Thursday, June 13, 2013

ሻዕቢያ ያሰማራው የሽብር ቡድን ተደመሰሰ

የሻዕቢያ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባው የሞከረው የሽብር ሃይል በህዝብና በፀጥታ ሃይሎች ትብብር ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ሻዕቢያ በሱዳን ሃምዳይት በኩል አድርጎ ያሰማራቸው የሽብር ቡድኑ አባላት ቀደም ሲል የነፍስ ማጥፋት፤ ስርቆትና መሰል ወንጀሎችን ፈፅመው በኢትዮጵያ መንግስት ሲፈለጉ የነበሩ ሲሆኑ የኢሳያስ መንግስት ለረጅም ግዜ በሽብር ተግባር አፈፃፀም ዙሪያ ስልጠና ከሰጣቸው በኋላ በተለይም በትግራይ ክልልና በዋና ዋና ተቋሞች ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ የላካቸው ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ ለኢሬቴድ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ዘጠኝ አባላት የነበሩት ይህ የሽብር ሃይል ግንቦት 25/2005 ወደ ቃፍታ ሁመራ በረኸት ቀበሌ ሊገባ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ የፀጥታ ሃይሎችና በህዝቡ በጋራ በተሰነዘረበት ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል፡፡

በጥቃቱ የቡድኑ መሪና ምክትሉን ጨምሮ አምስት አባላቱ ሲሞቱ ቀሪዎቹ አራቱ ደግሞ ተማርከዋል፡፡
ከተገደሉትና ከተማረኩት የሻዕቢያ ተላላኪዎች 3 ኤም ፎርቲን፤ 6 ክላሽንኮቭ፤ 2 የውጊያ መነፅር፤ 15 የእጅ ቦንብ፤ 4 ሞባይል፤  2490 የተለያዩ ጥይቶችና በርከት ያለ የኢትዮጵያ ገንዘብ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በህዝባችንና በፀጥታ ሃይላችን የተወሰደው ርምጃ ለሻዕቢያና ተላላኮዎቹም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈፅም የሚሹ ፀረ ሰላም ሃይሎች ትምህርት ያስተላለፈ ነው ብሏል የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢሬቴድ በላከው መግለጫ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለአካባቢው ህዝብና ለፀጥታ ሃይሎቹ ያለውን አድናቆትም ገልጧል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ ወረራ የማድረግ አቅም እንደሌለው የተረዳው የሻዕቢያ መንግስት በሚያደራጃቸው የሽብር ቡድኖች አማካኝነት የሃገራችንን ሰላም በማወክ ልማታችንን ለማደናቀፍ የሚያደርገውን ጥረት በንቃት በመከታተል ለማክሸፍ ያለውን ዝግጁነትም ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
http://www.ertagov.com

No comments:

Post a Comment