Wednesday, January 2, 2013

የፈረንሳዩ ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን ማኔጅመንት ዛሬ ለመንግሥት ያስረክባል


-    ኢትዮ ቴሌኮምን ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚመሩ የውጭ ዜጎች ተቀጥረዋል

በማኔጅመንት ኮንትራት ኢትዮ ቴሌኮምን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያስተዳድር የነበረው የፈረንሳዩ ኩባንያ ፍራንስ ቴሌኮም የኮንትራት ጊዜው በመጠናቀቁ ምክንያት ማኔጅመንቱን በዛሬው ዕለት ያስረክባል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምን የማስተዳደር ኃላፊነት በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንዲመራ መንግሥት ወስኗል፡፡

መንግሥት የቀድሞውን የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን እንደ አዲስ በማዋቀር
ኢትዮ ቴሌኮም የሚል ስያሜ በመስጠት፣ ማኔጅመንቱን ለሁለት ዓመታት እንዲመራ ፍራንስ ቴሌኮም መምረጡ ይታወሳል፡፡

ከቴሌኮም ንግድ የሚገኘውን ገቢ መጨመርና ለዚህ ጠቃሚ የሆኑ አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን የማስተዳደር ክህሎት በሥልጠና ማጎልበት የውጭ ኩባንያ ካስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡



ፍራንስ ቴሌኮም በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተጠቀሱትን በመንግሥት የታለሙ ግቦች ለመምታት የሚያስችል ብቃት ያለው መሆኑ በመረጋገጡ እንደተመረጠ በወቅቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ 30 ሚሊዮን ዩሮ ለኩባንያው መክፈል ደግሞ ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነበር፡፡

የሁለት ዓመታት የኮንትራት ጊዜው እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 23 ቀን 2012 ያጠናቀቀው ፍራንስ ቴሌኮም በተጠቀሱት ዓመታት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑ ቢነገርም፣ ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በእጅጉ የተለየ ሚና እንዳልነበረው ሲተች ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል ኢትዮ ቴሌኮምን በውጭ ኩባንያ አማካይነት በማስተዳደር ስለተገኘው ውጤት በይፋ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ በኮንትራት ስምምነቱ ሰነድ መሠረት ፍራንስ ቴሌኮም በሚያስመዘግበው ውጤት የኮንትራት ጊዜው እንደሚራዘም ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው ጥያቄውን ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቢያቀርብም ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አስተዳደሩን እንዲረከቡ በመንግሥት መወሰኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረሚካኤል ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በኢትዮ ቴሌኮም አመራር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አስተዳደሩን እንደሚረከቡ ኢትዮ ቴሌኮም የገለጸ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መግለጫ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም መረጃ መሠረት ኢትዮጵያውያን አስተዳደሩን የሚረከቡ ቢሆንም፣ ጥቂት የውጭ ዜጎች ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በመሆን ኩባንያውን እንዲያስተዳድሩ በጊዜያዊ ኮንትራት መቀጠራቸውን ምንጮች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የፍራንስ ቴሌኮም የኮንትራት ጊዜ ለመጠናቀቅ ሦስት ወራት ሲቀሩ በኩባንያው ዋና ጽሕፈት ቤት በኩል የተሾሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ብሩኖ ዱቱዋ በመንግሥት በጊዜያዊ ኮንትራት ከተቀጠሩት የውጭ ዜጎች መካከል አንዱ መሆናቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሚስተር ዳቱዋ የተቀጠሩት ከድርጅታቸው ፍራንስ ቴሌኮም ለቀው ይሁን አይሁን ለማወቅ አልተቻለም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment