች አባሪና ተባባሪ በመሆን የፈጸሙት ድርጊት መሆኑን በማስረዳት፣ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጐ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ አመልክቷል፡፡ በእነ አቶ መላኩ ፈንታም መዝገብ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸውን በመግለጽ ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጐ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድ ጠይቋል፡፡ 
ፍርድ ቤቱ የሁሉንም ተከራካሪ ወገኖች ክርክር ግራና ቀኝ ካዳመጠ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና ጊዜ ውድቅ አድርጐታል፡፡ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ የጠየቁትንም፣ በሕግ ያልተደገፈ ጥያቄ መሆኑንና አንድ ተጠርጣሪ ለምርመራ አመቺ በሆነበት በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ሕጉ እንደሚያዝ በመግለጽ፣ ጥያቄያቸውን እንዳልተቀበለው ችሎቱ ገልጿል፡፡ የአቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔርን ሕመም በሚመለከት ‹‹የጤንነት ጉዳይ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው›› በማለት በአገር ውስጥ አቅም በፈቀደው መሠረት ሕክምና ማግኘት እንዳለባቸው ለኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የሚያከናውነው ሥራ መዝገቡን በማስቀረብ ምን እንደሠራና እንዳልሠራ፣ ምን እንደቀረውና በማን ላይ ምን እንደሠራ እየመረመረውና እየተመለከተው መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በመጨረሻም መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መፈቀዱን ገልጾ፣ እነ አቶ ገብረዋህድ ሰኔ 17፣ እነ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ ሰኔ 18 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  
http://www.ethiopianreporter.com