Wednesday, August 27, 2014

ዋሊያዎቹ የብራዚል ቆይታቸውን አጠናቀው ተመለሱ፡፡ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል


-  60 የአልጄሪያ ልዑክ አዲስ አበባ ይመጣል    -  ሳላዲን ሰይድ ዛሬ ቡድኑን ይቀላቀላል

በሚቀጥለው ዓመት ሞሮኮ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅቱን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ 17 ቀን የብራዚል ቆይታውን አጠናቆ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

ለግብፅ አልአህሊ ክለብ የሚጫወተው ሳላዲን ሰይድ ትናንት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ ዛሬ ቡድኑን እንደሚቀላቀልም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

የተነቃቃው የአገሪቱ እግር ኳስ ተጠናክሮ መቀጠል ይችል ዘንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፖርቱጋላዊውን አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶን ቀጥሮ ዝግጅቱን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ አሠልጣኙ ጳጉሜ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከአልጄሪያ ጋር ለሚጠብቃቸው የመጀመርያው ምድብ ማጣሪያ ‹‹ይጠቅመኛል›› ያሉትን የአቋም መመዘኛ የወዳጅነት ጨዋታ በብራዚል ከተለያዩ አምስት ክለቦች ጋር ጨዋታ አድርገው በሁለቱ አቻ ተለያይተው፣ በሦስቱ ተሸንፈው ተመልሰዋል፡፡

ታክስና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ሳያካትት 18,000 ዶላር ወርሐዊ ክፍያ የተቆጠረላቸው አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ፣ ዋሊያዎቹን ከተረከቡ በኋላ ከዝግጅቶቻቸው ጎን ለጎን የአቋም መገምገሚያ የወዳጅነት ጨዋታ ትኩረት ከሰጡዋቸው ነገሮች መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ እስካሁንም ስድስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መሆናቸውም እየተነገረ ነው፡፡



በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአልጄሪያ አቻው ጋር ጳጉሜ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚጫወት መሆኑን በመጥቀስ አሠልጣኙ በብራዚል ያደረጓቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የሚናገሩ አሉ፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ ውስጥ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡናና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ የነበረው ውበቱ አባተን ጨምሮ በርካታ የዘርፉ ሙያተኞች ከወቅታዊ የኢትዮጵያና የብራዚል አየር ፀባይ ጋር በማያያዝ፣ ብራዚል በኢትዮጵያ ክረምት ወቅት እጅግ በጣም ሞቃታማ ስለመሆኗ በተቃራኒው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ ጨዋታ በሚደረግበት አዲስ አበባ ደግሞ ዝናባማና ቀዝቃዛ መሆኑን በማመላከት መከራከሪያ ነጥቦችን ያቀርባሉ፡፡ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ ብራዚል ላመራ የኢትዮጵያ ቡድን ከሆቴልና መሰል ወጪዎች በስተቀር ለትራንስፖርትና አበል ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጪው ጳጉሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያ አቻውን የሚገጥመው የአልጄሪያ ቡድን ተጨዋቾቹን ጨምሮ 60 ልዑካን ይዞ ለመምጣት ጥያቄ ማቅረቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment