በኢትዮጵያ
ባብዛኛው የተለመደው የተቸገረች ኢትዮጵያዊት እናት ልጇን ጥላ ስትሰወር፣ ብዙውን ጊዜ ፈረንጅ አሳዳጊዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ወላጅ አልባ ሕፃናትን በማደጐ ልጅነት አስመዝግበው ወደ አገራቸው ሲሄዱ ነው፡፡ በቅርብ ቀን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጠረው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ የ12 ዓመቱን ታደሰ ገብረ እግዚአብሔርን አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ማርቪን ሄጊ የሚባል ግለሰብ ከሁለት ዓመት በፊት በማደጐ ልጅነት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ አስመዝግቦ ወደ አሜሪካ እንደወሰደው ታዳጊው ይናገራል፡፡ ታደሰ ወላጅ አባቱ በልጅነቱ እንደሞቱ፣ እናቱ ደግሞ ወደ አሜሪካ ከአሳዳጊው ጋር ከመጓዙ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደሞቱበት ይገልጻል፡፡
በመቀሌ
ከተማ ቀበሌ 09 ተወልዶ እንዳደገ የሚናገረው ታደሰ፣ አሳዳጊው ሚስተር ማርቪን ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ይዞት እንደመጣና የኤምባሲውን ጉዳይ ፈጽሞ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ይዞት እንደሄደ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ ከአንድ ዓመት በላይ ሲኖር አሳዳጊው ትምህርት ቤት እንዳላስገባውና ከቤት እንደማያስወጣው ታደሰ ገልጾ፣ የእንግሊዝኛ መምህር ቀጥሮለት ቤት ድረስ እየመጣ ያስተምረው እንደነበር አብራርቷል፡፡
“ልብስ
ግዛልኝ ስለው ብዙም አይገዛልኝም ነበር፤ ምግብ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ያበላኝ ነበር፤” ያለው ታደሰ፣ አሳዳጊው የፈጸመበት ግፍ እንደሌለና ሁለት ዓመት አብሮት ሲኖር የመታው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ አሳዳጊው የሚሠራውን ሥራ በትክክል ባያውቅም ብዙ ድርጅቶች ያሉት ሀብታምና የሚኖረው ፒሊፓ ከምትባል እናቱ ጋር ነው ብሏል፡፡
ከሰባት
ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት እንሄዳለን ብሎ ይዞት እንደመጣና በሆለታ ቤት ተከራይተው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደኖሩ ታደሰ ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ቆይታው አሳዳጊው ሚስተር ማርቪን፣ መስከረም ከምትባል ኢትዮጵያዊ ጋር ተዋውቆ ፍቅር መጀመራቸውን የሚናገረው ታደሰ ኢትዮጵያዊቷ እርሱን በፍፁም እንዳልወደደችው ይናገራል፡፡
“ለምን
እኛ የራሳችንን ልጅ ወልደን አናሳድግም ትለው ነበር፤” ያለው ታደሰ፣ ባለፈው ሳምንት አሳዳጊው ከሆለታ ወደ አዲስ አበባ ይዞት እንደመጣና ኡራኤል አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆቴል ማረፋቸውንና መስከረምም አብራቸው እንደነበረች አብራርቷል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ቀኑን በትክክል በማያስታውስበት ቀን ማርቪንና መስከረም ከአረፉበት ሆቴል ጥለውት እንደተሰወሩ ተናግሯል፡፡
ልብሶቹና
የአሜሪካ ፓስፖርቱ አሳዳጊው ዘንድ እንደሆነ የሚናገረው ታደሰ፣ የሆቴሉ ሠራተኞች በሰጡት ምክር ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መሄዱን ተናግሯል፡፡ በመንገደኞች ተርሚናል የኤርፖርት ሴኩዩሪቲ ሠራተኞች አግኝተው እያነጋገሩት ሳለ በኤርፖርት ውስጥ የሚያውቃት አንዲት ኢትዮጵያዊ ሴት ይመለከታል፡፡ ለእነሱም ይህንኑ ይገልጻል፡፡
ልጁን
የተመለከተችው ወጣት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ ስትሆን ታዳጊውን የምታውቀው ቦሌ ሮክ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ “ከሁለት ወራት በፊት ቦሌ ሮክ ስዋኝ ታዳጊው ከአንድ ፈረንጅ ጋር እየመጣ ሲዋኝ በተለያዩ ቀናት አግኝቼዋለሁ፤” የምትለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቲኬት ኤጀንት ባለሙያ፣ ባለፈው ዓርብ ማታ ታዳጊውን ከሴኪዩሪቲ ሠራተኞች ጋር በመንገደኞች ተርሚናል ውስጥ እንዳገኘችው ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡ ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችው የአየር መንገዱ ባልደረባ ልጁን ካገኘችበት ቀን ጀምሮ ለምግቡ የሚሆን ገንዘብ እንደምትሰጠው ገልጻ፣ ታዳጊው እስካሁን የሚኖረው በመንገደኞች ተርሚናል ከሴኪዩሪቲ ሠራተኞችና ከፖሊሶች ጋር ነው፡፡ አሳዳጊው ከአገር ይውጣ ወይም እዚህ እንዳለ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
በስፍራው
ተገኝተን ያነጋገርናቸው የኤርፖርት ሴኪዩሪቲ ሠራተኞች የልጁ ሁኔታ ስላሳዘናቸው እንዳስጠጉትና ተራ በተራ ምግብ እንደሚገዙለት ገልጸውልናል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛዋ በበኩሏ እስካሁን ልጁን ብቻዋን እየረዳችው እንደሆነ ገልጻ፣ ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች ብትሄድም ልጁ ጠፋብኝ ብሎ ያመለከተ እንደሌለ፣ አሜሪካ ኤምባሲ የሚሠሩ ሰዎችንም አነጋግራ ልጅ ጠፍቶብኛል ብሎ ያመለከተ ሰው አለመኖሩንና ኤምባሲው የታዳጊውን ጉዳይ ሊመለከት የሚችለው በፖሊስ በኩል ሲመጣ እንደሆነ ስለነገራት፣ ትናንት ማለዳ ባምቢስ አቅራቢያ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ይዛው ሄዳለች፡፡ ኃላፊዎቹ በስብሰባ ላይ ስለነበሩ ሊያስተናግዷት ባለመቻላቸው ትናንት ከሰዓት በኋላ ታዳጊውን ወደ ኤርፖርት መልሳ እንደወሰደችው ገልጻለች፡፡
ይህን
ጉዳይ አስመልክቶ ለአሜሪካ ኤምባሲ ላቀረብነው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ፣ “ልጁ አሜሪካዊ መሆኑን ሳናረጋግጥ አስተያየት መስጠት አንችልም፡፡ ነገር ግን አጣርተን ልጁ በትክክል የአሜሪካ ዜግነት እንዳለው ካረጋገጥን የልጁን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርብናል፤” የሚል ነው፡፡ ኤምባሲው ጉዳዩን ለማረጋገጥ የልጁንና ያሳዳጊውን ስም ወስዷል፡፡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም፡፡
No comments:
Post a Comment