የበኩር
ልጇን ለመገላገል ሰዓታት ቀርተዋት የነበረች የ28 ዓመት ወጣት ምጥ ይዟት ወደ ሆስፒታል እየተወሰደች ማጅራት መቺዎች ባሏን በመደብደብ ላይ እያሉ ገፍትረዋት በመውደቋ ሕይወቷ ማለፉን ባለቤቷ ለሪፖርተር ገለጸ፡፡
በምጥ
ጭንቅ ውስጥ እያለች ተገፍትራ በመውደቋ ሚያዝያ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት አካባቢ ሕይወቷ ስላለፈው ወ/ሮ ምሥራቅ አክመል፣ ባለቤቷ ስለተፈጠረው አጋጣሚና እንዴት ሕይወቷ እንዳለፈ በዝርዝር ተናግሯል፡፡ የሟች ምሥራቅ አክመል ባለቤት አቶ ታሪኩ ጉዲሳ እንደገለጸው፣ ምሥራቅ ሚያዝያ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ ምጥ ይመጣባታል፡፡ የሚኖሩት ላፍቶ ቁጥር ሁለት ኮንዶሚኒየም ቤት በአንዱ ብሎክ ውስጥ ነው፡፡
ቤታቸው
ለአስፋልቱ ቅርብ በመሆኑ ታክሲ ይዞ ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ወጥቶ ይቆማል፡፡ ታክሲ ሊያገኝ ባለመቻሉ ተመልሶ ወደ ቤቱ ይገባና ታክሲ እንዳጣ ሲነግራት፣ ምሥራቅ ‹‹እኔን ይዘህ አስፋልት ላይ ብትቆም አዝነው ይወስዱናል›› ስትለው፤ ተያይዘው ወጥተው ደጅ ይቆማሉ፡፡
ትንሽ
እንደቆሙ አንድ ላዳ ከጐፋ ወደ ላፍቶ ሲመጣ የተመለከቱት ባልና ሚስት እጃቸውን ሲያውለበልቡ ታክሲው ዝም ብሎ ትንሽ ካለፋቸው በኋላ፣ አንድ ሰው አውርዶ ተመልሶ ይመጣና አጠገባቸው ይቆማል፡፡ ምጥ እንደተያዘችበትና ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው ላንድማርክ ሆስፒታል እንዲያደርሳቸው የተጠየቀው የላዳ ሾፌር፣ አንድ መቶ ብር እንዲከፍሉ ሲጠይቃቸው ይስማሙና እሷ ከፊት እሱ ከኋላ ይሳፈራሉ፡፡
ታሪኩ
ከኋላ ሲገባ አንድ ሰው ተቀምጦ ማየቱንና ትንሽ እንደተጓዙ በስካር መንፈስ፣ ‹‹የምከፍለው ይኼንን ያህል ነው›› ሲል ሾፌሩ ደግሞ ‹‹ካወረድኩት ሰው ጋር የተስማማሁት ይኼንን ያህል ነው›› በመባባል ሲነጋገሩ ባልና ሚስት ዝም ብለው ይሰማሉ፡፡
ላዳው
ጐፋ ገብርኤል አደባባይ ሲደርስ አደባባዩን በመዞር ወደ ላፍቶ አቅጣጫ የአደባባዩ ጫፍ ላይ ውረዱ ብሎ ባልና ሚስቶቹን በማውረድ ወደ ላፍቶ ይሄዳል፡፡ ታሪኩና በምጥ ላይ ያለችውን ምሥራቅን ያጋጠማቸው ሌላ ላዳ ሳይሆን ሁለት ግዙፍ ሰውነት ያላቸው ማጅራት መቺዎች ነበሩ፡፡ ‹‹ማነህ ምንድነህ›› ሳይሉ በታሪኩ ላይ የቡጢና የእርግጫ ውርጅብኝ ሲያዘንቡበት፣ በምጥ የተያዘችው ምሥራቅ እየለመነች ልትገላገል ስትሞክር፣ ማጅራት መቺዎቹ ከሩቅ ሰው በማየታቸው ወይም ድምፅ በመስማታቸው ይመስላል እሷን በኃይል ገፍትረዋት ይሮጣሉ፡፡ በጉልበተኞች የተገፈተረችው ምሥራቅ በሆዷ መሬት ላይ ትወድቃለች፡፡ ታሪኩም ለብቻው ወድቆ ነበርና ምሥራቅ በድንጋጤ ውስጥ ሆና በመነሳት ወደ ባሏ ተጠግታ ‹‹ተረፍክ›› ካለች በኋላ ተዝለፍልፋ መውደቋን ባለቤቷ በዝርዝር ተናግሯል፡፡
በምጥ
ጭንቅ ላይ የነበረችው ምሥራቅ ተዝለፍልፋ ስትወድቅ እሷን አቅፎ የድረሱልኝ ጩኸት ቢያሰማም ምንም ዕርዳታ አለማግኘቱን የገለጸው ባለቤቷ፣ አንድ ታክሲ ሲመጣለት ታቅፎ በማስገባት ላንድማርክ ሆስፒታል ቢያደርሳትም፣ ከዶክተሮቹ የተነገረው መርዶ ሕይወቷ ያለፈው በክንዱ ላይ መሆኑን በማንባት ገልጿል፡፡
ታሪኩና
ምሥራቅ የተጋቡት ሐምሌ 24 ቀን 2003 ዓ.ም. መሆኑንና አብረው መኖር ከጀመሩ ገና ዘጠነኛ ወራቸው እንደሆነ ተናግሮ፣ ‹‹እኔና እሷን ጨምሮ የእሷና የእኔ ቤተሰቦች፣ ጓደኞቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ጭምር የልጃችንን መወለድ ስንጠባበቅ ቆይተን፣ በገዛ አገራችን ውስጥ ይኼ ወንጀል ተፈጸመብን፤ ላልሰሙት ወገኖቻችን ምን ብዬ ልንገራቸው?›› በማለት መሪር ሐዘኑን ገልጿል፡፡
ምሥራቅ
የተወለደችውና ከ27 ዓመታት በላይ ዕድሜዋን ያሳለፈችው ሐረር ከተማ ውስጥ መሆኑን የገለጸው ባለቤቷ፣ አስከሬኗ ምኒልክ ሆስፒታል ከተመረመረ በኋላ፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም. ሐረር ከተማ ውስጥ ሥርዓተ ቀብሯ መፈጸሙን ገልጿል፡፡
በአስጐብኝነት
ሥራ ላይ የተሰማራ መሆኑን የገለጸው ታሪኩ፣ የባለቤቱን ማርገዝ ለውጭ ዜጐች ጭምር ሳይቀር መናገሩን ጠቅሶ፣ ‹‹የሃይማኖት አገር፣ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት በምትባለው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለቤቴን ማጅራት መቺዎች ገደሉብኝ ብል ምን ይሉኛል?›› በማለት በምሬት ተናግሯል፡፡
‹‹ክፉ
ናቸው፣ ሰው በላ ናቸው፣ በማለት ከሚታወቁት አንዳንድ አገሮች የበለጠ ክፉዎች ነን፤ ምናልባት እሷን ትተው የፈለጉትን በመውሰድ ቢለቁን? በወቅቱም የለመንናቸው ይኼንን ነበር፤›› ሲልም በምሬት አስረድቷል፡፡
ድርጊቱ
በተፈጸመበት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ መኖሩን የገለጸው ታሪኩ በሲቃ ውስጥ ያለ ድምፅ ቢሆንም፣ የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰማ ማንም እንዳልደረሰለት፣ በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ማንም ምንም ዓይነት ዋስትና እንደሌለው እንደሚሰማው ተናግሯል፡፡ አንድ ሰው ሲሰረቅ ወይም ሲደበደብ የሚያይ ሰው እንዳላየ የሚሆነው፣ ድርጊቱን ፈጻሚዎቹ ከቀናት በኋላ ከእስር ሲለቀቁ የሚያደርሱበትን ድብደባ ስለሚፈራ መሆኑን፣ እነሱ ሲደበደቡ በርቀት ሆኖ ይከታተል የነበረ አንድ ግለሰብ ለፖሊስ ከሰጠው ቃል ሊገነዘብ መቻሉን ታሪኩ ይናገራል፡፡
ግለሰቡ
በርቀት ሁኔታውን በሙሉ ሲከታተል ስለነበር ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ ሁለቱም ግለሰቦች ቢያዙም፣ ሆን ብሎና ተሻርኮ እነሱ ጋ ያደረሳቸው ባለላዳ እንዳልተያዘ ገልጿል፡፡ መንግሥት ለእሱ (ለታሪኩ) ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትና የሚያረጋግጥ ፍትሕ በወንጀለኞቹ ላይ እንዲሰጥም ጠይቋል፡፡
ምጥ
ተይዛ ወደ ሆስፒታል በመሄድ ላይ ሳለች ሕይወቷ ስላለፈው ወ/ሮ ምሥራቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የነፍስ ግድያና ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ‹‹ድርጊቱ አሳዛኝ ነው›› ብሎ፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ተይዘው በምርመራ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
http://ethiopianreporter.com
http://ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment