Wednesday, August 14, 2013

ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሁለት አውሮፕላኖች፤ሁለት መርከቦች እና ሁለት ሆቴሎች ባለቤት


በብርጋዴል ጄነራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሁለት አነስተኛ የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ከጣሊያን ኩባንያ መግዛቱን ምንጮች ገለጹ፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት የጀመራቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢንጂነሪንግ ሥራዎችን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት ላይ የሚገኙ አሥር የስኳር ፋብሪካዎችንና ሌሎችን የመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው ኮርፖሬሽኑ፣ ግብርና መር የሆነውን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ለተያዘው ዕቅድ ዋነኛ ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ፣ ለዚህ ተልዕኮው መሳካት አውሮፕላኖቹ እንዲገዙ ማስፈለጉን የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

 የአውሮፕላኖቹ ግዥ በሒደት ላይ እንደሆነና በግዥው መሠረታዊ ምክንያቶች ላይ ማብራሪያ ቢሰጥም፣ የአውሮፕላኖቹ ግዥ ስለመጠናቀቁ ግን ሙሉ መረጃ አልሰጠም፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ግን ግዥው ተጠናቆ የአውሮፕላኖቹ ርክክብ ተፈጽሟል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ግዥውን ለመፈጸም ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣ ባይታወቅም፣ አውሮፕላኖቹን ያቀረበው ኤርማክስ የተባለ ኩባንያ እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 
ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት የተጣሉበትን በርካታ ኃላፊነቶች ለመወጣትና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሻገር በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ከአዲስ አበባ በከፍተኛ ርቀት ላይ በሚገኙ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማከናወን ላይ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ገልጾ፣ ፕሮጀክቶቹን በመከታተል ረገድ የሚስተዋሉ የትራንስፖርት ችግሮችን ለመቅረፍ የአውሮፕላኖቹን ግዥ መፈጸም አስፈላጊ ሆኗል ብሏል፡፡ አውሮፕላኖቹ ግፋ ቢል አምስት ሰዎችን የማጓጓዝ አቅም ነው ያላቸው፡፡ በተለይም ያለ አንዳች ዕረፍት በመገንባት ላይ የሚገኘውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተያዘው ፍጥነትና ጥራት ለማስቀጠል ፕሮጀክቱን የሚከታተሉ ቡድኖችና የኮርፖሬሽኑ አመራሮችን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ወደ ሥፍራው ለማጓጓዝ ጥቅም እንደሚውሉ የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ገልጿል፡፡ ከህዳሴው ግድብ በተጨማሪም የባለሙያዎችንና የኮርፖሬሽኑን አመራሮች ክትትል የሚጠይቁ በተለያዩ ሩቅ አካባቢዎች ለሚገኙ ፕሮጀክቶች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ይውላሉ ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የበረራ አገልግሎት ቢሰጥም በረራው በፕሮግራም የሚመራ በመሆኑ ከኮርፖሬሽኑ የትራንስፖርት ፍላጐት ጋር አለመጣጣሙን፣ ከሌሎች የግል የአየር ትራንስፖርት ሰጪ ተቋማት አውሮፕላን ተከራይቶ (ቻርተር) ለመንቀሳቀስ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ግዥውን መፈጸም ተመራጭ ሆኗል በማለት ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡
 ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ ሁለት መርከቦችን ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መግዛቱ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይም ሁለት ሆቴሎችን ማለትም የቀድሞውን ኢምፔሪያል ሆቴልንና ሪቬራ ሆቴልን መግዛቱ አይዘነጋም፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከውጭ የሚያስገባቸውን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ዕቃዎች በራሱ ለማጓጓዝ ሁለቱን መርከቦች እንደገዛ፣ ሆቴሎቹ ደግሞ የተገዙት ለአጭር ጊዜ ለሚቀጥራቸው የውጭ ባለሙያዎች የሚያወጣውን ከፍተኛ የሆቴል ወጪ ለመቀነስ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በሰኔ ወር 2002 ዓ.ም. በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመ ሲሆን፣ በመከላከያ ሥር የሚገኙ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽኖችንና ሌሎች ከ15 በላይ የመንግሥት ድርጅቶችን በማቀፍ በአሥር ቢሊዮን ብር ካፒታል ሥራውን በ2003 ዓ.ም. ጀምሯል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በተቋቋመበት ዓመት ያገኘው ጠቅላላ ገቢ 538 ሚሊዮን 804 ሺሕ ብር ሲሆን፣ በ2004 ዓ.ም. በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ አጠቃላይ ገቢውን 16.8 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ በተጠቀሱት ዓመታት ካገኘው ገቢ በመጀመሪያው ዓመት የ316.1 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ሲደርስበት፣ በ2004 ዓ.ም. ግን ይህንን በማሻሻልና ወደ ትርፍ በመሸጋገር 181.142 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ትርፉን ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው ከኮርፖሬሽኑ የ2005 የስድስት ወራት ሪፖርት ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/