Wednesday, January 2, 2013

የሚያስጠኗትን ተማሪ በመድፈር የተጠረጠሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን ታሰሩ

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

-    ተማሪዋ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባት መሆኑን ትናገራለች

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ ሁለተኛ ዓመት ተማሪን እንዲያስጠኗት በዲፓርትመንቱ የተመደቡት የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን፣ ተማሪዋ ባቀረበችባቸው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን አቶ ናትናኤል ተሻለ፣ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት ‹‹ተደፍሬያለሁ›› ያለችውን ተማሪ እንዲያስጠኗት ዲፓርትመንቱ በመደባቸው በማግስቱ መሆኑም ታውቋል፡፡

አቶ ናትናኤል በተጠረጡበት ወንጀል ታኅሳስ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ፣ ከትናንትና በስቲያ በጎንደር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ወንጀሉን የማየት ሥልጣን እንደሌለው በመግለጹ፣ ተመልሰው ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጉን የፖሊስ ጣቢያው ኃላፊ ኢንስፔክተር ዋለልኝ ይምራው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡



በተማሪዋ ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ እንደገለጹት፣ ለዩኒቨርሲቲው የደረሰው መረጃ የለም፡፡ ችግሩ መከሰቱ የታወቀው አቶ ናትናኤል ሲታሰሩ መሆኑን፣ ተማሪዎች በተመደቡበት የትምህርት ዘርፍ ደከም ሲሉ ወይም የወደቁበትን ትምህርት እንዲያሻሽሉ መምህራን እንዲረዷቸው እንደሚደረግና በዚህ መሠረት ዲፓርትመንቱ ሳይመድባቸው እንዳልቀረ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዋ ስለደረሰባት የአስገድዶ መደፈር ጉዳይ ለዩኒቨርሲቲው ምንም የገለጸችው  እንደሌለ ያስረዱት ፕሮፌሰሩ፣ ድርጊቱ ተፈጽሟል መባሉን ያወቁት ፖሊስ መረጃ ሊጠይቃቸው ሲመጣ ታኅሳስ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገችው ‹‹ተደፍሬያለሁ›› ያለችው ተማሪን አነጋግረናት፣ ዲፓርትመንቱ በመደበላት መሠረት ለማጥናት ስትሄድ፣ ድርጊቱ በኃይል እንደተፈጸመባትና ወዲያውኑ ወደ ጎንደር ሆስፒታል በመሄድ መደፈሯን የሚያሳይ ማረጋገጫ የምርመራ ውጤት መያዟን ተናግራለች፡፡

ለምን ለዩኒቨርሲቲው ቀድማ እንዳላሳወቀች ተጠይቃ፣ ቀድማ ብታሳውቅ ተጠርጣሪው ባለሥልጣን ስለሆኑ መረጃውን ሊያጠፉባት እንደሚችሉ በመገመት፣ መጀመሪያ ወደ ሴቶች ጉዳይ ማምራቷን ገልጻለች፡፡ የሴቶች ጉዳይ መጀመሪያ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ እንዳለባት ስለመከራት ለፖሊስ ማመልከቷን አስረድታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜም በተለያዩ ስልኮች እየተደወለ  ማስፈራሪያ እየደረሳት መሆኑንም አስረድታለች፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment