Sunday, September 23, 2012

ሕወሓት የትጥቅ ታጋዮቹን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አድረጎ መረጠ


በትጥቅ ትግሉ ወቅት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ን ለበርካታ ዓመታት፣ እንዲሁም ከድል በኋላ ድርጅቱን ለ21 ዓመታት የመሩት የአቶ መለስ ዜናዊን ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ፣ ድርጅቱ የትጥቅ ተጋዮቹን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሾመ፡፡

የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱ የሕወሓት ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡የአራት ድርጅቶች ስብስብ የሆነው ኢሕአዴግ ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው የመተካካት ፖሊሲ መሠረት፣ የአመራር ኃላፊነቶች በትጥቅ ትግሉ ዘመን ላልነበሩ አባሎች እያስተላለፉ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት ባለፈው ሳምንት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያልነበሩ አመራሮችን የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሾሟል፡፡ በዚህም መሠረት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ዲኢሕዴን) ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ ደግሞ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሊቀመንበሩ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ሲሆኑ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ ደግሞ አቶ ሙክታር ከድር ናቸው፡፡ በሁለቱም ድርጅቶች ያሉት አመራሮች ሙሉ ለሙሉ በትጥቅ ትግሉ ያልነበሩ በመሆናቸው፣ የኢሕአዴግ የመተካካትን ፖሊሲ እየተገበሩ ናቸው፡፡ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀመንበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ሲሆኑ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ ደግሞ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲሶቹ አመራሮች የሚመደቡ ቢሆንም፣ አቶ ገዱ ግን ኢሕአዴግን በትጥቅ ትግሉ የመጨረሻ ዘመን የተቀላቁ ናቸው፡፡ በመሆኑም በብአዴን የኢሕአዴግ የመተካካት ፖሊሲ በከፊልም ቢሆን በአመራሮቹ ላይ ተግባራዊ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

አዲሶቹ የሕወሓት አመራሮች ሁለቱም በትጥቅ ትግሉ ወቅት የነበሩ በመሆናቸው፣ ለሕወሓት የኢሕአዴግ የመተካካት ፖሊሲ በደንብ የተዋጣለት አይመስልም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን፣ ‹‹የመተካካት ፖሊሲው በፍጥነት የሚተገበረው በትግል ወቅት አመራር ለነበረ ነው፡፡ ታጋይ የነበረ ሁሉ አመራር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ይህ የሚመለከተው በአመራር ላይ የነበሩትን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግሉ የነበሩትንና ሥራ አስፈጻሚዎች ሙሉ ለሙሉ ከሥልጣን እንደማያስወጣ የገለጹት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ የቀድሞ አመራሮች እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በየጊዜው እየወጡ ለአዳዲሶቹ አመራሮች ያስረክባሉ ብለዋል፡፡

ዶክተር ደብረፅዮን የድርጅቱ አመራር ለመሆን የዕድሜ ጣሪያው ሌላው የሚታይ ጉዳይ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡ የሕወሓት ፕሮግራም ያለና የነበረ ስለሆነ የሚቀየር ነገር አይኖርም ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን፣ ቀጣዩ ሥራ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማስቀጠል ይሆናል ብለዋል፡፡ ‹‹የሚለወጥ ነገር ካለ ወደፊት የምናየው ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com