Wednesday, October 30, 2013

ፓርላማው ያለ ማብራሪያ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ አባላትን ሾመ



-‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ አይገደድም›› አፈ ጉባዔ አባዱላ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አባልነት ስምንት ተሿሚዎችን ፓርላማው እንዲያፀድቀው በደብዳቤ በማቅረባቸው የተነሳው የማብራሪያ ጥያቄ ሳይመለስ ፀደቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ በኩል ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስምንት የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን ሹመት ማክሰኞ ዕለት ለፓርላማው አቅርበዋል፡፡

በቦርድ አባልነት ያቀረቧቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በቦርድ ሰብሳቢነት፣ የብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደስታ አስፋው በአባልነት፣ አቶ አማኑኤል አብርሃም በአባልነት፣ አቶ አብይ አህመድ በአባልነት፣ አቶ ገበየሁ በቀለ በአባልነት፣ አቶ አብዲሳ ዘርዓይ በአባልነት፣ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በአባልነት፣ አቶ ዘርዓይ አስገዶም በአባልነት ነው፡፡

የአዲሶቹ ቦርድ አባላት ሹመት እስኪቀርብ ድረስ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ አባል የነበሩ አንድ የፓርላማው አባል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመቱን የሰጡበት ምክንያት እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል፡፡

በሥራ ላይ የነበሩት የቦርድ አባላትን በተመለከተ የተደረገ ግምገማ ሳይኖርና በመልካም የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እያሉ ለምን በአዲስ እንዲተኩ አስፈለገ የሚለውን ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ የሹመት ደብዳቤውን ያቀረቡት የመንግሥት ተጠሪ ምላሽ ካላቸው በሚል ዕድል ለመስጠት ቢሞክሩም፣ ተጠሪው ምላሽ እንደሌላቸው በምልክት ገልጸውላቸዋል፡፡

አፈ ጉባዔው የራሳቸውን ምላሽ ሲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያቀርቡት የቦርድ አባላት ሹመት ላይ ማብራሪያ ለመስጠት አይገደዱም ብለዋል፡፡ ከዚያም ድምፅ ሲሰጥ ማብራሪያ የጠየቁት ግለሰብን ጨምሮ ሹመቱ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment