Tuesday, May 21, 2013

እስር ቤት የጠፋ ወጣትነት







 ‘’አንተ ሰው አትሆንም፤የማትረባ ነህ፤ አሰድብከን የእኛንም አንገት ነው ያስደፋሃን፤አንተን በመውለዳችን እንዲያውም እንፀፀታለን፡፡ብለው ተናገሩኝ፡፡’’ ይህ የዳንኤል ትውስታ ነው፡፡ከቤተሰቦቹ ጋር ለተፈጠረው አነስተኛ ግጭት የተሰጠ ምላሽ-ዳንኤልም ሆነ ቤተሰቦቹ ግጭቱን ለመፍታት በእርጋታ ለመነጋገር እና ለመወያየት መፍትሄ ለመፍጠር አልሞከሩም፡፡የቤተሰቦቹ ንግግር ዳንኤልን በሚፈልጉት መንገድ አላረቀውም፡፡ይባስ ብሎ ከቤት ወጣ፡፡ከታክሲ አስከባሪ ጋር ተጋጨ፡፡በግጭቱ የታክሲ አስከባሪው ጥርስ ወለቀና ለሶስት ወራት እስር ተዳረገ፡፡በዳንኤል መታሰር  ቤተሰቦቹ አቋማቸው አልተቀየረም፡፡የተበላሸውን ነገር የሚያስተካክሉበትን መንገድ አላሰቡም፡፡ይባስ ብሎ  ዳንኤልን መጠየቃቸውን አቆሙ፡፡
በዳንኤል መታሰር ራሱ ዳንኤል የተሰማው ፀፀት እና ድንጋጤ ከቤተሰቦቹም ጋር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ነገር ግን በዳንኤል የእድገት ሂደት ውስጥ ቀድሞ ይህን ማስቀረት ይቻል የነበረ ቢሆንም አልተደረገም፡፡ችግሮችን በእርጋታ በውይይት መፍታት፤ስድብ እና ግጭትን ማስወገድ፤ስሜታዊነትን መቆጣጠር የሚችልበትን የህይወት ልምድም አጣ፡፡በአንድ ቀን በተፈጠረ ስህተት በትምህርቱ፤ቤተሰባዊ ህይወቱ እና ከማህበረሰቡ ጋር ባለው ግንኙነት እንዲሁም በህይወት ግቡ(አላማው) ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ወደ ሚያሳድረው ማረሚያ ቤት ለመግባት ተገደደ፡፡

በወጣትነት መታሰር ላይ ለዳጉ አዲስ  ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም የሰራሁትን እና  በሸገር 102.1 የተላለፈውን ፕሮግራም እዚህ ማዳመጥ ይችላሉ፡፡



በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ለእስር ይዳረጋሉ፡፡ይህ ማለት ግን ሁሉም ጭልጥ ያሉ ወንጀለኞች ናቸው ማለት አይደለም፡፡እንደ ዳንኤል ሁሉ አነስተኛ ግጭቶች፤ስርቆት፤ደንብ መተላለፍ፤በህግ የተከለከሉ አደንዛዥ እፆችን መጠቀምም ሆነ ይዞ መገኘት፤ስድብ እና ለከፋን የመሳሰሉ ጥፋቶች ወጣቶችን ለእስር ይዳርጋሉ፡፡በኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ ደግሞ  እድሚያቸው 9 ዓመት እስከ 15 ዓመት ያሉትን በወጣት ጥፋተኝነት ከ15 ዓመት በላይ ያሉትን እንደማንኛውም አዋቂ ጉዳያቸው እንዲታይ ያደርጋል፡፡እድሚያቸው ከ15 አመት በታች ያሉ ወጣቶች  ፍርድ ቤቱ የጥፋቱን ክብደት፣ የጥፋተኛውን የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም የቅጣቱን አስጠንቃቂነት ልዩ ግምት ውስጥ በማስገባት አስተማሪ የሆነ ቅጣት ይጥላል፡፡እድሚያቸው ከ15 አመት በላይ የሆኑ ወጣቶች ግን በህ ፊት እንደ አዋቂዎች ይታያሉ፡፡

 ዳንኤል ወደ ማረሚያ ቤት ሲገባ ቀድሞ ከለመደው አኗኗር የተለየ ሁኔታ ነበር የገጠመው፡፡ በድንጋይ በተገነባው የማረፊያ ክፍል ግድግዳዎች ላይ “የጨካኞች ቅጣት አረመኔዎችን ይፈጥራል፡፡”  “ጊዜ እና ሁኔታ እስኪፈቅድ ጠላትህን ተሸከመው::” የሚሉ ጥቅሶች  እንደተፃፉ ያስታውሳል፡፡የመኝታ ክፍሎች እና ቦታ፤የመዝናኛ አማራጮች፤የሌሎች ታራሚዎች ወንጀል እና ልምድ ቀድሞ ከለመደው እና ከኖረበት እጅጉን የተለየ ነበር፡፡ዳንኤል በማረሚያ ቤት ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተዋውቋል፡፡ ከእንጀራ በሹሮ የተሰራ ደያስ ፒዛ ተመግቧል፤ብርጭቆ ድርድር እና ደቦቃ ተኝቷል(ደቦቃ አንድ ሰው ወደ ላይ ሌላው ወደ ታች ተደርጎ ብዙ ሰዎች የሚተኙበት መንገድ)በሰው ፊት ሽንቱን ሸንቷል፡፡ሁሉንም ፈቅዶ ባይሆንም አንድ ጊዜ የሰራው ስህተት አስገድዶታል፡፡
የአብነቱ አቡሽ የሜክሲኮው ግሩም በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደ ዳንኤል ሁሉ ለእስር ተዳርገዋል፡፡አቡሽ ከእስር ሲወጣ ተስቦ በሽታ ይዞት ነበር፡፡ግሩም ከካዛንቺሱ ፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ ቃሊቲ እና ዝዋይ ድረስ ተጉዟል፡፡ የአቡሽ ህይወት እንዳይመለስ ተበላሽቷል፡፡የሲጋራ፤ጫት እና መጠጥ ሱሰኛ ሆኗል፡፡የሰፈር ጓደኞቹ መልከ መልካም እና ጎበዝ ተማሪ እንደ ነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ዛሬ ግን ማልዶ የሚነሳው ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ሳይሆን ከመጠጥ ቤት ጎራ ለማለት ነው፡፡በስርቆት ላይ ከተሰማሩ ጓደኞቹ ጋር በመያዙ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል፡፡ያደገበት ሰፈር ሰዎች የቀድሞውን ጎበዝ ተማሪ ረስተውታል፡፡በአካባቢው ለተፈጠረ ስርቆትም ሆነ አምባጓሮ በተጠያቂነት ቀድመው ስሙን ይጠራሉ፡፡ሲያዩት ይፀየፋሉ፡፡ሲርበው ምግብ ይችሩት እንጂ ህይወቱን ለማስተካከል አንዳቸውም የሞከሩት ነገር የለም፡፡ግሩም መታሰሩ ከቤተሰብ አቆራርጦታል፡፡ዛሬ ህይወትን አንድ ብሎ ለመጀመር ቢታገልም ቀላል አይደለም፡፡የመፃህፍት ንግድ፤አስተናጋጅነት እና የታክሲ ረዳትነት ሞክሯል፡፡በሙከራው ውስጥ በልፋቱ ውስጥ የተሻለ ነገን ይ ፈልጋል፡፡ግን በአንድ ወቅት በወጣትነት ስሜት በመጠጥ ቤት በተፈጠረ ግጭት የሰው ጥርስ ማውለቁ ያስከፈለውን ዋጋ አይዘነጋም፡፡”ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ የሂሳብ አስተማሪ መሆንን እመኝ ነበር::” የሚለው ግሩም ትምህርቱ የተቋረጠው ከ ዘጠነኛ ክፍል ነው፡፡
የ23 አመቱ ወጣት በረከት ሰፈር ውስጥ በተፈጠረ የቡድን ፀብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእስር ሲዳረግ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ከአንድ ወር በላይ በእስር የቆየው በረከት አህቱ፤አባቱ እና ጓደኛው ይጠይቁት ነበር፡፡ሲገባ የደነገጠበትን የማረሚያ ቤት ሲወጣ ተላምዶታል፡፡ዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን ያቋረጠው ወጣት እንደገና በአነስተኛ ስርቆት ተመልሶ ለእስር ተዳረገ፡፡መጀመሪያ የታሰረበት ፖሊስ ጣቢያ ባያስደነግጠውም የቃሊቲው ማረሚያ ቤት እንግዳ ሆኖበታል፡፡ከበርካታ ቀናት እስር በኋላ ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት በፍርድ ሂደቱ ወቅት የታሰሩበትን የጊዜ ርዝመት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በይብቃ አሰናበታቸው፡፡ከጓደኞቹ ጋር ሰው ፈነከተ፡፡ለሶስተኛ ጊዜ ለእስር ተዳረገ፡፡በዋስትና ሲወጣ ‘’ድጋሚ እታሰራለሁ ብዬ አላሰብኩም’’ ይበል እንጂ ለአራተኛ ጊዜ ታሰረ፡፡ቤተሰቦቹ ሰለቻቸው፡፡መጠየቃቸውንም አቆሙ፡፡በረከት አልታረመም፡፡አምስት…ስድስት….እያለ ለአስራ ስምንት ጊዜ እንደታሰረ አጫውቶኛል፡፡ ማህበረሰቡ ዳንኤል፤አቡሽ፤ግሩምና በረከትን ወልዶ ሲያሳድግ መልካም መልካሙን ሁሉ ቢመኝም ስኬታማ አልሆነም፡፡ቤተሰቦቻቸው የልጆቻቸውን ስብዕና በሚገባ አልቀረፁም፡፡ምናልባትም እንዴት መቅረፅ እንዳለባቸው አያውቁ ይሆናል፡፡
ወጣቶች በማንኛውም አጋጣሚ የሚፈጥሯቸው ስህተቶች ትምህርታቸው፤ህይወታቸውና ህልማቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው፡፡በማንኛውም አጋጣሚ ይህ ቢፈጠር ግን አስቀድሞ ለቤተሰብ ማሳወቅ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ከዚህ ባሻገር ለእስር በተዳረጉበት ወቅት ያለመናገር መብት አላቸው፡፡ያጠፉት ጥፋት ቢገባቸው ቋንቋ ይገለፅላቸዋል፤ቃላቸውን ሰጥተው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፡፡በፍርድ ቤት የዋስትና መብት መጠየቅ፤የህጉን አካሄድ የማያውቁ ከሆነም መንግስት ጠበቃ ሊያቆምላቸው ይችላል፡፡

No comments:

Post a Comment