Sunday, May 20, 2012

“ጥቁር ሰው” አልበም ሊመረቅ ነው::ቴዎድሮስ ካሳሁንና አዲካ ተስማሙ


በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና በአዲካ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንትስ ኩባንያ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት መፈታቱን ምንጮች ገለጹ፡፡ አለመግባባቱ የተፈታው በሽምግልና ሲሆን ቴዎድሮስ ያነሳቸውን የቅሬታ ሐሳቦች በሙሉ በመሰረዝ፣ ከአዲካ ዋና ባለድርሻና ዳይሬክተር አቶ አዋድ መሐመድ ጋር መግባባት ላይ መድረሱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የተፈጠረውን መግባባት ተከትሎ በግንቦት ወር መጨረሻ ወይም በሰኔ ወር መጀመርያ “ጥቁር ሰው” የተሰኘውን የቴዎድሮስ አዲስ አልበም ለማስመረቅ ቀጠሮ ተይዟል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቀሙት በሁለቱ ባለጉዳዮች መካከል በተነሳው አለመግባባት የአልበሙ ሽያጭ ተቀዛቅዟል፡፡ “ምርቃቱ ያስፈለገውም የተቀዛቀዘውን ገበያ ለማነቃቃት ነው” ሲሉ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

ባለፉት ሳምንታት በቴዎድሮስና በአቶ አዋድ ኩባንያ መካከል አለመግባባት መፈጠሩ አይዘገነጋም፡፡ አለመግባባቱ የተነሳው ቴዎድሮስ ባነሳቸው ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡

የመጀመርያው አልበሙ በሜታ ቢራ ስፖንሰር ተደርጎ ሲዲው ላይ የሜታ ቢራ ማስታወቂያ በመለጠፉ ሲሆን፣ እንዲሁም የአልበሙ ሽያጭ ከሁለት ሚሊዮን ኮፒ በላይ በመሆኑ፣ ላገኝ የሚገቡኝን ጥቅሞች አጥቻለሁ የሚል ነው፡፡

ይህ የቴዎድሮስ ካሳሁን የቅሬታ ሐሳብ ለአዲካ ሚዛን የሚደፋ አልሆነም፡፡ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ በቴዎድሮስና በአዲካ መካከል መጋቢት 2004 ዓ.ም. በተደረገው ውል ቴዎድሮስ አዲካ ለአልበሙ ስፖንሰር እንዲጠቀም ይፈቅዳል፡፡ ይህም በመሆኑ አዲካ ሜታ ቢራን ለስፖንሰርነት ካመጣ በኋላ ቴዎድሮስ ቢራ ማስተዋወቅ አልፈልግም በማለቱ፣ ከመጀመርያው ሊታሰብበት ይገባ ነበር በሚል አቶ አዋድ እንዳልተቀበሉት ታውቋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተነሳው የቴዎድሮስ ቅሬታ የተሸጠው የሲዲ ቁጥር ከፍተኛ ነው ነገር ግን በአዲካ የተገለጸው የሽያጭ ቁጥር ዝቅተኛ ነው የሚል ነበር፡፡ በዚህም ሊያገኝ ይገባው የነበረውን ገቢ እንዳጣ ቴዎድሮስ መናገሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአዲካና በቴዎድሮስ መካከል ያለው ስምምነት እንደሚያመለክተው፣ አዲካ ያወጣውን ወጪ መልሶ የተጣራ ትርፍ ማግኘት ሲጀምር ከሚገኘው ትርፍ 20 በመቶ እንደሚያገኝ ነው፡፡ ነገር ግን በአዲካ የቀረበው መረጃ ቴዎድሮስ አለ እንደሚባለው ከሁለት ሚሊዮን በላይ ኮፒ አይደለም፡፡

ከህትመት ኩባንያው የተገኘው መረጃም የሲዲ ሽያጩ ሚሊዮን ቤት አልገባም፡፡ በመረጃ የተደገፈው ይህ ሆኖ ሳለ በቴዎድሮስ በኩል የሚነሳው ግምታዊና ሐሳባዊ ቁጥር ነው በሚል አዲካ አልቀበልም እንዳለ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ይህንን ችግር በግልግል ለመዳኘት ባለፉት ሳምንታት በርካታ ሰዎች ሞክረዋል፡፡ ስምምነቱ ላይ ለመድረስ በርካታ ጊዜያት ቢፈጅም በመጨረሻ ቴዎድሮስ የቅሬታ ሐሳቦቹን ሙሉ በሙሉ በማንሳቱ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቴዎድሮስ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ቴዎድሮስ ከእጮኛው ከወ/ሪት አምለሰት ሙጬ ጋር ሽርሽር ላይ መሆኑን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment