Wednesday, January 16, 2013

በደቡብ ኦሞ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ ተጀመረ



በደቡብ ኦሞ ጨው ባህር አካባቢ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ታሎው ኦይል የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ የመጀመሪያው የሆነውን የፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ ከትናንት በስቲያ ጀመረ፡፡

ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ቁፋሮው የተጀመረው በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ ከኦሞራቴ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የነዳጅ ፍለጋ ቁፋሮ የተጀመረው 18 ወራት የዘለቀ የሴይስሚክ (በመሬት የድምፅ ሞገድ በሚከናወን) ጥናትና 18,000 ኪሎ ሜትር በሸፈነ የአውሮፕላን የግራቪቲ ጥናት ከተከናወነ በኋላ እንደሆነ ኩባንያው ገልጿል፡፡ የአየር ጥናቱ በዓለም ላይ ከተከናወኑት ሰፊ ጥናቶች ውስጥ ይመደባል ተብሏል፡፡ ጥናቶቹ በደቡብ ኦሞ ዞን የመጀመሪያው የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ የት አካባቢ መቆፈር እንዳለበት ያመላከቱ እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

የመጀመሪያው የፍለጋ ጉድጓድ (Wild Cat Well) ሳቢሳ አንድ በመባል የተሰየመ ሲሆን፣ ሳቢሳ ማለት በደቡብ ኦሞ ዞን ጨው ባህር አካባቢ የምትገኝ የወፍ ዝርያ ናት፡፡ የመጀመሪያው የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ በወፏ ስም ተሰይሟል፡፡



የታሎው ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ አበበ ኩባንያው ካካሄዳቸው የጂኦሎጂ ጥናቶች የተገኙ መረጃዎችን ከተተነተኑ በኋላ፣ ቦታ ተመርጦ ቁፋሮ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ቁፋሮውን እያከናወነ ያለው ኦጄክ የተሰኘ የፖላንድ ኩባንያ መሆኑን አቶ ጴጥሮስ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሁን የተጀመረው የነዳጅ ማፈላለግ ቁፋሮ በደቡብ ኦሞ ዞን ነዳጅ ስለመኖሩ የሚፈትሽ ሲሆን ውጤቱንም በወራት ውስጥ ማወቅ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ሁለት ተጨማሪ የነዳጅ ጉድጓዶችን በዞኑ ለመቆፈር እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡

ታሎው ኦይል የነዳጅ ፍለጋ ሥራውን ሲያከናውን ከማዕድን ሚኒስቴርና ከሌሎች የመንግሥት አካላት እንዲሁም አጋሮች ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል፡፡ ታሎው ኦይል መቀመጫው ለንደን የሆነ የግል የነዳጅ ፍለጋና ምርት የሚያከናውን ድርጅት ሲሆን በለንደን፣ በአየርላንድና በጋና ስቶክ ኤክስቼንጅ የተመዘገበ ኩባንያ ነው፡፡

ታሎው በጋና ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ዘይት አግኝቷል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በኡጋንዳ አልበርት ቤዚን ተመሳሳይ መጠን ያለው የነዳጅ ከምችት አግኝቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ታሎው በኬንያ ቱርካና ቤዚን የነዳጅ ክምችት ማግኘቱም ይታወሳል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ቀደም ሲል በነዳጅ ግኝት የማይታወቅ የነበረ ቢሆንም፣ በድፍረት ገብቶ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰው ታሎው በኡጋንዳና በኬንያ ውጤታማ ለመሆን በቅቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አዙረዋል፡፡ በታንዛኒያና በሞዛምቢክም ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መገኘት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ለነዳጅ ፍለጋ ሥራ ምቹ መሆናቸው ታምኖበታል፡፡

በኦሞራቴ አካባቢ የሚቆፈረው ሳቢሳ አንድ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ 2,500 ሜትር ጥልቀት ሲኖረው፣ ጉድጓዱን ቆፍሮ ለማጠናቀቅ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት እንደሚፈጅ የታሎው ኦይል ኮርፖሬት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ሲሳይ ዘሪሁን በተለይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከተሰበሰበው የሴይስሚክ መረጃ በመመርኮዝ ታሎው ከመጀመሪያው ጉድጓድ ምን ዓይነት ውጤት ይጠብቃል ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ከወዲሁ ምንም ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

‹‹የነዳጅ ፍለጋ ሥራ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ጉድጓድ ተቆፍሮ ነዳጅ የመገኘት ዕድሉ ወደ 17 በመቶ ነው፡፡ የሳቢሳ አንድ ውጤትም ቁፋሮው ተጠናቆ ካልታየ በስተቀር ከወዲሁ መተንበይ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኡጋንዳና በጐረቤት ኬንያ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ መጀመሪያ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ የጀመረው ዋይት ኦይል የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ ነበር፡፡ የተወሰነ የጂኦፊዚካል ጥናቶች አካሂዶ የሴይስሚክ ጥናት ሳያካሂድና የፍለጋ ጉድጓድም ሳይቆፍር 80 በመቶ ድርሻውን አፍሪካ ኦይል ለተባለ የካናዳ ኩባንያ ሸጦ ወጥቷል፡፡ አፍሪካ ኦይል በበኩሉ ከዋይት ናይል ከገዛው 80 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ 50 በመቶውን ለታሎው ኦይል ሸጧል፡፡ ዋይት ናይል በቅርቡ የቀረውን የ30 በመቶ ድርሻ ማራቶን ኦይል ለተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ሸጦ ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ወጥቷል፡፡

የደቡብ ኦሞ ቤዚን ኢትዮጵያ ካሏት አምስት ሴዲመንታሪ ቢዚኖች (ኦጋዴን፣ ጋምቤላ፣ መቀሌ፣ ዓባይ ሸለቆና ደቡብ ኦሞ) አንዱ ሲሆን፣ በክልሉ የሴይስሚክ ጥናትና የፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ ነው፡፡ የሴይስሚክ መረጃውን የሰበሰበው ቢጂፒ ጂኦ ሰርቪስስ የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ ታሎው ኦይል የነዳጅ ፍለጋ ሥራውን የሚያካሂደው ከአፍሪካ ኦይል ጋር በመተባበር ነው፡፡

የሳቢሳ አንድ ቁፋሮ እንደተጠናቀቀ በጉድጓድ ውስጥ ሙከራ (Well Testing) ይካሄዳል፡፡ ሙከራው የሚደረገው በጉድጓድ ውስጥ ያለውን አየር በመምጠጥ በማውጣት የግፊት ልዩነት በመፍጠር ነው፡፡ በጉድጓዱ ውስጥ ያለው ግፊት አነስተኛ በመሆኑ፣ በአካባቢው የነዳጅ ክምችት ካለ ወደ ጉድጓዱ ይፈሳል፡፡ በዚህም የነዳጅ ክምችት መኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በአካባቢው ነዳጅ ከሌለ ሙከራው በሚከናወንበት ወቅት ወደ ጉድጓዱ የሚፈስ ነዳጅ አይኖርም፡፡ የሳቢሳ አንድ ጉድጓድ ሙከራ ውጤትም ከሦስት ወራት በኋላ የሚታወቅ ይሆናል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment