Wednesday, October 16, 2013

በስራ ሰዓት ፌስ ቡክ እየተጠቀሙ ስራ የሚበድሉን ለመቆጣጠር መመሪያ እየተዘጋጀ ነው


አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) ማህበራዊ ድረ ገጾች ቀላል የመገናኛ ዘዴ ከመሆን ባለፈ የስራ ሰአት እየተሻሙ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ፌስ ቡክን ያለ አግባብ በመገልገል ፥ ውድ የስራ ሰዓትን በማቃጠል ደንበኛን ያጉላላሉ ሲሉም ነው የሚናገሩት።

አስተያየት ሰጭዎቹ እንደሚናገሩት ሰራተኞቹ በስራ ሰአት “ ኦንላይን ” በመሆን ጉዳይ ለማስፈጸም የመጡ ደንበኞችን በአግባቡ ካለማናገር ጀምሮ ስራን ይበድላሉ።

ሁኔታው ወደ ሱስነት እየተቀየር መሆኑንም የሚገልፁ አሉ።



ለደንበኞች መጉላላትና ለስራ መበደል ትልቁ ምክንያት ይኼው አላስፈላጊ ኢንተርኔት አጠቃቀም መሆኑን የሚያነሱት ደግሞ የተለያዩ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ናቸው።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው እነዚህ የስራ ሀላፊዎች ሁኔታው እየጨመረ መምጣቱ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል ባይ ናቸው።

በዘርፉ የተካሄዱት ጥናቶች በስራ ሰአት መሰል ተግባራትን መከወን ምርታማነትን ከመቀነሱም ባሻገር ፈጠራ እና የስራ ተነሳሽነትን እንደሚቀንስ አረጋግጠዋል።

ሰራተኞች ፌስ ቡክን የመሳሰሉ ማህበራዊ ድረ ገጾችን አብዝተው በመጠቀም ስራን እንደሚበድሉ ፥ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባካሄደው ጥናት አረጋግጧል።

ለዚህም የስራ አመራር ቦርዱ አሰራር ለማበጀት ዝግጅት ላይ መሆኑን ፥ በሚኒስቴሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም በቀለ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ፥ በአሁኑ ሰዓት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፖሊሲው እየተሰራ ሲሆን ከፀደቀ በኋላ ትግበራው ይጀመራል።

መመሪያው ሰራተኞች በሻይና በእረፍት ሰዓት ላይ  ብቻ  እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ነው ተብሏል ።
http://fanabc.com

No comments:

Post a Comment