Monday, August 4, 2014

ሳሙኤል ዘሚካኤል ፍ/ቤት ቀርበው የ14 ቀን ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

 በሃሰት “ዶክተር ኢንጂነር” ነኝ ሲሉ የቆዩት ሳሙኤል ዘሚካኤል፤ተሸሽገው ከቆዩበት ኬንያ በአዲስ አበባ ፖሊስና በፌደራል ፖሊስ የኢንተርፖል ዲቪዥን በቁጥጥር ስር ውለው ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከባድ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዝዮን ምክትል ኮማንደር አበራ ቡሊና ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ግለሰቡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ሃገር ቤት እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ በ24 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት ቀርቦ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆበታል፤ ፖሊስም በግለሰቡ ተጭበርብረናል፣ ተታለናል የሚሉ ግለሰቦች ካሉ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአካል አሊያም በስልክ ቁጥር 0111110111 እንዲያመለክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡


ፖሊስ የራሱን የምርመራ ስራ እያከናወነ ነው ያሉት ም/ኮማንደሩ፤ የምርመራ ሂደቱን በተገቢው መንገድ ለመምራት ሲባል ዝርዝር መረጃዎችን ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ራሳቸውን “ዶክተር ኢንጂነር” እያሉ ሲጠሩ የነበሩት ሳሙኤል ዘሚካኤል፤ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ የተመረቁ፣ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም እንደተማሩ በመግለፅ፤ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለመምህራንና ለተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግሮች ያደርጉ እንደነበር መዘገቡ ይታወቃል፡፡ ተጠርጣሪው እነዚህ መረጃዎች በተለያዩ ሚዲያዎች መሰራጨታቸውን ተከትሎ ለየትኛውም የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ምላሽ ሳይሰጡ ከሃገር መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተርፖል ዲቪዥን አማካይነት በቁጥጥር ስር ውለው፣ ማክሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል፡፡
http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment