Thursday, May 3, 2012

ሚስቱን በአሲድ አቃጥሎ የገደለውና ደቡብ ሱዳን የተያዘው የሞት ቅጣት ተወሰነበት


- ግብረ አበሮቹ 16 እስከ 23 ዓመታት ጽኑ እስራት ተቀጡ

አምና ሚያዝያ 30 ቀን 2003 . በልጁ እናት ላይ አንድ ሊትር ሰልፈሪክ አሲድ በመድፋት ለሞት የዳረጋት ግለሰብ፣ ከትናንት በስቲያ በሞት እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔ ሰጠ፡፡ በሞት እንዲቀጣ ውሳኔ የተላለፈበት የሟች የወ/ ትዕግስት መኮንን ባለቤት የነበረው አቶ ምናለ አቻም፣ በልጁ እናት ላይ አንድ ሊትር ሰልፈሪክ አሲድ በማርከፍከፍ ከተሰወረ ከወራት በኋላ፣ ባለፈው ዓመት ነፃነቷን ባገኘችው ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ውስጥ ተይዞ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ይታወሳል፡፡

ግለሰቡ የፈጸመው የወንጀል ድርጊት በፍርድ ቤት ሲታይ ከቆየ በኋላ፣ ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተበትን ክስ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ሲያረጋግጥ፣ ግለሰቡ የቀረበበትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ባቀረባቸው የመከላከያ ምስክሮችና ሰነዶች ማስተባበል ባለመቻሉ፣ ሚያዝያ 26 ቀን 2004 . ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ ከትናንትና በስቲያ በሞት እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡

/ ትዕግስትን ለመግደል ባለቤቷ ያዘጋጀውን አንድ ሊትር ሰልፈሪክ አሲድ ደብቆ በማቆየትና በመተባበር ጥፋተኛ የተባለው ዘለዓለም ውበት ወይም በቅፅል ስሙ ‹‹ጉቼ ውበት›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው 16 ዓመታት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

ዘለዓለም የደበቀውን ሰልፈሪክ አሲድ ተቀብሎና ክዳኑን ከፍቶ ለባለቤቷ የሰጠውና በተባባሪነት በሠራው ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ነበረ ጎሹ ወይም በቅፅል ስሙ ‹‹ቀበሮው›› በመባል የሚታወቀው 23 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

ተባባሪዎቹ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ለአምስት ዓመታት ከማንኛውም የሕዝባዊ መብቶቻቸው ታግደዋል፡፡ ሦስቱም ግለሰቦች ማለትም ባለቤቷ ምናለ አቻምና ሁለቱ ተባባሪዎቹ ሚያዝያ 30 ቀን 2003 . የሦስት ሕፃናት እናት የነበረችውን ትዕግስት መኮንን፣ ወደ ቤቷ ልትገባ ትንሽ ሲቀራት በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 19 ሂልሳይድ ትምህርት ቤት አጠገብ፣ ባልየው በዱላ ደብድቦ ከጣላት በኋላ ተባብረው ሰልፈሪክ አሲድ በመላ ሰውነቷ ላይ አርከፍክፈውባት መሰወራቸውን፣ ሆስፒታል ተወስዳ ለሦስት ቀናት ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ግንቦታ 2 ቀን 2003 . ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም ሕይወቷ ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment