Sunday, September 23, 2012

የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ ንብረት ታገደ


በሽብር ወንጀል በተመሠረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው 18 ዓመታት የተፈረደበትጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ እድሜ ልክ የተፈረደበት የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል አንዱዓለም አራጌና  በሌለበት 15 ዓመታት የተፈረደበት አበበ በለው፣ ንብረት ላይ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ የእግድ ትዕዛዝ መተላለፉን ያስታወቁት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ  ብርሃኑ ፀጋዬ ሲሆኑ ፍርደኞቹ ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል ለአገርና ለሕዝብ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑና ሕጉ በሚያዘው መሠረት የተፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በቂ ጥናት በማድረግ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ  98 (1,2) እና በጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001(27) መሰረት፣ ለፍርድ ቤቱ የእግድ ትዕዛዝ እንዲተላለፍለት ማቅረቡን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ፍርድ ቤቱም በተጠየቀው አግባብ መሠረት ትዕዛዙን ማስተላለፉን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም የአቶ አንዱዓለም አራጌ ንብረት የተባለውና በባለቤታቸው በዶክተር ሰላም እሸቴ ልየው  ስም ተመዝግቦ የሚገኝ የሰሌዳ ቁጥሩ 2-79095 የቤት መኪና፣ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ስም የተመዘገበው፣  በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቁጥር 158 ባለ አንድ ፎቅ የመኖሪያ ቪላ ሕንፃ ፣ በ150 ሜትር ካሬ ላይ ያረፈና ከእናቱ በውርስ ያገኘው በየካ  ክፍለ  ከተማ ቀበሌ 01/02 የሚገኝ   መኖሪያ ቤት፣ በባለቤቱ  በወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል  ስም የተመዘገበ አቶዝ የቤት መኪና እንዳይሸጡ እንዳይለወጡና በሌላ በማንኛውም መንገድ ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ ፍርድ ቤቱ ማገዱ ታውቋል፡፡ እንዲሁም በሌለበት 15 ዓመታት እስር የተፈረደበት አበበ  በለው፣  በባለቤቱ ስም ተመዝግቦ በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 20/21 የሚገኘው ባለ አንድ ፎቅ የመኖሪያ ቪላ ሕንፃም በተመሳሳይ መንገድ የእግድ ትዕዛዝ ተላልፎበታል፡፡

እነ አንዱዓለም አራጌ፣ የፀረ - ሽብርተኝነት ሕጉን በመተላለፍ በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኛነቱ ለተፈረጀው ከግንቦት 7 ድርጅትን ዓለማ በመደገፍና መረጃ በመለዋወጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለማፈራረስ፣ አሲረዋል፣ ተንቀሳቅሰዋል፣ ዜጎችን አደራጅተዋል፣ መልምለዋል፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ከወገኑ ፀረ - ኢትዮጵያውያኖች ጋር ተገናኝተዋል…  በማለት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ፋሲል የኔዓለም፣ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ፣ ጋዜጠኛ አብይ ተክለማርያምን ጨምሮ  በድምሩ 24 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱን፣ ጋዜጠኛ  እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ ስምንት ተከሳሾች በአገር ወስጥ ሆነው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ  ጥፋተኛ  ተብለው  የጹኑ እስራት ቅጣት እንደተወሰነባቸውና ሌሎቹም በሌሉበት እስከ እድሜ ልክ እስራት እንደተወሰነባች መዘገባችን ይታወሳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment