Monday, August 19, 2013

‹‹ካፍ በሰጠኝ ኃላፊነት ፌዴሬሽኑም ሆነ ሥራ አስፈጻሚው የሚመለከታቸው አይመስለኝም›› አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሲኤምሲ አካባቢ ለሚገኘው የካፍ የወጣቶች አካዴሚ ማስፋፊያና ማጠናቀቂያ ይውል ዘንድ 3.6 ሚሊዮን ብር፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መስጠቱ ይፋ ተደርጓል፡፡

ሆኖም ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ ትዕዛዝ ያሬድ ኮንትራክተር ለተባለ ድርጅት ምንም ዓይነት ጨረታ ሳይወጣ በቀጥታ 1.3 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል መባሉ እያነጋገረ ይገኛል፡፡

የፌዴራሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የድርጊቱን አሳሳቢነት በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽንና ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግረው ማብራሪያ እንዲሰጡበት መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡



በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ ይሁንታ ተከፈለ ስለተባለው 1.3 ሚሊዮን ብር ጉዳዩ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጠየቀ ስለተባለው ማብራሪያ ተነጋግረው ማብራሪያውን መስጠት ይችሉ ዘንድ ‹‹ስብሰባ እንቀመጥ፣ አንቀመጥም በመባባልና ጉዳዩ እናንተንና ፌዴሬሽኑን አይመለከትም›› የሚለው የአቶ ሳሕሉ ንግግር አለመግባባቱን አባብሶታል የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተነጋግሮ አብሮ ማብራርያ እንዲሰጥ የተጠየቀው ስፖርት ኮሚሽን ጉዳዩ ‹‹እኔን አይመለከትም›› ማለቱም ተሰምቷል፡፡

‹‹ቀልድ›› ሲሉ የኮሚሽን አባባል የሚያጣጥሉት የፌዴሬሽኑ ምንጮች በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ በካፍ ሙሉ ወጪ ሲኤምሲ አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘው የካፍ የወጣቶች አካዴሚ መጀመርያ ግንባታውን አጠናቆ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲያስረክብ ኃላፊነት የወሰደው የግብፅ ተቋራጭ ነበር፡፡ ተቋራጩ ግንባታውን አጠናቆ ማስረከብ የሚጠበቅበት የጊዜ መጓተት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተጀመረውም ቢሆን ከደረጃ በታች ሆኖ በመገኘቱ ካፍ ውሉን እንዲያቋርጥ ተደገዷል፡፡

ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይውል ዘንድ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳሕሉ ገብረወልድና የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብዲሳ ያደታ ባለፈው ዓመት የካፍ ጽሕፈት ቤት ወደሚገኝበት ግብጽ ካይሮ ተጉዘው ከካፍ ፕሬዚዳንት ሚስተር ኢሳ ሐያቱና ከዋና ፀሐፊው ሂሻም ጋር ተነጋግረዋል፡፡

በወቅቱ የተደረገውን ውይይት መነሻ በማድረግና ፕሮጀክቱ የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያጠና የካፍ ልዑክ ከወራት በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ተደርጎ፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ፣ አቶ ተካ አስፋውና የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ፀሐፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ፣ እንዲሁም ከስፖርት ኮሚሽን አቶ አብዲሳ ያደታና የኮሚሽኑ መሃንዲስ አቶ ጥበቡ ጎርፉ ፕሮጀክቱ በሚገኝበት ሲኤምሲ ድረስ በመሔድ አጠቃላይ ያለውን ሁኔታ ከካፍ ሰዎች ጋር ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ቀጥሎም የካፍ ተወካዮች ለኮሚሽኑና ለፌዴሬሽኑ አመራሮች የተቋረጠው ግንባታ እንዲጀመርና ሥራውን የሚያከናውነውንም ተቋራጭ አገሪቱ በምትመራበት የጨረታ ሕግ መሠረት፣ የጨረታ ሰነድ ወጥቶ ሥራው እንዲጀመር መመሪያ ሰጥቶ መመለሱም የሚታወስ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በተሰጠው መመሪያ መሠረት የጨረታውን ሰነድ የሚያዘጋጅ ሙያተኛ አዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የጨረታ ማስታወቂያ ሳይወጣ ቆየ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ ውጪ ለቀሪዎቹ አመራሮች ጉዳዩ ምስጢር ሆኖ ከቆየ በኋላ ሰሞኑን ይፋ መሆኑ ታወቀ፡፡

ያለጨረታ አካዴሚውን ለሚገነባው ያሬድ ኮንትራክተር ለተባለ ድርጅት ወደ ፌዴሬሽኑ ካዝና ከገባው 3.6 ሚሊዮን ብር ውስጥ 1.3 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ ሲከፈል ያልታወቀበትን ምክንያት በተመለከተ ምንጮቹ፣ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ይኼው ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓይነት የሚሉት እነዚሁ አካላት፣ በዚህ መንግሥታዊ በሆነ ተቋም ስም ሌላ ተመሳሳይ ነገር ላለመሥራቱ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

ስለጉዳዩ በስልክ ያነጋገርናቸው አቶ ሳሕሉ፣ ‹‹ባለፈው ረቡዕ በወጣው ሊግ ጋዜጣ ከሰጠሁት ውጭ የምለው የለኝም›› ብለዋል፡፡ ይሁንና በጋዜጣው ከሰፈረው አስተያየት፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም ጉዳይ ዙሪያ ለየትኛውም ሚዲያ ምንም መናገር አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም የምሠራውን በደንብ ጠንቅቄ የማውቅ ነኝና›› ብለው፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማብራሪያ ጠየቀ ስለተባለው ጉዳይና ስለክፍያው፣ ‹‹ፌዴሬሽኑም ሆነ ሥራ አስፈጻሚው አያውቀውም፣ አይመለከተውምም፡፡ ምክንያቱም እኔ የካፍ ዴሊጌት ነኝ፡፡ ስለሆነም ካፍ የሚያሠራውን አካዴሚ ግንባታ በተመለከተ እኔ በውክልና ለምሠራው ሥራ ፌዴሬሽኑና ሥራ አስፈጻሚው የሚመለከታቸው ያለ አይመስለኝም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

ይህንኑ የአቶ ሳሕሉን አስተያየት አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምንጮች፣ ‹‹አባባሉ እጅግ አስገራሚና አነጋጋሪም ነው፡፡ ምክንያቱም ካፍ አቶ ሳሕሉን የሚያውቃቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነታቸው እንጂ አቶ ሳሕሉ በመሆናቸው አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ የተቀሩት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካዝና ገቢ ስለተደረገ ገንዘብና በፌዴሬሽኑ ስም ስለሚኖረው ግንኙነት የማይመለከታቸው ከሆነ በጠቅላላ ጉባኤ መመረጥ ባላስፈለጋቸው ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ነቢዩ በበኩላቸው፣ ያሬድ ኮንትራክተር ለተባለው ድርጅት ክፍያ እንዲፈጸም ያደረጉት አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ ግልባጭ ለስፖርት ኮሚሽን በማድረግ በደብዳቤ አዘዋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክፍያውን የፈጸሙትም በፋይናንስ ሥርዓት የአከፋፈል ሒደቱን ተከትለው ስለመሆኑ ጭምር አስረድተዋል፡፡

ሌላው አቶ ሳሕሉ በማብራሪያቸው ያካተቱት የአካዴሚውን ማስፋፊያ ግንባታ እንዲያከናውን የተመረጠው ያሬድ ኮንትራክተር የተባለው ድርጅት፣ ስምምነቱን የፈጸሙ ወደ ካይሮ አምርቶ በቀጥታ ከካፍ ጋር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ፌዴራሉ ስፖርት ኮሚሽን ስለጉዳዩ የሚያውቀው ካለ በሚል በስልክ ያነጋገርናቸው የኮሚሽኑ መሐንዲስ አቶ ጥበቡ ጐርፉ በበኩላቸው፣ ስልካቸውን ካነሱ በኋላ እንደማይሰማቸው ገልጸው አቋረጡት፡፡ ይሁን እንጂ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ኮሚሽኑ በጉዳዩ እንደማይመለከተው በአቶ ጥበቡ በኩል ለፌዴሬሽኑ መልስ መስጠቱን ነው፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያለጨረታ ክፍያ ፈጽሞበታል ስለተባለው የካፍ አካዴሚ ግንባታ ጉዳይ፣ ፌዴሬሽኑ ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በጋራ ተነጋግረው ማብራሪያ እንዲሰጡበት መጠየቁ ባለፈው ሳምንት ዘግበናል፡፡ ለጉዳዩ እንግዳ መሆናቸውን የገለጹ የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለጠየቀው ማብራሪያ መልስ ለመስጠት ይችሉ ዘንድ፣ ነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ተሰብስበው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ሊገኙ ባለመቻላቸው መበተናቸውም ተገልጿል፡፡

ይሁንና ከአንዳንድ የፌዴሬሽን አመራሮች ለመረዳት እንደቻልነው፣ እስካለፈው ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ፕሬዚዳንቱ ሥራ አስፈጻሚውን ጠርተውና በጉዳዩ ተወያይተው ፀረ ሙስና ኮሚሽን ላቀረበው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆኑ፣ የቀሩት አመራሮች ተሰብስበው ማብራሪያ የሚሰጡበት ሁኔታ እንደሚኖር ነው ያስረዱት፡፡

ምክንያቱም የሚሉት እነዚሁ አመራሮች፣ አካዴሜውን በተመለከተ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ ተጨማሪ ማስፋፊያዎችን ለማከናወን ከመንግሥት ተጨማሪ መሬት ተጠይቆ ተፈቅዷል፡፡ ይህ በሆነ ማግስት መንግሥታዊ ተቋም ከሆነው ለተጠየቀ ማብራሪያ መልስ አለመስጠት እንዴትስ ይቻላል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment